የናይጄሪያ የባህር ላይ ወንበዴዎች የስዊዘርላንድ መርከበኞችን አገቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእቃ ጫኝ መርከብ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ 12 የስዊዘርላንድ የመርከብ ድርጅት ሰራተኞች በናይጄሪያ የውሃ ክልል ውስጥ በባህር ወንበዴዎች ታግተዋል።
ማሶኢል የተባለው መርከብ ድርጅት እንዳስታወቀው ''ኤም ቪ ግላረስ'' የተባለው እቃ ጫኝ መርከብ ስንዴ ጭኖ ''ከሌጎስ'' ወደብ በመነሳት ወደ ''ሃርኮርት'' በመጓዝ ላይ እያለ ነበር ቅዳሜ ዕለት በወንበዴዎቹ ጥቃት የደረሰበት።
የወንበዴው ቡድን አባላት ረጃጅም መሰላሎችን በመጠቀም ወደ መርከቡ እንደገቡና አብዛኛውን የመገናኛ መስመሮችን ከጥቅም ውጪ እንዳደረጉ ድርጅቱ 'ለኤኤፍፒ ገልጿል።
45 ደቂቃ በፈጀው የወንበዴዎቹ ጥቃት ከ19 የመርከቡ ሰራተኞች መካከልም 12ቱን አግተዋል።
ከታገቱት መርከበኞች መካከል ሰባቱ ከፊሊፒንስ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ከስሎቬኒያ፣ ዩክሬይን፣ ሮማኒያ፣ ክሮሺያ እና ቦስኒያ መሆናቸውን ሮይተርስ የናይጄሪያ የባህር ጉዳዮች መስሪያ ቤትን እንደ ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል።
የታጋቾቹ ቤተሰቦች ስለሁኔታው እንደተነገራቸውና ጉዳዩንም በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ የመርከብ ድርጅቱ ቃል አቀባይ ገልጸዋል። በጉዳዩ የዓመታት ልምድ ያካበቱ የተባሉ ባለሙያዎች ታጋቾቹን ለማስለቀቅ እየጣሩ መሆናቸውንም ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።
የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከታጋቾቹ መካከል አንድም የስዊዘርላንድ ዜግነት ያለው ሰው አለመኖሩን ተናግዋል።
በናይጄሪያ የውጪ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች እንዲሁም ታዋቂ ናይጄሪያውንን አግቶ ማስለቀቂኣ ገንዘብ መጠየቅ የተለመደ ነው።












