ካለሁበት 23፡ ተአምር መሥራት ብችል ለሁሉም ሰው አንድነትና ፍትሕ አመጣ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Beejhy Barhany
ቢጀይ ብርሃነ እባላለሁ። ትግራይ ውስጥ ተወልጄ አሁን በኒዉ ዮርክ ከተማ ነው የምኖረው።
የ7 ዓመት ልጅ ሆኜ ወደ እስራኤል ሄድኩኝ እዚያም ወታደራዊ ሥልጥናና አገልግሎቴን አጠናቀኩኝ።
ከዚያም በአጋጣሚ እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም ለጉብኝት ኒው ዮርክ መጥቼ እግረመንገዴን ሌሎችን ቦታዎች ጎበኘሁ።
ብዝሃነት የሚታይባት ከተማ በመሆኗ ኒው ዮርክን ወደድኳትና እዚያው ለመቆየት ወሰንኩኝ።
እዚህ ከተማ በተለየ ሁኔታ ያስታዋልኳቸው ነገሮች አሉ። ማህበረሰባችን ሰው ያሰባስባል ደግሞም በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ይከብራል።
በአሜሪካ ግን ተቃራኒው ነው የሚታየው። ግለኝነት አለ፤ በዕድሜ የገፉ ሰዎችም ወደ አረጋውያን መንከባከበያ ተቋማት ይልካሉ እንጂ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቆዩ አይደረግም።

የፎቶው ባለመብት, Beejhy Barhany
በኒው ዮርክ ከተማ የጽዮን ምግብ ቤት ባለቤት ነኝ። ከሃገሬ የሚናፍቀኝ ደግሞ በዋነኝነት ንፁህ አየሩ ነው። በተለይ ወደ አክሱም አካባቢ ያለውን አየር በጣም እወደዋለሁ፤ በጣምም ይናፍቀኛል።
ከታሪክ አንፃር እዚህ ሃገር ደስ የሚያሰኘኝ ጽዮን ብዬ የሰየምኩት ይሄው ምግብ ቤት ያለበት ቦታ ነው። ምክንያቱም ስፍራው በጣም ታሪካዊ ነው።
ድሮ ማልኮም ኤክስ፤ ረድፎክስ፤ ፖሊ ፖከር እዚህ ቦታ ላይ ሠርተው ነበር። አሁን ይሄ ቦታ 'ፒሚ ሻጪክን' ነው የሚባለው በዚያ ላይ የ'ሹጋር ሂል'ን ታሪክ ያዘለ ቦታ ነው።
ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የመጡ ሰዎች ጋር አብረን ነው የምንሠራውና የተለያየ የምግብ ዓይነቶች በጋራ እናዘጋጃለን። በተጨማሪም ከብዙ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ ችያለሁ።
በጽዮን ምግብ ቤት ለኢትዮጵያም ለአሜሪካም ሕዝብ ተስማሚ የሆነ ዓይነት ምግብ አቀርባለሁ። በሽንኩርትና በእንቁላል የሚቁላላው ሳልመን ዓሣ በእንጀራ ሲቀርብ ተወዳጅ ምግብ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Beejhy Barhany
ተአምር መሥራት ብችል ለሁሉም ሰው አንድነትና ፍትሕ አመጣ ነበር። ምክንያቱም ብዙ ሰው ያጣቸው ነገሮች ናቸው።
በኒው ዮርክ ከተማ ኢትዮጵያን የሚያስታውሰኝ ነገር ... የተለያየ ቀለም ያላቸው የ'ሃርለም' ሕዝቦች መኖራቸው ነው።
ለምሳሌ አንድ ቀልድ አዋቂ ሮማዊን አንድ ጋዜጠኛ 'ከየት ነው የመጣኸው?' ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ ከ125 ሃርለም ሊትል ኢትዮጵያ ነው የመጣሁት ብሎ ነበር የመለሰለት። 125 ሃርለም ሊትል ኢትዮጵያ የሰፈሩ ስም ነው።
አዚህ የመጣሁት የ22 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው። ልጅ ስለነበርኩ በወቅቱ ሁሉ ነገር ይከብደኝ ነበር። እንዲሁም ደግሞ ከፍተኛ የቤተሰብ ናፍቆት ነበረብኝ።
ይሁን እንጂ ይሄን ሁሉ አልፌያለሁ። ስኬታማ ለመሆን በእንዲህ ዓይነት ፈተናዎች ማለፍ ግድ ነው። አሁን ደግሞ በኒው ዮርክ 22 ድፍን ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ።
ወደኋላ ተመልሶ ማየት የሚቻል ቢሆን ኖሮ፥ የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበትን ጊዜና ውግያው ሲካሄድ ማየት ብችል ደስ ባለኝ ነበር።

ለኤደን ሃብተሚካኤል እንደነገረቻት
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦














