ስደተኛው የፊልም ባለሙያ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, "መጪው ትውልድ ከእኛ ምን ይወርሳል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።"

ገመዶ ጀማል ይባላል። ከቤተሰቦቹ ጋር ከሃገር ከተሰደዱ ቆይተዋል። ለዚህ ምክንያቱ አባቱ በፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ምክንያት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት በመሸሽ ነው። አባቱን ጨምሮ ከስድስት የቤተሰቦቹ አባላት ጋር በመሆን ኬንያ ገቡ።

ከዛም ወደ ኡጋንዳ በመቀጠልም አሁን ያሉበት የኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ገብተዋል።

ጅማሮ

ወጣቱ ፊልም ሰሪ ገመዶ ጀማል ከልጅነቱ ጀምሮ ለኪነጥበብ በተለይም ለስዕል ትልቅ ፍቅር እንደነበረው ይናገራል።

ከዚህም በተጨማሪ "በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን የፊልም ጥበብ ክፍተት ለመሙላት በማሰብ ነው የጀመርኩት"ይላል።

የካሜራ ጥበብ፣ የምስል እና ድምፅ አርትኦት መስራት፣ እንዲሁም የአዘጋጅነት ሙያዎችን ኖርዌይ በሚገኝ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት ተምሯል።

"ቤተሰቦቼ በጣም ያበረታቱኝ ነበር።" የሚለው ወጣቱ ገመዶ በተለይም አባቱ ፍላጎቱን ከሁሉም በተለየ ይደግፉለት ነበር።

" ለህዝቤ በታማኝነት እንድሰራ ይመክረኝ ነበር። 'ላመንክበት ነገር ብቻህን እንኳን ብትቆም ከዳር አድርሰው' ይለኛል።" በማለት የአባቱን ምክር ያስታውሳል።

ገመዶ ጀማል

የፎቶው ባለመብት, GAMMADO JAMAL

ጥበብ በስደት በራስ ቋንቋ

"ከውጭ ሃገር የምታገኛቸው ዕውቀት እና መሳሪያዎች ብዙ ናቸው" የሚለው ይህ ወጣት ትልቁ ፈተናው ግን በኦሮምኛ የሚተውኑ ተዋንያንን ማግኘት ነው።

በአንድ ወቅት ቀረፃ ሊጨርሱ ሲሉ አንድ ተዋናይ አቋርጦ ሄደ። "በዚህም የተነሳ ፊልሙን ዳግመኛ እንደ አዲስ ለመቅረፅ ተገደን እንደነበር አልረሳም" ይላል።

ይህ መሰናከል ባይሆንበት ኖሮ እስከዛሬ ድረስ ብዙ ፊልሞችን መስራት ይችል እንደነበር ይናገራል።

ይህንን እና ይህን የመሰሉ ውጣ ውረዶችን በፅናት በማለፍ እስካሁን ስድስት የኦሮምኛ ፊልሞችን እና በርካታ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን ሰርቷል።

ከነዚህም ውስጥ አማና እና ጨባሳ በርካታ ተመልካቾች የወደዷቸው ነበሩ። አብዛኞቹ ፊልሞቹ የሚያጠነጥኑት በወቅታዊ የኦሮሞ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሲሆን ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል።

ከዚህም ባሻገር ገመዶ የፊልም አሰራርን በቪዲዮ ድረ-ገፆች ላይ በኦሮምኛ አጫጭር ትምህርቶችን ይሰጣል። የሚሰጣቸው ትምህርቶች የፎቶ አነሳስ ጥበብ፣ የፊልም ቀረፃ እና አርትኦት ላይ ያተኩራሉ።

ወደጥበቡ መግባት ለሚፈልጉ የኦሮሞ ወጣቶች እንደመንደርደሪያ እያገለገላቸው ይገኛል ሲል ገመዶ ይናገራል ።

ገመዶ ጀማል

የፎቶው ባለመብት, GAMMADO JAMAL

የምስሉ መግለጫ, '' ላመንክበት ነገር ብቻህን እንኳ ብትቆም ከዳር አድርሰው''

ወደፊትስ?

ቢሳካልኝ ወደ ሃገር ቤት ተመልሼ ጥበብን ማሳደግ እፈልጋለሁ የሚለው ገመዶ "ሃገር ቤት ያሉ የጥበብ ሰዎችን በሁሉም በኩል ማገዝ እፈልጋለሁ" ይላል።

"ትናንት ዛሬ አይደለም ዛሬ ደግሞ ነገን አይሆንም" የሚለው ገመዶ የኦሮሞ ኪነጥበብ አሁን እያደገ እንደሆነ ይናገራል።

በዐዓለም ላይ እንዳሉ እና በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚሰሩ ፊልሞች አንፃር ካየነው ግን አድጓል ለማለት አያስደፍርም።

ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበሩ ስርዓቶች የኦሮሞን ባህልና ኪነጥበብ ለማሳደግ ተፅእኖ የነበሩ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው።

ነገር ግን ከዚህ አንፃር ሳየው ያን ያህል ወደ ኋላ ቀርተናል የሚያስብለን አይደለም ይላል።

ከዚህም ባሻገር በራሱ በኩል አዲስ የኦሮምኛ ፊልም እያዘጋጀ መሆኑን ነግሮናል።

"ይሀ ፊልም ከዚህ በፊት ከሰራኋቸው ፊልሞች አንድ ደረጃ ከፍ ያለ እንዲሆን ስለምፈልግ በጥሩ መንገድ እየሰራሁት ነው" በማለት ገመዶ ይገልፃል።

ገመዶ ጀማል

የፎቶው ባለመብት, GAMMADO JAMAL

የአምሮ ነፃነት

"በሰው ሃገር በአዕምሮ ባርያ ትሆናለህ አዕምሮህን ተጠቅመህ ነፃ ትወጣለህ" የሚለው ገመዶ " የሰው ልጅ አለም ላይ ሲኖር ሰላም እና ነፃነት ያስፈልጉታል" ይላል።

ገመዶ አሁን በሚገኝበት የሰው ሃገር በነፃነት ይኑር እንጂ ሃገሩን ይናፍቃል።

"የራስ ሃገር ሁሌም እናት ነች፤ በሰው ሃገር አገኘሁ የምለው ነገር ስደተኛ በሚል ስም መጠራት ብቻ ነው።"

ገመዶ ሃገሬ የምገባው ዛሬ ወይስ ነገ ሲል ይተክዛል። አንድ ቀን ግን እንደሚሳካለት ተስፋ ያደርጋል።