በእንግሊዝ የጠጪዎች ቁጥር ማሽቆልቆል ኮማሪዎችን አሳስቧል

በጠጪ እጥረት ምክንያት የሚዘጉ መጠጥ ቤቶች ቁጥር በእንግሊዝ እያሻቀበ ነው።

ስለ ጠጪዎች እና መጠጥ ቤቶች መብት ከ40 ዓመታት በላይ የተጋው በምህፃረ ቃሉ ካምራ በሚል የሚጠራው ተቋም እንዳስታወቀው ፤በያዝነው የጎረጎስያዊያኑ ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 476 መጠጥ ቤቶች ተዘግተዋል።

በ2017 የመጨረሻ ስድስት ወራት 13 መጠጥ ቤቶች መዘጋታቸውንም አስታውሷል።

የተቋሙ ሊቀመንበር ጃኪ ፓርከር መጠጥ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦ ለመጠጣት በእጅጉ ውድ በመሆኑ በርከት ያሉ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ መጎንጨትን ስለመምረጣቸው ተናግረዋል።

በመጠጦች ላይ እና በመላ የንግድ ስራው ላይ በሚጣሉ ቀረጦች ለመጠጥ ሻጮች ፈተና መተውን የሚያነሳው ተቋሙ አንድ ብርጭቆ መጠጥ ከሚሸጥበት ዋጋ ሲሶው ቀረጥ ለመሸፈን እንደሚውል በማንሳት ይከራከራል።

እንደ ካምራ ከሆነ መጠጥ ቤቶች ለእንግሊዝ ኢኮኖሚ በየዓመቱ 23.1ቢሊየን ፖውንድ ያበረክታሉ።