የታላቁ ሕዳሴ ግድብ "ፊት" የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሲታወሱ

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ሲመሩ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ
የምስሉ መግለጫ, ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የግድቡን ግንባታ ፕሮጀክት ለሰባት ዓመታት መርተዋል

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲነሳ በረሃ ባጠየመው ፊታቸው ላይ ጺማቸው የጎፈረ አንድ ጎልማሳ አይዘነጉም።

የእኚህ ሰው ስም እንዲሁ አይጠራም። ብዙ ቅጽሎች ይቀድሙታል። የጉባው መናኝ፣ ህልመኛው፣ ታታሪው፣ ትሁቱ፣ ባህታዊው. . . ሌላም ሌላም።

ጉባ እና የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት መኖሪያቸውም መለያቸውም የሆነ፤ እርሳቸውም ለግድቡ "ፊት" የነበሩ ሰው።

ስማቸው ከግድቡ ጋር ከተጣበቀ ባለታሪኮች መካከልም አንዱ ናቸው - ኢንጂነር ስመኘው በቀለ።

ኢንጂነሩ የመሠረተ ድንጋይ ከተጣለበት መጋቢት 24/2003 ዓ.ም. አንስቶ የግድቡን ፕሮጀክት ለሰባት ዓመታት መርተዋል።

በእነዚህ ዓመታት ከጉባ በረሃ ጠፍተው አያውቁም።

ባልደረቦቻቸው፣ የሚያውቋቸው፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው ስለ እርሳቸው ሲጠየቁ ሳይጠቅሱ የማያልፉት ሙሉ ጊዜያቸውን ለግድቡ መስጠታቸውን ነው። ይህ ግብራቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተመሰከረለት ነው።

የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ላይ "ስመኘው ልጆቹን፣ ሚስቱን እና ቤተሰቡን ትቶ ያገባው ሕዳሴን ነበር" ብለዋል።

የቤተሰብ አባሎቻቸውም የሚያስረግጡት ይህንኑ ነው።

የኢንጂነሩን ሕልፈት ተከትሎ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የቤተሰብ አባል "እሱ አገሬን ሥራዬን እያለ ሁሉም ሰው ረስቶታል። እሱ ሁሉ ነገሩ ሥራው ላይ ነበር። ዘመድ አይልም . . ." ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እኚህ የቤተሰብ አባል እንዳሉት ኢንጂነሩ ማኅበራዊ ሕይወት የሚባል ነገር እንኳን አልነበራቸውም።

ኢንጂነሩ ለሕጻናት ልጆቻቸው፣ ለደካማ ቤተሰቦቻቸው፣ ለራሳቸው እንዲሁም ለማኅበራዊ ሕይወታቸው መስጠት ያለባቸውን ጊዜ ሁሉ ለግድቡ ገብረዋል።

እርሳቸው የግድቡን ሥራ እየመሩ በነበረበት ወቅት ባልደረባቸው የነበረችው ኢንጂነር ብሩክታዊት እሸቱ፣ "ኢንጂነሩ እረፍት አልበራቸውም" ስትል ለቢቢሲ እማኝነቷን ሰጥታለች።

የግድቡ ግንባታ 24 ሰዓት የሚከናወን ስለነበር ሌሊት ሳይቀር ወደ ግንባታው ሥፍራ በድንገት የመጡበት ቀን ጥቂት እንዳልነበር ትናገራለች።

በዚህ ሁሉ ውስጥ እያለፉ "ትህትናቸው ያስገርመኝ ነበር" የምትለው ብሩክታዊት፣ እውቀታቸው እና አክብሮታቸው የሠራተኛውን ቀልብ የገዛ እንደነበርም ታወሳለች።

የሙቀት መጠኑ 43 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርሰውን የጉባን በረሃ ተቋቁመን እንድንሠራ የሚያበረቱን እርሳቸው ነበሩም ትላለች።

"እንኳን በእርሳቸው የኃላፊነት ደረጃ በእኛ ደረጃም ከባድ መስዋዕትነት ነው የከፈልነው" ስትልም ኢንጂነሩ ታሪክ እና ሕልም ተሸክመው ያሳለፏቸው ጊዜያት ቀላል እንዳልነበሩ ትዘክራለች።

"ሲመጡ እንደ አገር መሪ ነበር የምንቀበላቸው"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዎል ስትሪት ጆርናል የአፍሪካ ዘጋቢ ማቲና ስቴቪስ ግሪድኒፍ የኢንጂነሩን ሕልፈት ተከትሎ ለቢቢሲ ስትናገር፣ "እርሳቸው የመጡት ይህንን አገራዊ ህልም ለመወከል ነው" ብላለች።

ኢንጂነሩን በቅርበት እንደምታውቃቸው የተናገረችው ጋዜጠኛዋ፣ "ኢንጂነር ስመኘው የበዛ የአገር ፍቅር ያላቸው ለአገራቸው መለወጥ ሕይወታቸውን የሰጡ ነበሩ" በማለት ነበር የገለጸቻቸው።

"ለወደፊቷ ኢትዮጵያ የሚችሉትን ለማበርከት ሙሉ ሕይወታቸውን የሰጡ ይመስሉ ነበር" ስትልም አክላለች።

ኢንጂነሩም ቢሆኑ ህልማቸውን አብዝተው ይናገሩ ነበር።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ከአንድ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 'ሚት ኢቲቪ' ላይ ቀርበው በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ አንድ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

"አሁን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሆነው። ደስተኛ ነዎት ወይ?" የሚል።

ኢንጂነር ስመኘው ወደ ጥያቄው የተንደረደሩት የወሰዱት ኃላፊነት ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ ለመግለጽ በሚመስል አኳኋን ቁጥሮችን በመጥቀስ ነበር።

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምን ያህል ስፋት፣ ከፍታ እና ይዘት እንዳለው፣ ስንት ሠራተኞች እንደተሳተፉበት፣ ግድቡ ስለሚገኝበት ቦታ እና የአየር ጠባይ እንዲሁም ቤተሰባቸው ከሚኖርበት አዲስ አበባ ምን ያህል እንደሚርቅ አብራሩ።

ለጥያቄው ግን ቀጥተኛ ምላሽ አልነበረም የሰጡት።

". . . የአገራችን ዕድገት ጥሩ ሆኖ ማየት እንፈልጋለን። ለዘላቂ ልማት ደግሞ 'ሃይድሮ ፓዎር' የጀርባ አጥንት ነው። ሁሉም በግድቡ ላይ የሚሳተፈው የግድቡ ማኅበረሰብ ሙቀቱን እና ርቀቱን አያስበውም። ምክንያቱም ህልም አለን" ነበር ያሉት።

አገራቸው ከፍ ብላ፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ተሰልፋ ፣ ትውልዱ ካለፈው የተሻለ የሚኖርባት እንድትሆን ይመኙ ነበር።

ህልም ያነገቡት የግድብ ግንባታን እንደሚመራ እንደ አንድ ኢንጂነር ብቻ ሳይሆን ለአገር እና ለትውልድ እንደሚቆረቆር የአገር መሪም ጭምር ነበር።

"ሲመጡ እንደ ፕሮጀክት መሪ ሳይሆን እንደ አገር መሪ ነበር የምንቀበላቸው" የምትለው ብሩክታዊት፣ ይህን እንድናደርግ የሚያስገድደን እውቀታቸው እና ትህትናቸው ነበር ብላለች።

"ቦታው በጣም ከባድ ነው። በተራራ የተከበበ ቦታ ነው። እንደዚህ የሚገለጽ አይደለም። የበረሃው ነበልባል ይታይ ነበር" ስትልም ኢንጂነሩ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ሆነው የተጫወቱት ሚና በቃላት የሚገለጽ እንዳልሆነ ትናገራለች።

"ግድቡ ሲመረቅ ቢያዩት ትልቅ ኩራት ነበር። አሁንም ቢሆን ግድቡ ላይ ሐውልት ቢቀመጥላቸው እና በዚያ መልኩ ትውልድ ቢያስታውሳቸው ደስ ይለኛል።"

በግልገል ግቤ አንድ ከዚያም በሕዳሴ ግድብ ለሁለት ዓመት ገደማ አብረዋቸው የሠሩት እና የእርሳቸውን ሕልፈት ተከትሎ የግድቡን ግንባታ እንዲመሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮም፣ "ለሙያው ቦታ የሚሰጥ መሃንዲስ ነው። ለያዘው ሥራ እና ዓላማ ቁርጠኛ የሆነ፤ ብዙ ጊዜውን ለሥራው የሚሰጥ ጥሩ ሠራተኛ" ሲሉ ነበር የተናገሩት ከኢንጂነሩ ሞት በኋላ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ።

"የለፋበትን ውጤት ሳያይ ማለፉም አሳዝኖኛል።" ብለዋል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Grand Ethiopian Renaissance Dam

የምስሉ መግለጫ, ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 14 ዓመታት የፈጀ ሲሆን 233 ቢሊየን ብር እንደወጣበት ተገልጿል

"እንደ ተጨማሪ የስሜት ሕዋስ ነው የምንቆጥረው"

ግድቡ የዓለምን ትኩረት የሳበው እና ጂኦፖለቲካዊ ውዝግብ የተፈጠረው ወዲያውኑ ነበር።

የግድቡ ግንባታ በተጀመረ በአንድ ወር ውስጥ ነበር ስጋት የገባቸው ግብፅ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረው ጥናት ማካሄድ የጀመሩት።

የግድቡ ምልክት ተደርገው የሚቆጠሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ኃላፊነቱን የተረከቡት ዓለም ትኩረቱን ኢትዮጵያ ላይ ባደረገበት፣ የገንዘብ አቅም ባልጎለበተበት፣ "አባይን በአገሩ እናሳድረው በሚል ትልቅ ህልም እና ተስፋ" ብቻ ነበር።

ግንባታው ሲጀመርም ". . . አገራችንን ወደ ላቀ ደረጃ እናደርሳለን። ይህን ቃል ኪዳን ነው እየገባን ያለነው" ብለዋል።

ለግድቡ ሥራ አስኪያጅ ብቻ ሳይሆን እንደ ቃል አቀባይ እና የዘመቻ መሪ ሆነው እንዳገለገሉም ይነገርላቸዋል።

ኢንጂነር ስመኘው በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ድጋፍ እና ተሳትፎ የተጀመረው ታላቁ ሕዳሴ ግድብን ለሚጎበኙ የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜጎች እዚያው ጉባ በረሃ ላይ ቆመው እልፍ ጊዜ አስረድተዋል።

በንግግሮቻቸው ውስጥም ለአገር ያላቸው ፍቅር፣ ለሥራ ያላቸው ቁርጠኝነት እና ህልም ፍንትው ብሎ ይታይ ነበር።

ከማለፋቸው ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ከአገር ውጭ ለሚገኝ 'ሰላም' ለተሰኘ ሬዲዮ ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የተናገሩትም ለዚህ ማሳያ ይሆናል።

ኢንጂነሩ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን እንዴት እንደሚገልጹት ተጠይቀው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ምላሻቸውን በአንድ ጠንካራ ዓረፍተ ነገር ነበር ያሰሩት።

ግድቡን "እንደ ተጨማሪ የስሜት ህዋስ አድርገን ነው የምንቆጥረው" በሚል።

ሕዳሴ ግድብን ልክ እንደ ዓይን፣ እንደ አፍንጫ፣ እንደ ጆሮ፣ እንደ እጅ . . .።

ኢንጂነር ስመኘው የሕዳሴ ግድብን ሥራ ለመምራት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት እዚያው ደፋ ቀና ሲሉ ነበር።

". . . የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል፣ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውን ከፍ ማድረግ፣ መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር ማየት፣ መጪው ትውልድ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ የሚኖርባትን አገር መፍጠር ነው ህልማችን። ለዚህም ነው እራሳችንን እረስተን ተቋማዊ አስተሳሰብ እና አገራዊ አስተሳሳብ ይዘን ለውጥ እያየን ያለነው" ብለው ነበር በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ።

አንዳንዶችም 'የበረሃው ባህታዊ' የሚሏቸው ወደው አይደለም - "ራሳቸውን ረስተው" ለሕዳሴው ግድብ ማደራቸውን፤ ጉባ መመነናቸውን ልብ ቢሉ እንጂ።

ምንም እንኳን ወደ ኋላ ላይ የግድቡ የግንባታ ሒደት ተጓትቷል የሚሉ ቅሬታዎች ሲቀርቡ የነበረ ቢሆንም፤ ኢንጂነሩ የግድቡን ግንባታ ከመሠረት ድንጋይ ወደ ከ60 በመቶ በላይ ማድረሳቸው ተገልጿል።

የኢንጂነሩን ሕልፈት ተከትሎ ፕሮጀክቱን እንዲመሩ ሥልጣን የተሰጣቸው ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፣ ኃላፊነቱን ከተረከቡ ከአንድ ዓመት በኋላ የግድቡ ግንባታ ሒደት የደረሰበትን ደረጃ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

"የግድቡ ሲቪል ሥራ ወደ 84 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ደግሞ 28 በመቶ ደርሷል። በአጠቃላይ ግድቡ ወደ 68 በመቶ ደርሷል።"

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ከጀርባቸው የሕዳሴ ግድብ የሚታይበት ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢንጂነር ስመኘው ጥቅምት በግድቡ ግንባታ ሥፍራ

ኢንጂነር ስመኘው የውሃ ኃይል ማመንጫ ግንባታን ሲመሩ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያቸው አልነበረም።

በግልገል ግቤ አንድ እና በግልገል ግቤ ሁለት የውሃ ኃይል ማመንጫ ግንባታን መርተዋል።

ከአፍሪካ በግዝፈቱ ቀዳሚ የሆነው ግድብ ግንባታ የመጀመሪያ መሪ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው ጎንደር፣ ማክሰኝት በተባለች አነስተኛ ከተማ ነው የተወለዱት። የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በእንፍራንዝ፣ በደሴ እና በወልዲያ ከተሞች ተከታትለዋል።

ከዚያም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን ኮተቤ መብራት ኃይል ማሠልጠኛ ማዕከል፣ በኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ በዲፕሎማ ተመርቀዋል። በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል በሲቪል ምህንድስና ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚገኙ የተለያዩ የሃይድሮ ፓወር ኦፕሬሽን እና ፕሮጀክት አስተዳደር ሥልጣናዎችንም ወስደዋል።

በሥራቸውም ከመምህርነት ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የአገሪቱን ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታን እስከ መምራት ደርሰዋል።

የሕዝብ ዕይታ ውስጥ የገቡት እና ትኩረት የሳቡት ግን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን መምራት ከጀመሩ በኋላ ነበር።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ

የኢንጂነሩ ሞት እና ያልተመለሰው ጥያቄ

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን በሥራ አስኪያጅነት ለሰባት ዓመታት ከመሩ በኋላ ነበር በጨፍጋጋማው የሐምሌ ወር የኢንጂነሩ ድንገተኛ ሕልፈት የተሰማው።

ሐሙስ ሐምሌ 19/2010 ዓ.ም. ጠዋት ሕይወታቸው አልፎ የተገኘው አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ አደባባይ ቆማ በነበረችው ላንድክሩዘር ቪ8 መኪናቸው ውስጥ ነበር።

ዜናው በርካቶችን ያስደነገጠ፣ ያሳዘነ፣ ያስቆጣም ጭምር ነበር።

ኢንጂነሩ እንዴት እንደ ዓይን ብሌናቸው ከሚያዩት ግድብ በዚህ መልኩ ተለዩ የሚለው እስካሁንም ድረስ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው።

ፖሊስ በወቅቱ ኢንጂነሩ የራሳቸውን ሕይወት ቀጥፈዋል ሲል ነው መግለጫ የሰጠው።

ከሆነስ ለምን ራሳቸውን አጠፉ? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ግን እስካሁን አልተገኘም።

ሞታቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተቃውሞዎች ተቀስቅሰው ነበር።

"ጀግና አይሞትም"፣ "ኢንጂነር ህያው ነው"፣ "ፍትህ ለኢንጅነር"፣ " የሚሉ መፈክሮች ተነበዋል፤ ተሰምተዋል። በርካታ ወጣቶችም "የኢትዮጵያ አምላክ ይፍረድ" የሚል ካናቴራ ለብሰው "ለኢንጂነሩ ፍትሕ" ጠይቀዋል።

የሁለት ወንድ እና የአንድ ሴት ልጆች አባት በነበሩት ኢንጂነሩ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅትም ልጆቻቸው ለአባታቸው ፍትሕን ሲጠይቁ ተደምጠዋል።

ከዚያን ጊዜ በኋላ ግን ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ የሚያውቋቸው በእርሳቸው ሕይወት እና አሟሟት ላይ ዝምታን መርጠዋል።

ሕልፈታቸው የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የግድቡ ግንባታ እየሄደ በነበረበት ፍጥነት በአስር ዓመት ውስጥም አይጠናቀቅም ብለዋል የሚል መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በብዛት ከተንሸራሸረ በኋላ ነበር።

ይህንን ተከትሎም የግድቡን ግንባታ ሒደት ለመጠየቅ ከቢቢሲ ለኢንጂነሩ ስልክ ተደውሎ ነበር።

ኢንጅነሩ ከመሞታቸው ከአንድ ቀን በፊት ለቢቢሲ በሰጡት በዚህ አጭር ቃለ ምልልስ ላይ እንዲህ ነበር ያሉት።

"የተባለውን ጉዳይ አልሰማሁትም። 'ኦርጋናይዝድ' ሁኑና በመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በኩል ኮሚዩኒኬት አድርጉኝ አግባብ ያለው ምላሽ እሰጣለሁ። . . .

"[ግድቡ] የአንቺም ፕሮጀክት ነው። መግለጫ ለመስጠት ዝግጁ ነን። አካሄድ ደግሞ ጠብቄ ብሄድ መልካም ስለሚሆን ነው። ፕሮጀክቱ እየተሠራ ነው።"

በንግግራቸው ውስጥ በብዙዎች ልብ ውስጥ የቀረው ትህትናቸው አልተለያቸውም ነበር - "ከአክብሮት ጋር!"።