ቀጥታ, የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን “ጣቶቻችን አሁንም ቃታው ላይ ናቸው” ሲሉ አስጠነቀቁ

እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት በአሁኑ ጊዜ ኢራን በተጠንቀቅ ላይ እንደሆነች ፕሬዝዳንቷ አስታወቁ። የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እስራኤል ሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃትም "ግልጽ የተኩስ አቁም ጥሰት” ነው ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ከሊባኖስ ጋር ድርድር እንዲጀመር አዘዙ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሠራዊታቸው ከባድ ጥቃት እየፈጸመ ካለባት ሊባኖስ ጋር ሚኒስትሮቻቸው ቀጥተኛ ንግግር እንዲጀምሩ ማዘዛቸውን አስታወቁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ በእብራይስጥ ቋንቋ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከሊባኖስ በኩል ቀጥተኛ ድርድር እንዲደረግ ቀረበ ባሉት “ተደጋጋሚ ጥሪ” መሠረት ካቢኔያቸው ንግግሩን “በአስቸኳይ” እንዲጀምር መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

    ኔታኒያሁ ጨምረውም የሚደረገው ንግግር “ሄዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም በሊባኖስ እና በእስራኤል መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ” ላይ የሚያተኩር ይሆናል ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ይህንን ከማሳወቃቸው ቀደም ብሎ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አዎንስ ብቸኛው መፍትሄ ሁለቱ አገራት ተኩስ አቁም አድርገው “ቀጥተኛ ድርድር” ማካሄድ ነው ሲሉ ተናግረው ነበረ።

    ፕሬዝዳንቱ የሊባኖስ የፀጥታ ኃይሎች “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን” ሕግ የማስከበር ሥራቸውን ሙሉ ለሙሉ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

    እስራኤል የኢራን አጋር የሆነውን የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህን ዒላማ በማድረግ ከአንድ ወር በላይ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ እግረኛ ወታደሮቿንም በደቡባዊ ሊባኖስ አሰማርታለች።

    እስራኤል ባለፉት ሁለት ቀናት ዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ እና በሌሎች በርካታ የሊባኖስ አካባቢዎች በፈጸመቻቸው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

  2. ዴሞክራቶች የትራምፕን ጦርነት የማካሄድ ሥልጣን ለመገደብ እየጣሩ ነው

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእራኤል ጋር በመሆን ኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ደስተኛ ያልሆኑት ዴሞክራቶች፤ የፕሬዝዳንቱን ጦርነት የማወጅ ሥልጣን የሚገድበው ሕግ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለምክር ቤቱ ሊያቀርቡ ነው።

    በአሜሪካ ምክር ቤት አባል የሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት አገራቸው ከኢራን ጋር ባካሄደችው ጦርነት ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ ሰኞ ዕለት ትራምፕ የኢራንን ሥልጣኔ “በአንድ ሌሊት እንደሚያጠፉ” ከዛቱ በኋላ ስጋታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መደረሱ ተነግሯል።

    ከአሜሪካ ምክር ቤት አባላት መካከል ጥቂት የማይባሉትም በፕሬዝዳንቱ ላይ የተሰማቸውን ቁጣ ወደ ሕግ ለመቀየር በአገሪቱ ሕግ መሠረት ፕሬዝዳንቱን ከሥልጣን ለማንሳት የሚያስችለው 25ኛው የሕግ ማሻሻያ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

    ነገር ግን ሕግ አውጪዎቹ ፕሬዝዳቱን ለመቆጣጠር ሊጠቀሙበት የሚችሉት ቁልፍ አሠራር ትራምፕ ጦርነት ለማካሄድ ያላቸው ሥልጣን የሚገድበውን ደንብ ተግባራዊ ማስደረግ ነው።

    ይህ እርምጃ በምክር ቤቱ ተቀባይነት አግኝቶ ከጸደቀ ኮንግረስ እስካልፈቀደ ድረስ የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ አይችልም።

    በየካቲት ማብቂያ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈታቸውን ካሳወቁ በኋላ የፕሬዝዳንቱን ጦርነት የማካሄድ ሥልጣን ለመገደብ በሁለቱም የአገሪቱ ምክር ቤት ድምጽ ቢሰጥም ተቀባይነት የሚያስገኘውን ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል።

    ዛሬም በድጋሚ በምክር ቤቱ የሚገኙ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት በድጋሚ የትራምፕ ጦርነት የማካሄድ ሥልጣንን የሚገድበው ሕግ ተቀባይነት እዲያገኝ ሙከራ ያደርጋሉ።

    ውሳኔው አሁንም ተቀባይነት የማግኘቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ቢሆንም፣ አሜሪካውያን ለጦርነቱ ያላቸውን አቋም ለማሳየት ያስችላቸዋል ተብሏል።

  3. ስለ ኢራን ልናውቃቸው የሚገቡ አንዳንድ እውነታዎች

    ከእስላማዊው አብዮቷ በኋላ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ሆድ እና ጀርባ ሆና የቆየችው ኢራን ለስድስት ሳምንታት ከእነዚሁ አገራት ጋር ከባድ ጦርነት ውስጥ ቆይታለች።

    በዓለም የሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱት መካከል ፋርስ ተብሎ የሚታወቀው ሥልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ ሕዝብ ያላት እና በተፈጥሮ ሀብትም የታደለች ናት።

    ከምዕራባውያን ጋር በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ጥርስ ውስጥ ገብታ በተለያዩ ማዕቀቦች ጫና ውስጥ ቆይታለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጥቃት ሲፈጸምባት ቆይቶ የለየለት ጦርነት ተከፍቶባታል።

    ለ40 ቀናት ያህል ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ስለተፋለመችው ኢራን ልናውቃቸው የሚገቡ ዋና ዋና እውነታዎች እዚህ ይመልከቱ።

  4. በጦርነቱ ከ3,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ያካሄዱት ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በነበሩት ሳምንታት ውስጥ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የኢራን የሕክምና ምርመራ ድርጅት ዋና ኃላፊ የሆኑትን አባስ ማስጄዲ አራኒን ጠቅሰው እንደዘገቡት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በተጀመረው ጦርነት ከ3 ሺህ በላይ ኢራናውያን ሞተዋል።

    በአሜሪካ መቀመጫውን ያደረገው የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪዎች የዜና ተቋም የሆነው ሂራና እንደዘገበው አስከ መጋቢት 29 ድረስ 254 ሕጻናትን ጨምሮ 1,701 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

    የዜና ወኪሉ ጨምሮም 1,221 የኢራን ጦር ሠራዊት አባላት እና 714 ማንነታቸው ያልተለዩ ሰዎች ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተገድለዋል ብሏል።

    ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ሌሎች ድርጅቶች በኢራን ውስጥ ለመንቀሳቀስ ስለማይፈቀድላቸው በሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው።

    በተጨማሪም ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ በመላው አገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ መረጃዎችን ማግኘት እና ማጣራት አዳጋች ሆኗል።

  5. እስራኤል ነዋሪዎች ከተለያዩ የቤይሩት አካባቢዎች እንዲወጡ አዘዘች

    በሄዝቦላህ "ወታደራዊ መሠረተ ልማቶች" ላይ ላይ ተጨማሪ ጥቃት የመፈጸም ዕቅድ የያዘችው እስራኤል፤ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ የከተማ ዳርቻዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፈች።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ አቪቻይ አድራኢ በእነዚ አከባቢዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ እስራኤል "እናንተን የመጉዳት ዕቅድ የላትም... ስለሆነም ለደኅንነታችሁ ሲባል በአስቸኳይ ለቅቃችሁ መውጣት አለባችሁ" ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር የለቅቃችሁ ውጡ ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸው፤ ሃሬት ህሬክ፣ ጎቤይሪ፣ አል ሊላኪ፣ ሀዳት፣ ቦርጅ ኤል ባራጅነህ፣ ታህዊታት አል-ጋዲር፣ ሺያህ እና አል-ጃናህ የተባሉት አካባቢዎች ናቸው።

    እስራኤል ቤይሩት ውስጥ የምትፈጽመውን ጥቃት በከፍተኛ መጠን የጨመረችው አሜሪካ እና ኢራን የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስን የማካተቱ ጉዳይ አከራካሪ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

    ኢራን እና ስምምነቱን ያሸማገለችው ፓኪስታን ተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ቢገልጹም እስራኤል አቋሟ በተቃራኒው እንደሆነ አሳውቃለች።

    ኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ሊባኖስ ውስጥ የሚፈጸሙት ጥቃቶች የተኩስ አቁም ጥሰት እነደሆኑ ገልጸዋል።

    ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ተኩስ ካስወነጨፈ በኋላ በተከፈጠው ዘመቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

  6. የኢራን ፕሬዝዳንት “ጣቶቻችን አሁንም ቃታው ላይ ናቸው” ሲሉ አስጠነቀቁ

    እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት በአሁኑ ጊዜ ኢራን በተጠንቀቅ ላይ እንደሆነች ፕሬዝዳንቷ አስታወቁ።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እስራኤል ሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃትም "ግልጽ የተኩስ አቁም ጥሰት” ነው ብለዋል።

    የእስራኤል ጥቃቶች መቀጠላቸው ሊደረስ ለሚችል ስምምነት ቁርጠኝነት እንደሚጎድል የሚሳይ “አደገኛ ምልክት” ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ይህንን አስተያየት በኤክስ ገጻቸው ያሰፈሩት የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ ዒላማዎች እንደሆኑ በገለጻቸው የሊባኖስ ስፍራዎች ላይ ከ100 በላይ የአየር ጥቃቶችን በፈጸመ ማግሥት ነው።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያናሁ “አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ” ሄዝቦላህ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ በዛሬው ዕለት ተናግረዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን በኤክስ ልጥፋቸው የጥቃቶች መቀጠል ከአሜሪካ ጋር የሚደረገውን ድርድር ወደ “ትርጉም የለሽነት” እንደሚያወርደው ገልጸዋል። የኢራን ጣቶች “ቃታው ላይ ሆነው እንደሚቀጥሉም” ጽፈዋል።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ በበኩላቸው “የተኩስ አቁም ጥሰቶች ግልጽ ዋጋ” እንደሚያስከፍሉ እና “ጠንካራ ምላሽ” እንደሚያስከትሉ ተናግረዋል።

    ሊባኖስ “የማትነጠል የተኩስ አቁሙ አካል” መሆኗን ገለጹት አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ፤ “ለክህደት እና ማፈግፈግ የሚሆን ቦታ እንደሌለ” አሳስበዋል።

    “በአስቸኳይ እሳቱን አጥፉ” ሲሉም አክለዋል።

  7. ዩናይትድ ኪንግደም፤ እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመውን ጥቃት አወገዘች

    የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ አገራቸው የኢራን ጦርነትን ለማስቆም የተደረገውን የተኩስ አቁም እንደምትደግፍ እና እንዲዘልቅ እንደምትፈልግ ገልጸው፤ በሊባኖስ የሚታየውን የጥቃት መባባስ አወገዙ።

    የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦች እንቅስቃሴን ተመለከተ ዛሬ መግለጫ የሰጡት ሚኒስትሩ፤ የተኩስ አቁሙ ይዘልቃል ብለው ያስቡ እንደሆነ ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

    “የተኩስ አቁሙን በበጎን እንቀበለዋለን። እንዲዘልቅ እንፈልጋለን። እንዲጠናከር ለማድረግ የራሳችንን ድርሻ እንወጣለን” ብለዋል።

    መከላከያ ሚኒስትሩ አክለውም፤ “ሊባኖስ ውስጥ የሚታየውን [የጥቃት] መባባስ እናወግዛለን። የእስራኤል ሊባኖስ ግጭት በተኩስ አቁሙ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተት እንፈልጋለን፤ ምክንያቱም መላው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ወደ ትልቅ መረጋጋት ተመልሶ መመልከት እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሄሊ በመግለጫው ዩናይትድ ኪንግደም የኢራን ጦርነትን በተመለከተ የያዘችው አቋም እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዩናይትድ ኪንግደም ጦርን ወደ መካለኛው ምሥራቅ ማሰማራት “የብሪታኒያን ብሔራዊ ጥቅም” እንዳልሆነ አስረድተዋል።

    “በመካከለኛው ምሥራቅ እንደሆነው፤ ቀውስ በከፍተኛ ሁከት እና አደገኛ በሆነ ሁኔታ በሚፈነዳበት ወቅት፤ ሰዎች ለምን የዩኬ ወታደራዊ ይዞታዎች ችግሩን ለመፍታት አልተሰማሩም የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን እረዳለሁ” ብለዋል።

    “ነገር ግን ይሄ የብሪታኒያ ብሔራዊ ጥቅም አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ግዙፎቹ ስጋቶች ብዙውን ጊዜ የማይታዩ እና ድምጽ አልባ መሆናቸውን” የጠቀሱት መከላከያ ሚኒስትሩ፤ የመከላከያ ፍላጎቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው የዩናይትድ ኪንግደም "ሀብቶቻችንን የተሻለ ውጤት ባላቸው [ጉዳዮች ላይ] ማሰማራት” አለብን ብለዋል።

  8. ሆርሙዝ ተከፍቶ የሚቆየው አሜሪካ ጥቃቶችን እስካቆመች ድረስ መሆኑን ኢራን አስታወቀች

    አሜሪካ ስታካሂድ የቆየውን “የወረራ ጥቃት” እስካቆመች ድረስ ለሳምንታት ተዘግቶ የቆየው የሆርሙዝ ወሽመጥ መልሶ እንደሚከፈት ኢራን አስታወቀች።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳኢድ ኻቲብዛዴህ እንደተናገሩት አገራቸው መርከቦች በወሳኙን የባሕር መተላለፊያ በኩል እንዲተላፉ “ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን” እንደምታደርግ ገልጸዋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጦርነት እስከከፈተችበት ጊዜ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ለሺዎች ዓመታት ከፍት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፤ አሁንም መተላለፊያው ክፍት የሚሆነው እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጦርነት በመጥቀስ “አሜሪካ በተግባር ወረራው እንዲሆም” ስታደርግ ብቻ ነው ብለዋል።

    ባለሥልጣኑ ጨምረውም አገራቸው “ለዓለም አቀፍ ሕጎች እና ደንቦች እንድምትገዛ” ነገር ግን ሆርሙዝ የዓለም አቀፍ ውሃ አካል ባለመሆኑ፣ በወሽመጡ በኩል ያለ ችግር ለማለፍ “የኢራን እና የኦማን መልካም ፈቃድ ያስፋልጋል” ብለዋል።

    በሰላም በሆርሙዝ በኩል ማለፍ ማለትን በተመለከተ ኢራን የውሃ አካሉ “ሰላማዊ” እንዲሆን እንደምትፈልግ ነገር ግን ይህ የሚሆነው ሌላውም አካል ተመሳሳዩን ሲያደርግ እንደሆነ እና አገራቸው ባሕረ ሰላጤውን “የጦር መርከቦች”ያላግባብ እንዲጠቀሙበት አትፍቅድም ብለዋል።

  9. ስታርመር ለባሕረ ሰላጤው አገራት ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደ መደራደሪያ መያዝ የለባትም አሉ

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የገቡት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ኢራን “የሆርሙዝ ወሽመጥን መደራደሪያ” ማድረግ የለባትም አሉ።

    ስተርመር ከባሕረ ሰላጤው አገራት የመከላከያ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ንግግር አገራቸው በጦርነቱ ላይ ቋሚ አቋም ማንፀባረቋን ያነሱ ሲሆን፤ ግጭቱ እንዲረግብ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቅርበዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ አገራት በአንድ ላይ በመስራት መፍትሔ መፈለግ ይገባቸዋል ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ተኩስ የማቆም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ያለፈቃድ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማለፍ የሚፈልግ መርከብ ዒላማ እንደሚደረግ እና ጉዞው እንደሚዘገይ አስታውቋል።

    የዋይት ሐውስ ፕሬስ ኃላፊ ካሮሊን ሌቬት ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል የሚሉ ሪፖርቶች ሐሰተኛ ናቸው ብለዋል።

  10. ኔታንያሁ እስራኤል “አስፈላጊ በሆነ ጊዜ” ሄዝቦላህ ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ተናገሩ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል “አስፈላጊ በሆነ ጊዜ” ሄዝቦላህ ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ተናገሩ።

    እስራኤል ከዚህ ቀደም አሜሪካ እና ኢራን የደረሱት የተኩስ አቁም ስምመምነት ሊባኖስን እንደማያካትት ተናግረው ነው።

    ኢራን ግን እስራኤል ሊባኖስ ላይ የፈጸመችው ጥቃት የስምምነቱ “ከባድ ጥሰት” ነው ብላለች።

    ኔታንያሁ “መልዕክታችን ግልጽ ነው። ማንም ከእስራኤል ሰላማዊ ዜጎቻችን በተቃራኒ የቆመ ዒላማ ይሆናል” ብለዋል።

    “በሰሜን የሚገኙ ነዋሪዎችን ሙሉ ደኅንነት እስክናረጋግጥ ድረስ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ሄዝቦላህን እንደበድባለን።”

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የእስራኤል መከላከያ የሄዝቦላህ ዋና ፀሐፊ ናይም ቃሰም የወንድም ልጅ የሆነውን አሊ ዩሱፍ ሃርሺን መገደሉን ካስታወቀ በኋላ ነው።

  11. በሊባኖስ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ200 በላይ ሰዎች ተገደሉ

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት በመላ አገሪቱ የተፈጸመ የእስራኤል ጥቃትን ተከትሎ 203 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ1000 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ገለጸ።

    ኢራን በበኩሏ በሊባኖስ ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ድብደባ ከአሜሪካ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የተፈጸመ “ከባድ ጥሰት” ነው ስትል ተናግራለች።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር በሊባኖስ ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር ረቡዕ ምሽት በአደራዳሪዋ ፓኪስታን በኩል ንግግሮች እንደነበሩ ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ጊዜየዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸወን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ሊባኖስን አያካትትም" በማለት መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተዋል።

    ይህንንም ተከትሎ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "በተቻለ መጠን ጥቃቱን እንዲየስቆምላቸው" ተማጽኖ አቅርበዋል።

    ናዋፍ ሳላም የእስራኤል ጦር ጥቃቶች ለዓለም አቀፍ ሕግ "ፍፁም ቸልተኝነት" አሳይተዋል በማለት "ሁሉም የሊባኖስ ወዳጆች እነዚህን ጥቃቶች በሁሉም መንገዶች ለማስቆም እንዲረዱን ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

  12. እስራኤል በሊባኖስ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት እነማን አወገዙ?

    የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዬቬት ኩፐር እስራኤል በሊባኖስ ላይ የፈጸመቸውን ጥቃት “ሙሉ በሙሉ ስህተት” ሲሉ ገልጸውታል። ሌሎች የአውሮፓ አገራትም የአየር ድብደባውን አውግዘዋል።

    የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዢን ኖኤል ባሮት “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ያወገዙት ሲሆን፣ ኢራንም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመታጠቅ የምታደርገውን ጥረት እንዲሁም ለሄዝቦላህ እና ለሐማስ የምትሰጠውን ድጋፍ መተው አለባት ብለዋል። የእስራኤል ጥቃት “በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ዝቅ የሚያደርግ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አክለዋል።

    የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በበኩላቸው “መመለሻ የሌለው ነጥብ ላይ ደርሰናል፤ አሁን ግን በቁርጠኝነት ሊተገበር የሚገባው የሰላም ተስፋ እየጠበበ ነው” ብለዋል።

    ስፔን በቴህራን የሚገኘው ኤምባሲዋን ዳግም ልትከፍት መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ሆዜ ማኑኤል አልባሬሰ “የተኩስ አቁሙን በግልጽ ጥሳለች” ሲሉ እስራኤልን ወንጅለዋል። አክለውም “የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው” ሲሉ ኮንነውታል።

  13. የኢራን ሚኒስትር እስራኤል በሊባኖስ የፈጸመችው ድብደባ የተኩስ አቁሙ “ከባድ ጥሰት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይድ ኻቲብዛድ ከቢቢሲ ቱደይ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ እስራኤል ረቡዕ ዕለት በሊባኖስ የፈጸመችው ድብደባ የተኩስ አቁሙ “ከባድ ጥሰት ነው” አሉ።

    ሚኒስትሩ አሜሪካ ኢራን ላይ ጦርነት ከመክፈቷ በፊት ለዘመናት ክፍት ሆኖ ለዘለቀው የሆርሙዝ ወሽመጥ ቴህራን “ደኅንነቱ የጠበቀ እንቅስቃሴ” እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

    ሆኖም ወሽመጡ ዳግም የሚከፈተው “አሜሪካ በትክክል ከጥቃቷ ስትታቀብ” እንደሆነ እስራኤል ሊባኖስ ላይ የፈፀመችውን ጥቃት በማመልከት ገልፀዋል።

    ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢራን “ለዓለም አቀፍ መርኅ እና ሕግ ተገዢ” እንደምትሆን ጠቅሰው፤ ሆኖም ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዓለም አቀፍ ውሃ እንዳልሆነ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ “በኢራን እና ኦማን መልካም ፈቃድ” ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።

    ሚኒስትሩ ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ ማለት ኢራን በእያንዳንዱ መርከብ ክፍያ መጣል ወይም ለመደብደብ ማስፈራራት ማለት ነው ተብለው ተጠይቀዋል።

    ሚኒስትሩ በምላሻቸው ኢራን ወሽመጡ “ሰላማዊ” እንዲሆን እንደምትሻ ጠቁመው፤ ሆኖም ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ ሁለት ወገን እንደሆነ እና ሰርጡ “ለጦር መርከቦች ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዲውል” አንፈቅድም ብለዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸው ይፋ ቢደረግም እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት መፈጸም በመቀጠሏ ትናንት ለዋይት ሐውስ ጠቅለል ያለ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    “በአንድ ግዜ ኬክ ሊኖርህም ልትበላው አትችልም” በማለት የተኩስ አቁም ላይ ተደርሶ ሊባኖስን መደብደብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

    አክለውም በስምምነቱ ላይ ሊባኖስ መጠቀሷን በማንሳት የአሜሪካ አጋር የሆችው እስራኤል ግን “ጭፍጨፋ” መፈጸሟን በመጥቀስ ወንጅለዋል።

    አሜሪካ ጦርነት ወይም ሰላም እንደምትፈልግ “መምረጥ አለባት” ያሉት ሚኒስትሩ ሁለቱም በተመሳሳይ ወቅት ሊኖራት አይችልም ብለዋል።

    እስራኤል በሊባኖስ የምታካሄደውን ድብደባ ከቀጠለች ከስምምነቱ ይወጡ እንደሆን የተጠየቁት ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “በአጠቃላይ መካከለኛው ምሥራቅ ደህንት ላይ ነው ትኩረታችን” ሲሉ መልሰዋል።

    ኢራን ሄዝቦላህ ሮኬት መተኮሱን እንዲያቆም ታደርግ እንደሆን ሲጠየቁ ስምምነቱ ሊባኖስን ያካተተ ነው ኢራን እና አጋሮቿ “የተኩስ አቁሙን ለመቀበል” ፈቃደኞች ናቸው ብለዋል።

  14. የአሜሪካ-ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ‘አጠራጣሪ’ ቢሆንም የኢራን ተደራዳሪዎች ወደ ፓኪስታን አቀኑ

    የኢራን ተደራዳሪዎች ልዑክ ከአሜሪካ ጋር ጦርነቱን ለማቆም ወደ ፓኪስታን ማምራቱን በፓኪስታን የኢራን አምባሳደር አረጋግጠዋል።

    ልዑኩ ቅዳሜ ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዴ ቫንስ ጋር ይገናኛል።

    በፓኪስታን የኢራን አምባሳደር ሬዛ አሚሪ ሞግሃደም በኤክስ ገፃቸው ድርድሩ “ኢራን ባቀረበችው ባለ 10 ነጥብ ምክረ ሐሳብ” ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

    ድርድሩ በየትኛው አገር ባቀረበው ነጥብ ላይ ነው የሚለው አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል።

    አምባሳደሩ ንግግሩ የእስራኤል አገዛዝ የዲፕሎማቲክ ጥረቶችን ለማሰናከል በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ኢራናውያን ጥርጣሬ ባደረባቸው ሰዓት እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል።

  15. ትራምፕ ኢራን “ትክክለኛውን ስምምነት” እስክታከብር ድረስ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?

    አሜሪካ እና ኢራን ያወጁት ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው።

    አለመግባባቱ የመጣው ባለ አስር ነጥብ ዕቅድ በሚል እየተዘዋወረ ካለው ሰነድ ጋር ተያይዞ ነው።

    ትራምፕ “በዩናይትድ ስቴትስ ተቀባይነት ያለው እና አንድ ትርጉም ያለው” ስምምነት ብቻ መኖሩን ተናግረዋል።

    ይህንንም ትክክለኛ ስምምነት በሚል በመጥራት “የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እንደማይኖር እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥ ይከፈታል፤ ደህንነቱም የይጠባቃል” የሚል መሆኑን ጠቅሰዋል።

    በኢራን ወገን ግን የተለያዩ የስምምነት ሰነዶች ይገኛሉ።

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በኢራን፣ ኢራቅ፣ የመን እና ሊባኖስ የሚካሄደውንው ውግያ የሚያስቆም እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መክፈት እና አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳላት የሚግለጽ ሰነድን አቅርቧል።

    በኋላ ላይ ደግሞ የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ይፋ ያደረገው ባለ አስር ነጥብ ዕቅድ ዩራኒየም ማበልጸግ እና ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደምትቆጣጠር የሚሉ ሃሳቦችን ይዞ መጥቷል።

    በደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ ውስጥ በእንግሊዘኛ የቀረበው መግለጫ ላይ ዩራኒየም ማበልጸግ የሚለው ሃሳብ በኋለ ላይ እነዲወጣ ተደርጓል።

    ትራምፕ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ በተኩስ አቁሙ ሊባኖስ ስለመካተቷ ያሉት ነገር የለም። ነገር ገን በተኩስ አቁሙ ዙሪያ ላለመግባባት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ ግን የሊባኖስ አለመካተት ነው።

  16. የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥርጣሬ ማሳደሩን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    አሜሪካ ኢራንን ለሁለት ሳምንት ላለማጥቃት ከተስማማች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ሐሙስ ጠዋት ግን ዳግም ጨምሯል።

    በዓለም አቀፍ ገበያ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በበርሚል 2.2 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 96.70 ዶላር ገብቷል። በአሜሪካ ገበያ ደግሞ ከዚህም ከፍ በማለት በ2.8 በመቶ በመጨመር 96.90 ዶላር ገብቷል።

    እስራኤል በሊባኖስ ላይ ተከታታይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ቀዳዳዎች እንዲታዩ አድርጓል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን ካበሰሩ በኋላ ረቡዕ ዕለት ብሬንት ነዳጅ በ15 በመቶ በመቀነስ አንድ በርሜል 92 ዶላር ገብቶ ነበር። በኋላ ላይ ግን የነዳጅ ዋጋ ከዚህ ትንሽ ከፍ ብሏል።

    የነዳጅ ዋጋ ጦርነቱ የካቲት 21/ 2018 ዓ.ም. ከመጀመሩ በፊት ከነበረበት ዋጋ በጣም ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

  17. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር የአሜሪካ-ኢራንን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማፅናት በርካታ ሥራዎች ገና ይቀራሉ አሉ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ለሁለት ሳምንታት የታወጀውን የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማፅናት እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት “በርካታ ሥራዎች መሰራት” አለባቸው ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረቡዕ ዕለት ስምምነቱን ለመደገፍ እና ለማፅናት የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማድረግ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጉብኝት አካል በሆነው ጉዟቸው ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል።

    ሰር ኪር ስታርመር ስምምነቱን ተከትሎ “እፎይታ” ስሜት እንዳለ ጠቅሰው ጊዜው ገና መሆኑን ግን ተናግረዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው የኢራን መገናኛ ብዙኃን እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ማለፍ ማቆማቸውን ከዘገቡ በኋላ ነው።

    በተኩስ አቁም ድርድሩ አሸማጋይ ሆና ያገለገለችው ፓኪስታን እና ኢራን ስምምነቱ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ቢናገሩም፤ እስራኤል ግን ስምምነቱ ሊባኖስን አይጨምርም ብላለች።

    ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በሆርሙዝ ሰርጥ ማሳለፍ የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ቁልፍ አካል ነው።

    የዩናይትድ ኪንገደም እና የሳዑዲ ወታደሮችን ያነጋገሩት ስታርመር “እንደምታውቁት በርካታ መሰራት ያለባቸው ሥታዎች አሉ፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ቋሚ እንዲሆን እና ሁላችንም ማየት የምንፈልገውን ሰላም ለማምጣት በርካታ ሥራዎች መሰራት አለባቸው” ብለዋል።

    ስታርመር ወደ ጂዳ ተጉዘው የሳዑዲውን አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማንን አግኝተዋል።

    ይህን ንግግር ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ሁለቱ መሪዎች የሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የዩኬ በአጋሮች ዘንድ ስምምነት እንዲኖር በምታደርገው ጥረት ላይ እንደተነጋገሩ ገልፀዋል።

  18. ኢራን የተኩስ አቁሙ ሦስት አንቀጾች “በግልጽ እና በይፋ ተጥሰዋል” አለች

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ትናንት ምሽት በኤክስ ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ ኢራን ካቀረበችው ባለ 10 ነጥብ ምክረ ሀሳብ መካከል ሦስት አንቀጾች “በግልጽ እና በይፋ ተጥሰዋል” አሉ።

    አፈ ጉባዔው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የሁለትዮሽ የተኩስ አቁም ስምምነት ወይም ድርድር “ምክንያታዊ አይሆንም” ብለዋል።

    ጋሊባፍ ሊባኖስ በዚህ ምክረ ሀሳብ ውስጥ ተካትታ እንደነበር የጠቀሱ ሲሆን ዋይት ሐውስ ግን ይህንን አስቀድሞ ውድቅ አድርጓል።

    በተጨማሪም አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን ወደ ኢራን ደቡባዊ ፋርስ ግዛት መግባቱን አፈ ጉባዔው ጠቅሰዋል።

    የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት እንዲህ አይነት ክስተት ስለመፈጠሩ "እንደማያውቅ" ለቢቢሲ ተናግሯል።

    አፈ ጉባዔው በሦስተኛው አንቀጽ ላይ ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ መብት የሚል ተካትቷል ያሉ ሲሆን ይህም የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በፋርስ ቋንቋ በሰጠው እና በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በተነበበው መግለጫ ውስጥ ተካትቷል።

    የአሜሪካ እና የእስራኤል በኢራን ጦርነት የተጀመረው የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ሲሆን ይህም በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የተደረገው ድርድር ያለውጤት ከተጠናቀቀ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

    አንዳንድ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች የትራምፕ አስተዳደር አፈ ጉባኤ ጋሊባፍን የወደፊቷ ኢራን መሪ ለማድረግ እያጤነ መሆኑን ጠቁመዋል።

  19. ትራምፕ ኢራን “ለትክክለኛው ስምምነት” ሙሉ በሙሉ እስክትገዛ ድረስ ጦሩ በተጠንቀቅ እንዲቆይ አዘዙ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን “ትክክለኛውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ የማታከበር ከሆነ ማንም ካየው በላይ ጠንካራ የሆነ ጥቃት” እንደሚፈጸም በመግለጽ አስጠነቀቁ።

    ፕሬዚዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ላይ ባጋሩት ጽሑፍ “ተኩስ የሚጀመረው ግዙፍ እና የተሻለ እንዲሁም ማንም ካየው በላይ ጠንካራ ሆኖ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    አክለውም ሁሉም የአሜሪካ ጦር መርከቦች፣ አውሮፕላኖች እና ወታደሮች እንዲሁም ተጨማሪ ጦር መሣሪያዎች ዝግጁ እንዲሆኑ አዝዘዋል።

    ረቡዕ ዕለት አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቢቆሙም እስራኤል ግን በሊባኖስ ላይ ጠንካራ እና ገዙፍ ድብደባዎችን መፈጸሟን አስታውቃለች።

    በዚህም የተነሳ የሄዝቦላህ አዛዠን ጨምሮ ከ180 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በአስቸኳይ ካልቆመ “ጸጸት የሚያስከትል ምላሽ” እንደሚሰጥ ዝቷለ።

    የትራምፕ ማስጠንቀቂያ የተሰማው የአብዮታዊ ዘቡ ማስጠንቀቂያን ተከትሎ ነው።

    “ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ደረጃ አቅሙ የተዳከመውን ጠላት ለመምታት እና ለማጥፋት ተገቢ እና አስፈላጊ የሆነ ማንኛውም ነገር ትክክለኛው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ በኢራን እና በዙሪያው አካባቢ ይቆያል” ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ።

    ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው “ትክክለኛ ስምምነት” የማይከበር ከሆነ ግን “ሊሆን የሚችል አይመስለኝም” በማለት “ተኩስ የሚጀመረው ግዙፍ እና የተሻለ ሆኖ እንዲሁም ማንም አይቶት ከሚያውቀው በላይ ጠንካራ ሆኖ ነው” ብለዋል።

    ቀደም ብሎ “ምንም እንኳ ሐሰተኛ መረጃዎች ስለ አገሪቱ ቢኖሩም” ምንም ዓይነት የኒውከክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይኖር እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ደህንነቱ ተጠብቆ እንደሚከፈት ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር” ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ አንዳለ “ታላቁ ጦራችን መሣሪያውን እየጫነ እና እያረፈ ቀጣዩን ድል ይጠብቃል፤ አሜሪካ ተመልሳለች” ብለዋል።

  20. የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሊባኖስ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ከቀጠለ “ጸጸት የሚያስከትል ምላሽ” እሰጣለሁ ሲል አስጠነቀቀ

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በአስቸኳይ ካልቆመ “ጸጸት የሚያስከትል ምላሽ” እንደሚሰጥ መዛቱን የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ዘገበ።

    አብዮታዊ ዘቡ በቴሌግራም ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት “ቃሏን ላጠፈችው ዩናይትድ ስቴትስ እና ጽዮናዊት አጋሯ ከባድ ማስጠንቀቂያ አለን” ብሏል።

    “በውዷ ሊባኖስ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁኑኑ ካልቆመ የገባነውን ቃል በመፈጸም ጸጸት የሚያስከትል ጥቃት በቀጣናው ረባሽ ላይ እንሰነዝራለን” ሲል ዝቷል።

    የአገሪቱ ብሔራዊ የዜና ወኪል ኢርና የአብዮታዊ ዘቡ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ “በኩሩው ሄዝቦላህ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ኢራን ላይ እንደተፈጸመ ነው። ጦሩ ከባድ ምላሽ በጨካኙ ወንጀለኛ አገዛዝ [እስራኤል] ላይ ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው” ማለታቸውን ዘግቧል።