ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታወቀ
የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታወቀ።
ኦብነግ በመንግሥት በኩል ለንግግርና ለሰላም እየተወሰዱ ያሉትን አዎንታዊ እርምጃዎችን በመገንዘብ ከእሁድ ሐምሌ 06፣ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተኩስ አቁም ማወጁን ገልጿል።
ግንባሩ በሶማሌ ክልል ከመንግሥት አንፃር የሚያካሄደውን ወታደራዊና የደህንነት ተልዕኮዎችን በድርድር ስምምነት ላይ እስኪደረስ ድረስ ማቆሙን አሳውቋል።
የኦብነግ ቃል-አቀባይ የሆኑት አብዱልቃድር ሃሰን ሄርሞጌ ''በሶማሌ ክልል ውስጥ ሰላም ሰፍኖ ማየት እንፈልጋለን። የክልሉ ህዝብ ለረዥም ዓመታት በጭቆና ውስጥ ነው የቆየው። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና በክልሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ውይይት ማድረግ ያስፈልገናል'' ብለዋል።
በቃ-አባዩ አብዱልቃድር ሃሰን ሄርሞጌ የሚመራ የኦብነግ ልዑክ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።
ኦብነግ በተጨማሪም በአንድ ወገን ላወጀው የተኩስ አቁም የኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ የተጀመረው የሰላም ሂደት እንዲፋጠን ጠይቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኦብነግን ጨምሮ ኦነግ እና ግንቦት 7ን ሽብርተኛ መባላቸው ይሰረዝ ዘንድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የላከለትን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ከተወያየበት በኋላ ማጽደቁ ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና የመንግሥት ኮሚኬሽን ጉዳዮች ጸ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
ፓርቲው ያለፉትን ሶስት ቀናት በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ሁከት በተመለከተ ጥልቅ ግምገማ ካደረኩ በኋላ አህመድ ሺዴን የፓርቲው ሊቀመንብር በማድግ በሙሉ ድምጽ መርጫለው ብሎዋል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብዲ ሙሃመድ ኡመር ከክልሉ ፕሬዝዳንትነታቸው ቢነሱም በበፓርቲ ሊቀመንበርነታቸው ይቀጥላሉ ተብሎ ነበር።