የባርሳ ሴቶች ከወገብ በላይ ራቁት ለመሆን ድምጽ ሰጡ

የባርሳ መንደር ሴቶች ከእንግዲህ ከወገብ በላይ ለምን የዋና ልብስ አለበሳችሁም የሚላቸው የለም

የፎቶው ባለመብት, Michael Bezjian

የምስሉ መግለጫ, የባርሳ መንደር ሴቶች ከእንግዲህ ከወገብ በላይ ለምን የዋና ልብስ አለበሳችሁም የሚላቸው የለም

ባርሴሎና አቅራቢያ በምትገኝ መንደር የሚገኙ ሴቶች በሕዝብ የመዋኛ ሥፍራ ከወገብ በላይ ራቁታችንን መሆን ይፈቀድልን በሚል ያነሱት ጥያቄ መልስ አገኘ።

የመንደሯ ነዋሪዎች ድምጽ እንዲሰጡበት ተደርጎ ከመቶ 61 እጅ ነዋሪዎች "መብታቸው ነው" ሲሉ ቀሪዎቹ 39 ከመቶ ነዋሪዎች "ድርጊቱ ያሳፍራል፤ በሕግ ይከልከል" ብለው ድምጽ ሰጥተዋል።

የካታሎኒያ የአውራጃ አስተዳደር ባዘጋጀው በዚህ የድምጽ መስጠት ሂደት "ራቁታችንን እንሁን" የሚሉት በከፍተኛ ድምጽ በማሸነፋቸው ከዚህ በኋላ በዚያች አውራጃ ከወገብ በላይ መለመላቸውን መቅረት በሕግ ተፈቅዶላቸዋል።

የመንደሪቷ ሴቶች ለዚህ ሰፊ የእርቃን መብት የተፋለሙት ባለፈው የፈረንጆች በጋ የጸጥታ ኃይሎች የመዋኛ ልብስ (ቢኪኒ) ያልለበሱ ሴቶችን እንዲለብሱ በማስገደዳቸው ነው ተብሏል።

በመዋኛ ሥፍራው ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ ሕይወት አድን ዋናተኛ በወቅቱ ለፖሊስ ደውሎ "አንዳንድ ሴቶች ከወገብ በታች መለመላቸውን ናቸው" በሚል ጥቆማ በመስጠቱ ነበር ፖሊስ ወደ ሥፍራው ደርሶ ሴቶቹን የዋና ልብስ እንዲሊብሱ ያስገደዳቸው።

ይህ ክስተት በሴት መብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ ቁጣን በመቀስቀሱ የፖሊስን ድርጊት ለመቃወም የአካባቢው ወንዶች ሳይቀሩ ደረታቸው ላይ የጡት ጫፍ በመሳል ወደ መዋኛው ሥፍራ በማቅናት የፖሊስን ክልከላ በማውገዝ ተቃውሞ አሰምተው ነበር።

ከዚህ በኋላ ግን የዚህች የባርሴሎና መንደር ሴት ነዋሪዎች በሕዝብ የመዋኛ ሥፍራዎች ከወገብ በላይ ራቁታቸውን መዋኘት በሕግ ተፈቅዶላቸዋል።

በሰሜን ባርሴሎና 35 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ይህች መንደር 8ሺህ ነዋሪዎች አሏት።