ደቡብ ኢትዮጵያ፡ ያልተነገረለት የኮንሶ ጥያቄ

የኮንሶው ባህላዊ ንጉሥ ካላ ገዛኸኝ
የምስሉ መግለጫ, የኮንሶው ባህላዊ ንጉሥ ካላ ገዛኸኝ የኢንጂነሪንግ ምሩቅ ናቻው

በዞን ወይም በክልል እንደራጅ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተነሱ ነው። ከእነዚህም መካከል የኮንሶዎች በዞን እንደራጅ ጥያቄ አንዱ ነው። ትናንት ኮንሶዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከወጡ በኋላ የተደረጉ ለውጦችን ለማበረታት ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ የተስተጋባውም ይሀ ጥያቄ ነበር።

የኮንሶ ዞን የመሆን ጥያቄ፣ በኮንሶ የቀደሙ ተቃውሞዎች በጊዴሎና በአርባ ምንጭ የሚገኙ እስረኞች ጉዳይ የሰላማዊ ሰልፉ ዋነኛ አጀንዳዎች ነበሩ።

በሌላ በኩል ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ኮንሶዎች እንደሚገባው አልወከሉንም ያሏቸው በክልል፣ በፌደሬሽንና በህዝብ ተወካዮች ያሉ እንደራሴዎቻቸው እንዲነሱ ያቀረቡት ጥያቄም ዳግም በሰላማዊ ሰልፉ ተነስቷል። ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ኮንሶዎች የዞን ጥያቄ ካነሱ ጀምሮ የትናንትናው ለ23ኛ ጊዜ ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ነው።

የኮንሶዎችን በዞን እንደራጅ ጥያቄ ተከትሎም ቀውሶች ደርሰዋል። የሰው ህይወት ጠፍቷል። ብዙዎች ለእስርና ስደት ተዳርገዋል። ታስረው ከነበሩት መካከል የኮንሶ ብሄር ባህላዊ ንጉሥ ካላ ገዛኸኝ ወልደ ዳዊት አንዱ ነበሩ።

በእርከን አሰራራቸው በአለም አቀፍ መድረክ የተነገረላቸው ኮንሶዎች ያነሱት ጥያቄ ብዙ እንዳልተባለለት እና እንዳልተነገረለት ብዙዎች ይስማማሉ።

የኮንሶ ጥያቄ?

ካላ ገዛኸኝ እንደሚሉት የኮንሶ ብሄር በዞን እንደራጅ ጥያቄ፤ ባሉበት የደቡብ ክልል ያለ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲሁም ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር አንድ ላይ በሚገኙበት ዞን የብሄሩ አባላት በማንነታቸው የሚደርስባቸው ጉዳትና ብሶት የወለደው ነው።

"ቀበሌዎች ተቀንሰውብናል። በዞኑ በነበረ የስልጣን ሽኩቻ ከአጎራባች ብሄረሰቦች ጋር የነበረን ግንኙነትም ሻክሮ ነበር" የሚሉት ካላ ገዛኸኝ ነገሮች ይሻሻላሉ በሚል አራት ዓመታትን በተስፋ ከጠበቁ በኋላ በዞን እንደራጅ ጥያቄያቸውን እንዳነሱ ይናገራሉ።

በህዝብ ብዛት፣ በተማረ የሰው ሃይል፣ በገቢ ምንጭና በኢኮኖሚ አቅም ህገመንግስቱ ከሚያስቀምጠው መስፈርት አንፃር ጥያቄው ተገቢ እንደነበር ያምናሉ።

የጥያቄውን መነሳት ተከትሎ አካባቢው ላይ በተፈጠረ ቀውስ ብዙዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ህይወት መጥፋቱን፣ ብዙዎች ከስራ መባረራቸውንና መታሰራቸውን ይገልጻሉ። እሳቸውም ለሳምንታት ታስረው እንደነበር ያስታውሳሉ።

በመጨረሻ በተሰጣቸው መልስ ኮንሶዎች ደስተኛ ነበሩ። መልሱ ግን 'ዞን መሆን አትችሉም' የሚል ነበር።

ካላ ገዛኸኝ እንደሚሉት እንደ ፍላጎትህ እንዳሰብከው አይሆንልህም የተባለው የኮንሶ ብሄር ነገሩን ከደስታም በላይ በሆነ ስሜት ነበር የተቀበለው።

የፈለጉትን ስለተከለከሉ ደስታ እንዴት?

"የደቡብ ክልል ለዚህ ዓይነት ጥያቄ በፅሁፍ መልስ ሲሰጥ የኮንሶ የመጀመሪያው ነበር። እኛም በምላሹ ክልሉን አመስግነናል። ተከልክለው እንዴት ይደሰታሉ የሚለው በክልሉ ዘንድ አግራሞትን ፈጥሮ ነበር" በማለት ጊዜውን ያስታውሳሉ።

መልሱ ምንም ይሁን ምን ደስታ የተሰማቸው ጉዳያቸው በቁም ነገር በመታየቱ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ በራሱ የሚያሳየው ነገር አለ። ቦታ የማግኘትና የመደጥ የኮንሶዎች ንፁህ ፍላጎት።

ከዚያም ጥያቄአቸውን ህግ እንደሚፈቅደው ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ይዘው ሄዱ። በዚህ እርምጃቸው ግን ክልሉ ደስ ስላልተሰኘ የተለያዩ እርምጃዎችን እንደወሰደባቸው ይገልፃሉ።

ጥያቄያቸውን ይዘው አዲስ አበባ ላይ ከቀድሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲሁም ከፌደራል ጉዳዮችና ከአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ጋር እየተወያዩ ነበር።

የያኔው አፈ ጉባኤ ጉዳዩ ክልሉን ይመለከታል በማለት ወደ ክልሉ ሲመልሱት ውሳኔው ህገመንግስቱን የተከተለ አይደለም በማለት ቅሬታቸውን አስገብተው አቤቱታቸው ተቀባይነት አግኝቶ እያለ ዳግም መታሰራቸውን ይናገራሉ።

ካላ ገዛኸኝ ከሁለት ዓመት እስር በኋላ ከበርካታ የፖለቲካ እስረኞች ጋር የተለቀቁት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው።

የኮንሶው ንጉስ ካላ ገዛኸኝ

ካላ ገዛኸኝ ከወንድማቸው ጋር
የምስሉ መግለጫ, እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 የኮንሶው ንጉስ ካላ ገዛኸኝ ለአንድ አለም አቀፍ ስብሰባ ከወንድማቸው ጋር በሞስኮ ተገኝተው ነበር

ካላ የቤተሰባቸው መጠሪያ ሲሆን ኦክላ (ንጉስ) የሚል ማእረግ አላቸው። እሳቸው ከዘጠኙ የኮንሶ ጎሳዎች ከርቺሳ ከሚባለው ጎሳ ሲሆኑ በዚህ ጎሳ ግጭት ቢፈጠር ለማብረድና እርቅ ለማውረድ በፍትህ ጉዳይ ለመዳኘትም የሚታመነው የካላ ቤተሰብ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ካላ ገዛኸኝ ከመከላከያ ኢንጂነሪነግ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢንጂነሪንግ ዲፕሎማ ያገኙ ሲሆን የአባታቸውን ህልፈት ተከትሎ ስራቸውን አቋርጠው በአባታቸው ምትክ ህዝባቸውን ለማገልገል ወደ ቀያቸው ተመለሱ።

ካላ ገዛኸኝ የኮንሶ ባህላዊ መሪ በመሆን የኮንሶ ጥያቄ መሪ የሆኑትም በዚሁ መልክ ነው። የኮንሶን ጥያቄ ለማራመድ ለተሰጣቸው ሃላፊነት ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ።

ከኮንሶ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩ ብዞዎች ቢለቀቁም አሁንም በእስር ላይ ያሉ አሉ። ያለፈውን እንደ አንድ አጋጣሚ ቆጥረው አሁንም የዞን እንሁን ጥያቄያቸውን እንደሚያሰሙ ካላ ገዛኸኝ ይናገራሉ።

"ጉዳቶች ደርሰዋል። ግን ያለፈ አልፏል ወደ ኋላ ማየትና በቀል እንደማያስፈልግ ነው ህዝቡን እየመከርኩ ያለሁት። በዚሁ እንቀጥላለን" ብለዋል።