ለኡጋንዳዊው ሙዚቀኛና ተቃዋሚ ቦቢ ዋይን በተደረገ ሰልፍ 70 ሰዎች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዎሪ ሙሴቬኒ ተቺና ተቃዋሚ የፓርላማ አባል የሆነው ኡጋንዳዊው ዘፋኝ መታሰርን በመቃወም በርካቶች ከቅዳሜ ጀምሮ በአገሪቱ መዲና ካምፓላ የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
እስከ ትናንትና ማለትም የተቃውሞው ሶስተኛ ቀን 70 የሚሆኑ ተቃውሞ ሰልፈኞች በፖሊስ ታስረዋል።
ተቃውሞ ሰልፈኞቹ ጎማ በማቃጠል፣ ድንጋይ በመወርወርና መንገድ በመዝጋት ድምፃቸውን ለማሰማት ሞክረዋል።
ፖሊስም አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል ወደ ላይም ጥይት ተኩሷል።
የኡጋንዳ ህግ ባለሙያ ማህበረሰብ በአገሪቱ የተቃውሞ ድምፆችን ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን አካሄድ እየተቃወመው ነው።
ተቃውሞ ሰልፈኞቹ አደባባይ የወጡት በእስር ላይ የሚገኘው ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ሮበርት ካያጉላኒ ወይም በሙዚቃ ስሙ የሚታወቀው ቦቢ ዋይን ድብደባ ደርሶበታል በሚል ነው።
ሙሴቬኒ ግን በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ቦቢ ዋይን ምንም አይነት ድብደባም ሆነ አካላዊ ጉዳት እንዳልደረሰበት ተናግረዋል።
ባለፈው ወር ቦቢ ዋይን መንግስት ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ ግብር ለመጣል ያወጣውን ህግን በመቃወም ከብዙዎች ጋር ሆኖ ተቃውሞ ሰልፍ ወጥቶ ነበር።
የኡጋንዳ ገዥው ፓርቲ ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት(ኤን አር ኤም) በአገሪቱ ፕሬዘዳንት የመሆን እድሜን በ75 የሚገድበውን የህገመንግስት አንቀፅ ለማውጣት ሲደረግ ትልቅ ተቃውሞ የመራው ቦቢ ዋይን ነበር።
ቦቢ ዋይን በፓርላማ ድምፃቸውን ከሚያሰሙ ተቃዋሚዎች ግንባር ቀደሙ ነው።












