ካለሁበት 22፡ የተወለድኩባት፣ የቤተሰብ ፍቅርና ህይወት ያሞቃት ቤቴ ትናፍቀኛለች

የፎቶው ባለመብት, Nestanet Tesfamichael
ስሜ ነፃነት ተስፋሚካኤል ይባላል። የተወለድኩት ኢትዮጵያ ነው፣ ያደግሁት ግን ኤርትራ ነው።
የፊልም ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ጋዜጠኛና የሁለት ልጆች እናት ነኝ።
ከኤርትራ ወደ ሆላንድ ሐውዘን ወደሚባል ቦታ የመጣሁት እ.አ.አ. በ2005 ነበር። ወደ ሆላንድ የመጣሁት ልቤን ፍለጋ ነበር።
ባለቤቴ ስደተኛ ነበረ፣ ኑሮውንም በሆላነድ ነበር ያደረገው። 'በቤተሰብ በማሰባሰቢያ' ፕሮግራም ምክንያት እኔም ከእርሱ ጋር አንድ ላይ ለመሆን ወደ ሆላንድ አቀናሁ።
ከጊዜ በኋላ ቋንቋም ተማርኩኝ ሁለት ልጆችም አፈራን።
እዚህ መመገብ ከምወዳቸው ነገሮች ነገሮች መካከል የድንች ጥብስ በማዮኔዝ መብላት ነው። ምክንያቱም ርካሽም ነው ደግሞም ይጣፍጣል። ነገር ግን አሁኑ እንደሚያወፍር ስላወቅኩኝ ለመቀነስ እየሞከርኩኝ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Nestanet Tesfamichael
ኔዘርላንድን ከኤርትራ ጋር ሳነፃጽር የሚያስደንቀኝ ኤርትራን አንድ ሦስተኛ እያከለች 17 ሚሊዮን ሕዝብ መያዟ ነው።
ሃገሪቱ ባላት መሰረተ-ልማት እጅግ ያደገች ብትሆንም በአኗኗርና በባህል ግን እኛም ጥሩ ነገር እንዳለን አስባለሁ።
ለምሳሌ ማህበራዊ ኑሯዋችን ለፈረንጆቹ የሚስብ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም በደስታም ሆነ በሃዘን ያለን ቅርበትና አንድነት የትም ብንሄድ የሚገኝ አይደለም። ይህንንም እዚህ ማግኘት ባለመቻሌ ብቸኝነት ይሰማኛል።
ሌላ ደግሞ ልዩ የሚያደርገን ነገር ደግሞ የልጆች አስተዳደጋችን ነው። በእኛ ባሕል ወላጆቻችንን ቀና ብለን አይተን እንኳን አናውቅም።
እዚህ ግን ልጅን እንደዚህ እናሳድግ ብንል ልጆቻችንን ከመግደል አይተናነስም። ምክንያቱም በእራሳቸው እንዳይተማመኑ ማድረግ ስለሆነ።
እዚህ ከልጆቼ ባሻገር ቤተሰባዊ ፍቅር የሚሰጠኝ ኪነ-ጥበብ ወይም ጽሐፍ ነው።
ጽሑፍ በወረቀት ላይ ማስፈር፤ ማፃፍ እወዳለሁ። ይህ የዕለት-ተለት ተግባሬ ነውና ደስታን አገኝበታለሁ። ደግሞም የሥነ-ጽሑፍ ችሎታዬንም አዳብርበታለሁ።

የፎቶው ባለመብት, Natsinet Tesfalem
ካለሁበት ሆኜ መስኮቴን ከፈትኩም አልከፈትኩም ሁልጊዜ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ፀጥታው ነው።
ምክንያቱም ፀጥታ ትላንትናን ከዛሬ፣ ውድቀቴን ከመነሻዬ፣ ኑሮዬን ከእረፍቴ የማይበት ምዕራፍ ስለሆነ በፀጥታዬ ውስጥ ነፃነትን አገኛለሁ።
ከዚያ በኋላም የሚዋጋው የአውሮፓ ብርድ ምንም አይመስለኝም።
ከሃገር ቤት የሚናፍቁኝ ወላጆቼና ቤተሰቦቼ ናቸው። ማህበራዊ ኑሮዬና እሠራበት የነበረው የጋዜጠኝነት ሙያዬ ሁሌም ይናፍቁኛል። ግን በተለይ ፀሐይ ትናፍቀኛለች።
ከሆላንድ ዜጎች በተለይ የሚገርመኝ በዕቅድ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ስጦታ ሊያበረክቱ ቢፈልጉ በፌስታል ይዘውት መጥተው ፌስታሉ ግን እንዲመለስላቸው ይጠይቃሉ።
ምክንያቱም ዕቅዳቸው ስጦታውን ማበርከት እንጂ ፌስታሉን መስጠት ስላልሆነ። ከዚህ አንፃር እኛ በባሕላችን ይሉኝታ ስለሚያጠቃን ፌስታል ብንሞት አንጠይቅም።
እኛም ይህንን ከእቅድ ውጪ መሆንንና በይሉኝታ የመያዝ ልምዳችንን መቀየር ብችል ደስ ይለኛል።
በትርፍ ጊዜዬ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ እየሠራሁ እገኛለሁ። እኔ ብቻዬን ሁለት ልጆች አሳድጌ እዚህ ደርሻለሁና ሌሎችን መርዳት እፈልጋለሁ።
በአሁን ጊዜ ፊልም እየሠራሁ ስለሆነ ሰዎች ቢያበረታቱኝና 'ይቅናሽ' ቢለኝ ደስ ይለኛል።
እራሴን በቅፅበት ከሆላንድ አንስቼ በምፈልገው ቦታ ላይ ማግኘት ብችል። የተወለድኩባት፣ ያደኩባት፣ የቤተሰብ ፍቅርና ህይወት ያሞቃት ቤቴ ውስጥ መገኘትን እመኛለሁ።

ለኤደን ሃብተሚካኤል እንደነገረቻት
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍል ለማግኘት ፦














