ካለሁበት 34፡ በአሜሪካ የህግ አስከባሪዎች ከማንም ሰው በበለጠ ህግን ይጠብቃሉ፤ ያከብራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Gamachuu Aabbugaree
ገመቹ አቡጋሬ በዱኬ እባላለው። በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ፤ ጊዶ ኮምቦልቻ ባቱ አካባቢ ነው ተወልጄ ያደግኩት። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እዛው ነው ተከታተልኩት።
የከፍተኛ ትምህርቴን ለመከታተል ደግሞ ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሄድኩ። የመጀመሪያ ዲግሪዬን እዛው አገኘሁ። ትምህርቴን ጨርሼ ከተመረቅኩኝ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች ውስጥ በሂሳብ ሰራተኝንት ስሰራ ቆየሁ። ከዚም ዲቪ ደርሶኝ ወደ አሜሪካ መጣሁ።
አሁን የምኖረው በሳውዝ ዳኮታ ግዛት ሲ ፎልስ በምትባል ከተማ ነው። ይቺ ከተማ በጣም የተዋበች እና ዘመናዊ ናት። ከፍ ካለ ስፍራ የሚፈሰውና ከተማዋን አቋርጦ የሚሄደው ወንዝ ደግሞ ልዩ ውበት ሰጥቷታል።

የፎቶው ባለመብት, Gamachuu Aabbugaree
ሃገሬን እና አሜሪካን ማወዳደር ይከብደኛል። አሜሪካ በቴክኖሎጂ የመጠቀች ናት፤ ኢትዮጵያ ግን ገና በማደግ ላይ ያለች ሃገር ነች። እዚህ አገር ሁሉም ነገር በተግባር ነው የሚገለጸው። ህጎች እንኳን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያን ከአሜሪካ የሚለያት ዋናው ነገር ብዬ የማስበው የህግ አተገባበር ሥርዓቱ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ ህጎች አሉ፤ ነገር ግን ልዩነቱ ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ ነው። እዚህ አገር ህጎች ተግባራዊ የሚደረጉት በሰዎች ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂም ጭምር ታግዘው ነው። የተለያዩ ካሜራዎች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ህግን ለማስከበር ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ህግ አስከባሪዎቹም ቢሆኑ ለህጉ ተገዢዎች ናቸው። የእኛን ሃገር ስንመለከት ግን ከታች ካለው የህግ አስከባሪ ጀምሮ እስከ ትልቅ ባለስልጣን ድረስ ሁሉም ከህግ በላይ እንደሆኑ ነው የሚያስቡት። እዚህ አገር ግን ከኢትዮጵያ ተቃራኒ ነው።
ህግ አስከባሪዎቹ በግንባር ቀደምነት ለህግ ተገዢ ናቸው። ይሄ ለኔ በጣም ልዩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Gamachuu Aabbugaree
ወደ አሜሪካ በመምጣቴ አተረፍኩ ብዬ የማስበው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ አይደለም፤ ተግባራዊ እና መፍትሄ ላይ ያተከረ የትምህርት ማግኘቴም ጭምር ነው።
የተለየ ስልጣን ወይም ችሎታ ቢኖረኝ በምኖርባት ከተማ ያለውን ከፍተኛ የጤና አገልግሎት እና ለትምህርት የሚደረግ ክፍያ መለወጥ እፈልጋለው። ምክንያቱም ለትምህርት እና ለጤና አገልግሎት የሚከፈለው ክፍያ በጣም የተጋነነ ነው።
እኔ የምኖርበት አካባቢ ብዙ የምግብ አይነቶች አሉ፤ እንደ እንጀራ ግን የሚያስደስተኝ የለም። እዚህ ካሉት ምግቦች የምመርጠው ግን ፒዛ ነው። ከሃገሬ ደግሞ ከሚናፍቁኝ ነገሮች መካከል የሰዉ የእርስ በርስ መከባበር እና ባህል አክባሪነት ሁሌም ከልቤ አይጠፉም።
የምኖርባት ከተማ ብዙ ተፈጥሮአዊ መስህቦች አሏት፤ ለኔ የተለየ ስሜት የሚሰጠኝና የምወደው በከተማዋ መሃል የሚፈሰው ሲ ፎልስ ወንዝ ነው። ከተማዋ ስሟን ያገነችውም ከዚሁ ወንዝ ነው። አካባቢው ለአይን ስለሚማርክ ብዙ ሰዎች መጥተው ይጎበኙታል።

የፎቶው ባለመብት, Gamachuu Aabbugaree
ሁሌም ቢሆን እዚህ ያለውን የተራቀቀ ቴክኖሎጂ እና የተቀናጀ ሥርዓት ስመለከት ሃገሬ ትዝ ትለኛለች። ምናለ ኢትዮጵያም እንደዚህ ብትሆን እላለሁ። እዚህ ሃገር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመጣሁ ያስደነገጠኝ ነገር የሃገሬ ልጆች በተለያዩ ሱሶች እና አደንዛዥ እጾች ተጠምደው ስመለከት ነበር።
ያንን ሁሉ ችግር አልፎ እዚህ ደርሶ፤ የመጣበትን ምክንያት ረስቶ ሰው እንዴት ሱስ ውስጥ ይገባል ብዬ በጣም አዘንኩ። እራስን ለማሻሻል ዋናው ነገር የግል ጥረት እና ውሳኔ እንጂ ከሃገር መውጣቱ ብቻ እንዳልሆነ አስተምሮኛል።
በሆነ ተአምር አንድ ኃይል ሃገሬ ቢወስደኝ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሻሸመኔ መንገድ ላይ የምትገኘው የትውልድ ቦታዬ ብሄድ ደስ ይለኛል። ይህች ከተማ በትንንሽ ሃይቆች የተከበበች በመሆኗ ለኑሮ ምቹ እና ተስማሚ መልከዓ-ምድር አላት።

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦













