በሕዳሴ ግድብ ታላቅ አስተዋጽኦ ከነበራቸው መካከል የተናገሩት በጥቂቱ






ግንባታው 14 ዓመታትን የፈጀው እንዲሁም አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተበጀተለት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማክሰኞ፣ ጳጉሜ 4/ 2017 ዓ.ም ተመርቋል። የናይልን 55.ሚሊዮን ኪዩቢክ ውሃን የምትጠቀመውና ለዓመታት ኢትዮጵዮያ ግድብ እንዳትገነባ ስትከላከል የነበረችው ግብፅ የግድቡን ግንባታ ከጅምሩ ተቃውማዋለች። በሕዳሴ ግድብ የተካሄዱ አምስት የውሃ ሙሌቶችም ከግብፅ በኩል ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎችን ያስከተሉ ናቸው።







የፎቶው ባለመብት, SM
ከ15 ዓመታት በኋላ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ሆነ ያሉት የጣሊያኑ ሳሊኒ (ዊ ቢውልድ) ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ፤ ግድቡን ለመገንባት የነበረውን ውጣ ውረድ እና የተከፈለውን ዋጋ ገልፀዋል።
“ለእኔ እና ለአገሪቱ ሕልማችን እውን ሆነ። ዛሬ ከዚህ በላይ እንዴት መኩራት ይቻላል?” ያሉት፤ ይህን ስኬት እውን ላደረጉ የግንባታውን ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።
የህዳሴግድብ ፕሮጀክትን “በዓለም በጣም ደኅንነት የነበረው ፕሮጄክት ነው” ያሉት ሳሊኒ፤ ሆኖም ግን ታላቅ ስኬቶች ዋጋ እንደሚከፈልባቸው ሁሉ በግድቡ ግንባታ ሂደት የሰው ዋጋ መከፈሉን አንስተዋል።
ፔትሮሳሊኒ ባለፉት 15 ዓመታት፤ 33 ሠራተኞች በመንገድ አደጋ እና በሌሎችም ሁኔታዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውቀዋል።
የግዱቡ ግንባታ ሂደት ጋር በተያያዘ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ለዚህስኬት ሕይወታቸውን ለሰጡ ሠራተኞች ያላቸውን ከበሬታ የገለፁት ሳሊኒ ለቤተሰቦቻቸውም ትውስታቸው አይጠፋም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞች ተቀይረው መስራታቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ 250 ሺህ ሰዓት ሠራተኞችን ስለ ደኅንነት ለማሰልጠን እንደዋለ ጠቅሰዋል።
25 ሺህ ወጣቶች በሥራ ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደተሰጣቸው ጠቅሰው፤ ይህም ለአገሪቱ ወደፊት መሰረታዊ አበርክቶ ይኖረዋል ሲሉ በሙሉ ልብ ተናግረዋል።
የግድቡን መሠረት ካሳረፉት እና በግድቡ ዙሪያ ሥማቸው በጉልህ ከሚነሳው ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በቅርበት መስራታቸውን የተናገሩት ሳሊኒ፤ ከመለስ ዜናዊ ጋር ያደረጉትን ንግግርም ጠቅሰዋል።
“‘ለዚህ አገር ሕልም አለኝ፤ የተትረፈረፈ የኃይል ሉዓላዊነት። ዓባይ ላይ ፕሮጀክት ልትነድፍልኝ ትችላለህ? ታላቅ ፕሮጀክት፤ ቢያንስ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ እፈልግላሁ’ አለኝ። ፤በፍጥነት ስራው[አለኝ]’ ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ሕይወቱ አለፈ” በማለት የግድቡን ውጥን እንዴት እንደተጠነሰሰ ገልፀዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር በግድብ ግንባታ እስከ ቤተሰባቸው ታሪካዊ ትስስር እንዳላቸው በስሜት የገለፁት ፔትሮ ሳሊኒ፤ ኢትዮጵያ በምንያህል ፈተና ውስጥ ተከባ ሕዳሴን እንደገነባችም ዘርዝረዋል።
“አገሪቱ ይህን ግድብ እንድትገነባ ማንም አልፈለገም። ማንም ገንዘብ ለማቅረብ አልፈለገም። ብዙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች፤ ብዙ ችግሮች [ነበሩ]፤ ቀላል መፍትሔ አልነበረም። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ችግር ፈሪ አይደሉም። አይበገሬ ናቸው። መገዳደር ወይም ጠላት ሲገጥማቸው ጥረታቸውን በእጥፍ ይጨምራሉ፤ ማግኘት ያለባቸውን ያገኛሉ” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Fana
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ በእንግድነት የታደሙ በርካታ አገራት መሪዎች የመልካም መግለጫ መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል።
የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ “ታሪካዊ ስኬት” ላሉት የሕዳሴ ግድብ ምርቃት ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ በበኩላቸው በግድቡ ጉብኝት ወቅት የታዘብኩት የዓድዋ ድል ተምሳሌት በምህንድስና ጥበብ ዳግም ተገልጦ ነው ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት በቅርቡ አገራቸው እንደምትፈጽም ተናግረዋል።
ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምህንድስና ምኞት ብቻ አይደለም ያሉት ሩቶ፤ አፍሪካ እጣ ፈንታዋን እንደምትወስን ደማቅ ማረጋገጫ ነው ሲሉ አብስረዋል።
“ዛሬ ይህን ታላቅ ድል ስናከብር ዘላቂነት ላለው የወዳጅነትን ትስስርን፣ ትብብር እና የጋራ ራዕይ እናረጋግጣለን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሕዳሴ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን እና ሰፊው የናይል ተፋሰስ አገራት አያያዥ አድርገው ገልፀዋል።
አገራቸው ኬንያ ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
“. . .ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም። የፓን አፍሪካን መገለጫም እንጂ። አቅም እና ምኞት በአፍሪካዊያን የተመራ መሠረተ ልማት፣ ከአፍሪካ ኅብረት ርዕይ የሆነው አህጉሪቱ በኃይል ማስተሳሰር የተሳሰረ ነው” ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በበኩላቸው ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጠናውን አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረው፣ በቅርቡ አገራቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር እንደምትፈፅም ጠቁመዋል።
ይህም በደቡብ ሱዳን ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ከተሞች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንደሚፈታ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ግድቡ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ አዲስ ምዕራፍን የሚከፍት ነው ብሲኦኡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ አስተላልፈዋል።
የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ በበኩላቸው በግድቡ ጉብኝት ወቅት የታዘብኩት የዓድዋ ድል ተምሳሌት በምህንድስና ጥበብ ዳግም ተገልጦ ነው ሲሉ ታላቁ ሕዳሴ ግንባታን መጠናቀቅን አሞካሽተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ፥ የሕዳሴ ግድብ እውን መሆን ውኃን ገድቦ ኃይል ከማመንጨት እና ከአስደናቂ የምህንድስና ውጤት በላይ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ግድቡ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊእና የደኅንነት ዘርፎችም ከሚኖረው ጥቅም በላይ የሚያኮራው ኢትዮጵያዊያን ግድቡን እውን ለማድረግ የተጓዙበት መንገድ መሆኑንም ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር በ30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነቡ ስድስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ዝርዝር ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ ይውላል ያሉት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ በቅርቡ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ኢትዮጵያ የሕዳሴን ግድብ የሚተካከል ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚውል የኒውክሌር ፕላንት መገንባት በቅርቡ ትጀምራለች” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኒውክሌር ልማቱ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም በቅርቡ ከአቶሚክ ኃይል ኤጄንሲ ኃላፊ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው መነጋገራቸው ይታወሳል።
ከዚህ ባሻገርም የነዳጅ ማጣሪያ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሥራ እንደሚጀመር አብስረዋል።
የጋዝ ፋብሪካ፣ የኤርፖርት ማስፋፊያ እና የቤቶች ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቂት ዓመታት ይጀመራሉ ካሏቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ተካተዋል።
“የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያሰምሩ ሜጋ ሜጋ ፕሮጄክቶች፤ ያልገለፅኳቸውም ጭምር ከፊታችን ስላሉ ከዚህ ሰዓት በኋላ ኢትዮጵያውያን በሠራነው ገድል ሳይሆን ከፊታችን ለሚጠብቀን ከባድ ሥራ ታጥቀን እንድንነሳ. . . “ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
“ለዘመናት ስንመኘው የነበረው ነዳጅ የማውጣት ፍላጎታችንን፤ ህልማችንን እውን የሚያደርገው [የነዳጅ] ማጣሪያ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሥራ ይጀምራል” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ የማንሰራራት የመጀመሪያው ቀን” ሲሉ ሁነቱን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት “በትንሹ 1.5 ሚሊዮን ቤቶች ለኢትዮጵያዊያን ይገነባሉ” ሲሉም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዳሴው ግድብ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር ግድቡ ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ሆኖ የሚቆይ ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን “ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ምድር እስክትሰበሰብ ታሪክ ሆኖ የሚኖር ታላቅ ገድል ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዳሴ ግድብ ምርቃት ወቅት ባደረጉት ንግግር በተለያየ አመለካከት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ግድቡን መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "የእኔ ምኞት ኢትዮጵያዊ ይህንን ገድል፣ ይህንን ታሪክ፣ ይህንን ሥራ ሳያይ እንዳያልፍ ብቻ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ሕዳሴን በንግግር በምሥል መግለጥ አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መጥቶ ያየ ሰው ብቻ ልኩን መገንዘብ እንደሚችል ተናግረው ኢትዮጵያውያን ይህ ትውልድ የሠራውን ገድል እየመጡ እንዲጎበኙ "ምኞቴና ፍላጎቴ ነው" በማለት ጥሪ አቅርዋል።
“ለተቀረው የጥቁር ሕዝብ ደግሞ ግብዣዬ ነው" ሲሉም አክለዋል።
"ጥቁሮች እንደምንችል፣ ጥቁሮች እንደምናሳካ በጥቁር ዘር ታሪክ የመጀመሪያው ሕዳሴ ነው።"
ሕዳሴን "የትናንት ቁጭት ማሰሪያ፣ የመጪው ንጋት ማብሰሪያ" ሲሉ የጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሁኑ ወቅት 74 ትሪሊየን ውሃ መያዝ መቻሉን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ ሲመረቅ ለተገኙ አገራት መሪዎች ደግሞ "የኢትዮጵያ ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ከሃብቷ ከልምዷ የምታቋድሳችሁ እንደሚሆን አረጋግጥላችኋለሁ" ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ለታችኛው ተፋሰስ አገራት በማለትም ኢትዮጵያ ሕዳሴን የሠራችው ለመበልፀግ፣ አካባቢውን በብርሃን ለመሙላት፣ የጥቁር ሕዝብ ታሪክ ለመቀየር እንጂ በፍፁም ወንድሞቿን ለመጉዳት አይደለም በማለት የውሃው ፍሰት እንደማይቀንስ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ለግብፅ እና ሰለሱዳንም የአብረን እንሥራ፣ በጋራ እንቁም ጥሪ አቅርበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Fana
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሕዳሴ ግድብ ለረዥም ዓመት ላገለገሉ የተለያዩ ባለሙያዎች የክብር ኒሻን ሸለሙ።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በግድቡ ግንባታን በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አበርክቶ ያሳረፉ ኃላፊዎች የአገሪቱን የክብር ኒሻን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተበርክቶላቸዋል።
ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ኢንጅነር ኤፍሬም ወ/ኪዳን የግድቡ ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ኢንጅነር ከማል አህመድ የግድቡ ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ በላቸው ካሳ የግድቡ የፕሮጀክት ሳይት አስተባባሪ ከተሸለሙት መካከል ናቸው።
ይሁን እንጂ ግድቡን ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ዓመታት በሥራ አስኪያጅነት የመሩት እና በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በአነጋጋሪ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፎ የተገኘው ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሽልማት አልተበረከተላቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ኸልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኢንቫይሮመንት ኮርዲኔተር ሆነው የሠሩት ምንተስኖት "በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች የሞቱበት መንገድ አለ" ይላሉ።
"ከሥራ ጋር በተገናኘ በአደጋ የሚሞቱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። የግድቡን ኅልውና በማስጠበቅ፣ ከተለያዩ ቦታዎች ላይ ቁሳቁሶችን በማመላለስ፣ ጥቃት ሲደርስ ስለነበር በዚያ ሰዓት የተሰዉ ወገኖችም፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትም ሊኖሩ ይችላሉ" ብለዋል።
ነገር ግን በትክክል መናገር የሚችሉት ከግድቡ ግንባታ ሥራ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን በተመለከተ እንደሆነ አስረድተዋል። "ከዚህ ጋር በተያያዘ የነበረው ሞት በጣም ጥቂት ነው። 15 ሺህ ከሚለው አንጻር ጋር ሲታይ በጣም ጥቂት ነው የነበረው" ብለዋል።
"እኛ ሳሊኒ ጋር የነበረው ከሥራ ጋር የተያያዘ የሞተ ሰው ከ100 የሚያልፍ አይመስለኝም። 100ም የሚደርስ አይመስለኝም" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Fana
የደም፣ የላብ እና የውሃ ጠብታ ምልክት ሆኖ የተሰራው የጠብታ ሐውልት ተመረቀ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገኛ የተሰራው ይህ የጠብታ ሐውልት በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና በባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ነው የተመረቀው።
ይህ ሐውልት በግንባታ የተሳተፉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያሳይ ነው ተብሎ።
በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የሕዳሴ ግድብ በ2003 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ይህ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ 233 ቢሊየን ብር ለግንባታ እንደወጣበት ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የተናጠል እርምጃ ወስዳ የግድቡን ሙሌት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ ይህም ሁልጊዜም በታችኛው ተፋሰስ አገራት ዘንድ ስጋትን ሲያጭር ቆይቷል።
የሕዳሴ ግድብ 13 ተርባይኖች የሚኖሩት ሲሆን አጠቃላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሙ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት እንደሚደርስ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, EBC
ታላቁ የሕዳሴ ግደብ ዛሬ ማለዳ የጎረቤት አገራት መሪዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይም የተለያዩ አገራት መሪዎች፣ የክልል ባለሥልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በምረቃው ሥነ ስርዓት ላይ ከተገኙ የአፍሪካ መሪዎች መካከል የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡማር ጌሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ይገኙበታል።
እንዲሁም የኢስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒ፣ የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር አሞር ሞትሊ እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ተገኝተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህ ግድብ በብሔር ግጭት በምትናጠው አገር ውስጥ ሕዝቧን በአንድ መንፈስ በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሞሰስ ክሪስፐስ ኦኬሎ "ኢትዮጵያውያን እንጀራን እንዴት መበላት አንዳለበት ላይስማሙ ይችላሉ፤ በግድቡ ላይ ግን ይስማማሉ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። የሚመለከቱትም በወንዝ መሀል እንደቆመ የኮንክሪት ክምር ሳይሆን ለስኬታቸው እንደቆመ ሐውልት ነው። ግንባታው በ2003 ዓ.ም. ሲጀመር ግድቡን በገንዘብ ለመደገፍ በርካቶች ቃል ገብተዋል።"







የፎቶው ባለመብት, PM Office
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር አለመግባበት ውስጥ ቆይታለች።
ግብፅ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ላለፉት አስራ አራት ዓመታት በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
በ2003 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው ይህ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ 233 ቢሊየን ብር ለግንባታ እንደወጣበት ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የተናጠል እርምጃ ወስዳ የግድቡን ሙሌት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ ይህም ሁልጊዜም በታችኛው ተፋሰስ አገራት ዘንድ ስጋትን ሲያጭር ቆይቷል።

ከጉባ በረሃ ጠፍተው አያውቁም።
ባልደረቦቻቸው፣ የሚያውቋቸው፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው ስለ እርሳቸው ሲጠየቁ ሳይጠቅሱ የማያልፉት ሙሉ ጊዜያቸውን ለግድቡ መስጠታቸውን ነው። ይህ ግብራቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተመሰከረለት ነው።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን በአንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ "ስመኘው ልጆቹን፣ ሚስቱን እና ቤተሰቡን ትቶ ያገባው ሕዳሴን ነበር" ብለዋል።
የቤተሰብ አባሎቻቸውም የሚያስረግጡት ይህንኑ ነው።
የኢንጂነሩን ሕልፈት ተከትሎ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የቤተሰብ አባል "እሱ አገሬን ሥራዬን እያለ ሁሉም ሰው ረስቶታል። እሱ ሁሉ ነገሩ ሥራው ላይ ነበር። ዘመድ አይልም . . ." ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እኚህ የቤተሰብ አባል እንዳሉት ኢንጂነሩ ማኅበራዊ ሕይወት የሚባል ነገር እንኳን አልነበራቸውም።
ኢንጂነሩ ለሕጻናት ልጆቻቸው፣ ለደካማ ቤተሰቦቻቸው፣ ለራሳቸው እንዲሁም ለማኅበራዊ ሕይወታቸው መስጠት ያለባቸውን ጊዜ ሁሉ ለግድቡ ገብረዋል።
ለወጣቶቹ የሜካኒካል ኢንጂነሮች ቀድሞ ቀልባቸውን የሚሰርቀው የግድቡ ግንባታ የሚካሄድበት ስፍራ ግዝፈት ነው።
አሁን በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የአፍሪካ ግዙፉ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ግድብ በ2003 ዓ.ም. የመሠረት ሥራውን ለማስጀመር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየቆፈሩ ነበር።
ሞገስ የሺዋስ በ2003 ዓ.ም. በሙያው በቂ ልምድ ለማግኘት ተስፋ ሰንቆ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲደርስ ገና የ27 ዓመት ወጣት ነበር።
የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ አገሩን እንደሚቀይር ተስፋ ቢያደርግም የእርሱንም ሕይወት ቀይሮታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሰኞ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በይፋ ሲመረቅ ለአገሪቱ የኤሌትሪክ ብርሃን መስጠት ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ኃይል ያቀርባል ብለዋል።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዛሬ ማክሰኞ ጳጉሜ 4 2017 ዓ.ም. የተለያዩ የጎረቤት አገራት መሪዎች በተገኙበት ተመረቀ።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት፣ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌህ እንዲሁም የሶማሌው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ተገኝተዋል።
የጂቡቲው እና የኬንያው ፕሬዚዳንት በሕዳሴው ግድብ የተቀመጠውን የምረቃ መጋረጃ ከፍተው መርቀውታል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የቀድሞ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።

የፎቶው ባለመብት, PM Office
የሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው በ2003 ዓ.ም ሲሆን ለማጠናቀቅ 14 ኣመታትን ፈጅቷል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 233 ቢሊየን ብር ለግንባታው ወጥቶበታል።
ከአጠቃላይ ወጪው ውስጥ 223 ቢሊየን ብር ወይም 91 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘ ሲሆን ቀሪው 9 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከሕዝብ ተሳትፎ የተገኘ ገንዘብ ነው።
18.9 ቢሊየን ብር በኢትዮጵያውያን እና በትውልደ ኢትዮጵያዊን የቦንድ ሽያጭ፣1.6 ቢሊየን ብር በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያን የቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ፣ 3.2 ቢሊየን ብር ከስጦታ ተሰብስቧል።
1.78 ኪሎ ሜትር የተዘረጋው ይህ ግዙፍ ግድብ 145 ሜትር ከፍታ አለው።
ግድቡ 13 ተርባይኖች ያሉት ሲሆን ከ5000 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ያመነጫል።