ቀጥታ, የአሜሪካ ኢሚግሬሽን መኮንን የሦስት ልጆች እናትን ተኩሶ መግደሉን ተከትሎ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

የአሜሪካ የኢሚግሬሽን መኮንን የ37 ዓመቷን እና የሦስት ልጆች እናት የሆነችውን አሜሪካዊት ተኩሶ መግደሉን ተከትሎ በሚኒያፖሊስ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። የፌደራል ባለሥልጣናት ሟች ሬኔ ኒኮሌ ጉድ የኢምግሬሽን መኮንኑን ለማምለጥ ሙከራ አድርጋለች ብለው ሲከስሷት፣ የከተማዋ ከንቲባ ደግሞ ተኩሶ የገደላት ግለሰብ በግዴለሽነት እርምጃ ወስዷል ሲሉ ወንጅለውታል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የየመኑ ተገንጣይ ቡድን መሪ 'በሶማሊያ በኩል ወደ አቡዳቢ ሸሽቷል' መባሉን ተከትሎ ሞቃዲሾ ምርመራ ጀመረች

    የደቡብ የመን ሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባይዲ

    የፎቶው ባለመብት, X

    የሶማሊያ የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ የደቡብ የመን ሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባይዲ የአየር ክልሏን ያለፈቃድ ተጠቅሟል መባሉን ተከትሎ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።

    የኢሚግሬሽንና የዜግነት ኤጀንሲ (አይሲኤ) ሐሙስ ታሕሳስ 30 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ የአየር ክልልና የአውሮፕላን ማረፊያዎች የአገሪቱን ሕግ ወይም ፈቃድ በመጣስ የ"ተፈላጊ ፖለቲከኛ"ን ጉዞን ለማመቻቸት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ከሌሎች አገራት ባለሥልጣናት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የተገንጣይ ቡድኑ መሪ በጀልባ ወደ በርበራ ካመራ በኋላ በሞቃዲሹ በኩል ወደ አቡዳቢ መሄዱን ዘግቧል።

    የዜና ወኪሉ በየመን በሳዑዲ አረቢያ የሚመራውን ጥምረት ጠቅሶ እንደዘገበው የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባይዲ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በሶማሊላንድ በኩል አድርጎ አምልጧል።

    የአማፂ ቡድኑ መሪ ያመለጠው በሪያድ የሰላም ንግግር ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እያለ ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ ዩኤኢ ከአገር እንዲወጣ ረድታዋለች በማለት ወቅሳለች።

    የሶማሊያ መንግሥት ግን አይዳረስ አል ዙባይዲ በጀልባ ወደ ሶማሊላንድ ስለማምራቱ የጠቀሰው ነገር የለም።

    የሶማሊያ የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ ዙባይዲ በሞቃዲሾ የአየር ክልል በኩል መውጣቱ ከተረጋገጠ፣ እርምጃዎቹ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የኢሚግሬሽን ሕጎች ላይ ከባድ ጥሰት መፈፀማቸውን እንደሚያመለክቱ ተናግሯል።

    ተፈላጊ ሰዎችን ማዘዋወር ወይም ያለ ፈቃድ በግዛቱ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም የተናጠል እንቅስቃሴዎችን ማመቻቸት “ተቀባይነት የሌለው” መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል።

    ሐሙስ ዕለት ሳዑዲ አረቢያ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን የየመን ተገንጣይ ቡድን መሪ የሆነው እና በአገር ክህደት ወንጀል የሚፈለግ ግለሰብን ከአገር ወጥቶ ወደ አቡዳቢ እንዲሸሽ በማድረግ ወንጅላታለች።

    የሳዑዲ መከላከያ የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባዲ ከየመን በጀልባ ወደ ሶማሊያ መሸሹን ተናግሮ ነበር።

    ሞቃዲሾ ሳዑዲ አረቢያ በየመን ያለውን ሁኔታ ለመፍታት በሪያድ ለመወያየት ያቀረበችውን ጥሪ “ተገቢ የፖለቲካ ሂደት” እንደሆነ በመግለጽ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።

    ኤጀንሲው አል ዙባይዲ “ይህንን ሂደት ለማምለጥ፣ የውጭ ድጋፍ በማግኘት ጭምር፣ የሚያደርገው ማንኛውም ጥረት ቀጣይነት ያለውን የዲፕሎማሲ ጥረት በቀጥታ የሚቃረን ይሆናል” ሲል አክሏል።

    ጥሰት መፈጸሙ ከተረጋገጠ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እና የዓለም አቀፍ ሕግን መጣስን እንደሚያመለክት ኤጀንሲው ጨምሮ አስጠንቅቋል።

    ኤጀንሲው “በምርመራው ግኝቶች ላይ በመመስረት ጥሰቶች መኖራቸው ከተረጋገጠ ሙሉ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ተገቢ እርምጃዎች ይወሰዳሉ” ብሏል።

  2. በዩክሬን የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ከማሞቂያ እና ውሃ አቅርቦት ውጭ ሆኑ

    በዛፖሪዝሂያ የኤሌክትሪክ መብራት በመጥፋቱ መኪኖች በጨለማ ጎዳና ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በዲኒፕሮፔትሮቭስክ ክልል ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ከማሞቂያ እና የውሃ አቅርቦት ውጪ መሆናቸውን ተናገሩ።

    ኦሌክሲ ይኩሌባ አክለውም በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል መሠረተ ልማቶችን ያወደመውን ሰፊ ​​ጥቃት ተከትሎ አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    በአጎራባች ዛፖሪዝሂያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ ሆነዋል፤ ነገር ግን አሁን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደነበረበት ተመልሷል።

    ሩሲያ በቅርቡ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች አጠናክራ ቀጥላለች።

    ይህም በከባድ ክረምት ወቅት የኃይል አቅርቦቱን ለማዳከም ያለመ ነው። ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጥቃቱን "ማላገጥ" ሲሉ ጠርተውት የምዕራባውያንን ድጋፍ ጠይቀዋል።

    በድኒፕሮፔትሮቭስክ የሚገኙ ሆስፒታሎች፣ የውሃ ተቋማት እና ሌሎች ወሳኝ አገልግሎቶች በመጠባበቂያ ስርዓቶች እየሰሩ መሆናቸውን የኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀማቸው ላይ ተጨማሪ ጫና እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

  3. አሜሪካውያንን ስላስቆጣው የ37 ዓመቷ አሜሪካዊት ግድያ እስካሁን የምናውቀው

    የ37 ዓመቷ አሜሪካዊት ሬኔ ኒኮል ጉድ

    የፎቶው ባለመብት, Facebook

    የአሜሪካ የኢሚግሬሽን መኮንን የ37 ዓመቷን አሜሪካዊት ተኩሶ መግደሉን ተከትሎ በሚኒያፖሊስ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

    የፌደራል ባለሥልጣናት ሟች ሬኔ ኒኮሌ ጉድ የኢምግሬሽን መኮንኑን ለማምለጥ ሙከራ አድርጋለች ቢሉም የከተማዋ ከንቲባ ግን ተኩሶ የገደላት ግለሰብ በግዴለሽነት እርምጃ ወስዷል ሲሉ ወንጅለውታል።

    ሬኔ ኒኮል ጉድ ወላጆች ከቤቷ ጥቂት ርቆ በሚገኝ ስፍራ ስለተገደለችው ልጃቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    አባቷ ቲም ጋንገር ለዋሽንግተን ፖስት “ጥሩ ግን ደግሞ አስቸጋሪ ሕይወት ነበራት” ካሉ በኋላ “ድንቅ ሰው ነበረች” ሲሉ ገልጸዋታል።

    ተሸላሚ ገጣሚ እና በትርፍ ጊዜዋ ጊታር ተጫዋች ነበረች ያሉት ደግሞ የሚኒሶታ ሴናተር ቲና ስሚዝ ናቸው።

    የከተማው አስተዳዳሪዎች ጉድ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ መኮንኖች (አይስ) እንቅስቃሴዎችን ሕጋዊነት የምትከታተል እንደነበረች መስክረዋል። ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር "የአገር ውስጥ አሸባሪ" ሲል ጠርቷታል።

    እናቷ ዶና ጋንገር ለሚኒሶታ ስታር ትሪቡን እንደተናገሩት ልጃቸው መኮንኖቹን በተጋፈጠችበት ወቅት “ምናልባት ፈርታ የነበረ ይሆናል” በማለት “ከማውቃቸው ደግ ሰዎች መካከል አንዷ ነች” ብለዋል።

    የአሜሪካዊቷን ሞት ተከትሎ አደባባይ የወጡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ የሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የአይስ መኮንኖች መንገድ መሃል ላይ ያለን መኪና ሲጠጉ ያሳያል።

    መኪናው መንቀሳቀስ ሲጀምር አንዱ መኮንን አሽከርካሪዋ ላይ ሽጉጡን በማነጣጠር ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሲተኮስ ይሰማል።

    ኤፍቢአይ በግድያ ወንጀሉ ላይ ምርመራ እያደረገ ነው።

    ዋይት ሐውስ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት የያዘውን ዘመቻ ተከትሎ በሚኒሶታ ግዛት ስር በምትገኘው ሚኒያፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአይስ መኮንኖች ተሰማርተዋል።

    የ37 ዓመቷ አሜሪካዊት ሬኔ ኒኮሌ ጉድ በአይስ መኮንን በተተኮሰባት ጥይት ከተገደለች በኋላ የከተማዋ ነዋሪዎች ሻማ በማብራት እና የተቃውሞ መፈክሮችን በማሰማት ቁጣቸውን እየገለፁ ነው።

    አንድ የሚኒያፖሊስ ነዋሪ ለቢቢሲ “በርካቶች በፍርሃት ውስጥ ናቸው” ብሏል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት በኢሚግሬሽን መኮንን ስለተፈጸመው ግድያው የተለያየ መረጃ እየሰጡ ነው።

    የአሜሪካ አገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት ክርስቲ ኖኤም ሬኔ ኒኮሌ ጉድ መኮንኑን ቀኑን ሙሉ “ስትከታተለው እና ስትደበቀው” ነበር ያሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለማምለጥ ሙከራ በማድረግ “መኪናዋን እንደ መሣሪያ ተጠቅማለች” በማለት ይህም “የአገር ውስጥ ሽብርተኝነት ነው” ብለዋል።

    የሚኒያፖሊስ ከተማ ምክር ቤት ግን ግለሰቧ ተተኩሶባት የተገደለችው “ለጎረቤቶቿ በነበራት ርህራሄ ነው” ብሏል።

    የከተማው ከንቲባ የተኮሰባት መኮንን በግዴለሽነት እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

    የሚኒሶታ አስተዳዳሪ ቲም ዋልዝ በበኩላቸው ስለግድያው የፌደራል መንግሥቱ ያለውን እንደማይቀበሉ አስታውቀው “ሙሉ፣ ፍትሃዊ እና ፈጣን ምርመራ እንዲደረግ” ጠይቀዋል።

    የሚኒያፖሊስ ፖሊስ አዛዥ ብራያን ኦ ሃራ በበኩላቸው አሽከርካሪዋ መንገድ ዘግታ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

    የፌደራል ሕግ አስከባሪዎች በእግራቸው ሲጠጓት ልታመልጥ ሞክራለች ሲሉም ወንጅለዋታል።

  4. ትራምፕ አሜሪካ ከ66 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንድትወጣ አደረጉ

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከበርካታ ዓለም አቀፍ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች እንደምትወጣ አስታወቁ።

    ከ66ቱ መካከል ግማሽ ያህሉ የተባበሩት መንግሥታት አካል የሆኑ ድርጀቶች ሲሆኑ፥, የዓለም ሙቀት መጨመርን የሚታገለው የመንግሥታቱ የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍም ይገኝበታል።

    ዋይት ሐውስ እንዳለው እርምጃው የተወሰደው እነዚህ ድርጅቶች “ለአሜሪካ ጥቅም አስፈላጊ ስላለሆኑ” እና “የማይሰራ ወይም አደገኛ አጀንዳ” ስለሚያራምዱ ነው።

    ከዚህ ቀደም የአየር ንብረት ለውጥ “ሐሰተኛ” ነው ሲሉ ያጣጣሉት ትራምፕ የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ፈንድ ሰርዘዋል።

    ዋይት ሐውስ ረቡዕ ዕለት “የግብር ከፋዮችን ገንዘብ የሚያባክኑ” ካሏቸው ድርጅቶች አሜሪካ ራሷን እንድታገል የሚያደርግ ሰነድ ፈርሟል።

    “ከድርጅቶቹ መውጣታችን አሜሪካዊያን ግብር ከፋዮች ገንዘባቸው አሜሪካ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች ይልቅ ለዓለም አቀፍ ጉዳዮች እንዳይውል ያደርጋል” ይላል መግለጫው።

    አሜሪካ በሰነዱ መሠረት በሰላም እና ደኅንነት፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የእናቶችን እና የሕፃናት ጤና እንዲሁም በግጭት ወቅት የሚሰከቱ ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ራሷን አግልላለች።

    ትራምፕ ሀገራቸውን ከዓለም አቀፍ ተቋማት ማግለላቸው ሕጋዊ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ተገምቷል።

    ተንታኞች እና የፖሊሲ አርቃቂዎች የትራምፕን ድርጊት “አምባገነናዊ” እና “ፀረ-ሳይንስ” ሲሉ ተችተውታል።

    ትራምፕ ባለፈው ዓመት የዓለም ሀገራት የሙቀት መጠንን ለመቀነስ ቃል-ኪዳን ከገቡበት የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ሀገራቸውን ከማግለላቸውም በተጨማሪ ብራዚል በተካሄደው ኮፕ30 አለመሳተፋቸው ይታወሳል።

    የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያተኩረው ኮፕ32 ስብሰባ ከሁለት ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ይዘጋጃል።

  5. አሜሪካ ለሶማሊያ የምትሰጠውን ሁሉንም ድጋፍ ማቋረጧን አስታወቀች

    የዓለም የምግብ ድርጅት እርዳታ በሶማሊያ

    የፎቶው ባለመብት, AP

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ለሶማሊያ መንግሥት የሚያደርገውን ሁሉንም ድጋፍ ማቋረጡን አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ እንዳለው ድጋፉ የተቋረጠው የሶማሊያ ባለሥልጣናት በአሜሪካ እርዳታ የተገነባ የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘንን በማውደማቸው እና እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የተዘጋጀ 76 ሜትሪክ ቶን ምግብ በቁጥጥር ሥር በማዋላቸው ነው።

    “የትራምፕ አስተዳደር የምግብ ብክነት፣ ዘረፋ እና ሕይወት አድን እርዳታ መያዝን አይታገስም” ማለቱን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    መግለጫው አክሎ “የአሜሪካ መንግሥት ለሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጥቅም ያላቸው ሁሉንም ድጋፎች አቋርጣል” ይላል።

    “የተቋረጠው ድጋፍ የሚቀጥለው የሶማሊያ መንግሥት ተቀባይነት ለሌለው ድርጊቱ ኃላፊነት የሚወስድ ከሆነ እና አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰደ ነው።”

    አሜሪካ ለሶማሊያ የምትሰጠው ድጋፍ መቋረጡ የተሰማው የትራምፕ አስተዳደር በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሶማሊያዊያን ላይ ትችት እያሰማ በሚገኝበት ወቅት ነው።

    ዋሺንግተን ወደ አሜሪካ መምጣት በሚፈልጉ ሶማሊያዊያን ላይ ጠንከር ያለ ገደብ የጣለች ሲሆን፣ አሜሪካ የሚገኙ ሶማሊያዊያንም ስጋት ላይ እንዳሉ ይነገራሉ።

    የትራምፕ አስተዳደር ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅትን (ዩኤስኤይድ) ማፍረሱ ይታወሳል።

  6. የኢራን ተቃውሞ ወደ አዳዲስ አካባቢዎች ሲስፋፋፋ ከባድ ግጭቶች መከሰቱ ተነገረ

    ተቃዋሚዎች በምሽት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ

    የፎቶው ባለመብት, UGC

    በኢራን በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ 11ኛ ቀኑን ሲይዝ፣ ረቡዕ ዕለት በፀረ መንግሥት ተቃዋሚዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ከባድ ግጭት ተከስቷል።

    ለኢራን አብዮታዊ ዘብ ቅርበት ያለው ፋርስ ዜና ወኪል እንደዘገበው ሎርዴጋን በተባለ ከተማ ሁለት የፖሊስ መኮንኖች መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

    በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የተለጠፉ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የጥይት ድምፆች እና ተቃዋሚዎች እና የፀጥታ ኃይሎች በውጥረት ሲፋጠጡ አሳይተዋል።

    በሌሎች አካባቢዎችም የፀጥታ ኃይሎች ድንጋይ ሲወረወርባቸው እና በተቃዋሚዎች ላይ ጥይት እና አስለቃሽ ጋዝ ሲተኩሱ ታይተዋል።

    ተቃውሞው እስካሁን በ31 ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ 111 ከተሞች መዛመቱን በአሜሪካ መቀመጫውን ያደረገው ህራን የተባለ የዜና ምንጭ ጠቅሷል።

    የዜና ምንጩ በተቃውሞው ቢያንስ 34 ተቃዋሚዎች እና አራት የፀጥታ ኃይል አባላት መገደላቸውን እና 2,200 የሚሆኑ ተቃዋሚዎች ደግሞ መታሰራቸውን አስታውቋል።

    ቢቢሲ ፐርሺያ 21 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጦ ማንነታቸውን ለይቷል። የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው አምስት የፀጥታ አባላት መገደላቸውን ገልፀዋል።

  7. ዩኬ ለአሜሪካ ድጋፍ ማድረጓን ስትገልፅ ሩሲያ የአሜሪካን ተግባር ኮንናለች

    በአውሮፓው የአሜሪካ ዕዝ ያጋራው ምስል

    የፎቶው ባለመብት, US EUROPEAN COMMAND

    የሩሲያ ትራንስፖርት ሚኒስትር “የትኛውም ሀገር በአንድ ሀገር የተመዘገበ መርከብን በኃይል የመያዝ መብት የለውም” የሚል መግለጫ አውጥቷል።

    በቀድሞ ስሙ ቤላ 1 ተብሎ የሚታወቀው የነዳጅ መርከብ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር መዋሉን ተክተሎ ነው ሩሲያ መግለጫ ያወጣችው።

    አሜሪካ ከቬንዙዌላ ነዳጅ ጋር ግንኙነት ያለው መርከብ ማዕቀብ ጥሷል በማለት አድና በቁጥጥር ሥር ማዋሏን አስታውቃለች።

    ማሪኔራ ተብሎ የሚጠራው መርከብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሩሲያ ባንዲራ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን ሞስኮው መርከቡን ለማጀብ የባሕር ኃይሏን አሰማርታ ነበር።

    የሩሲያ መግለጫ እንደሚጠቁመው በሞስኮው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 9 ሰዓት የአሜሪካ ኃይሎች መርከቧን በቁጥጥራቸው ስር ካዋሉ በኋላ ከመርከቡ ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋርጧል ብሏል።

    ሚኒስቴሩ አክሎ እንደገለፀው ማሪኔራ ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ጀምሮ “በጊዜያዊ ፈቃድ” በሩሲያ ባንዲራ ሲንቀሳቀስ ነበር።

    በተያያዘ ዜና ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ መርከቡን በቁጥጥር ሥር እንድታውል ድጋፍ ማድረጓን አስታውቃለች።

    የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መርከቡ በሰሜን አትላንቲክ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ድጋፍ ማድረጉን አስታውቆ “መርከቡ ሩሲያ እና ኢራን ማዕቀብ ጥሰው ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ዩክሬን ሽብርን፣ ግጭት እና መከራን የሚያስፋፉበት ነው” ብሏል።

    አሜሪካ ከዚህ መርከብ በተጨማሪ ሌላ ቬንዙዌላ ላይ የተጣለ ማዕቀብ የጣሰ ነው ያለችውን መርከብ ካሬቢያን ላይ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታውቃለች።

  8. አሜሪካ እያደነችው የነበረውን የነዳጅ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች

    በአውሮፓ የአሜሪካ ዕዝ

    የፎቶው ባለመብት, US EUROPEAN COMMAND

    በአውሮፓ የአሜሪካ ዕዝ ከቬንዙዌላ ነዳጅ ጋር ግንኙነት ያለው እና በአሜሪካ ሲታደን የነበረው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታወቀ።

    ዕዙ የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር እና የሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤትን ዋቢ አድርጎ “ኤም/ቪ ቤላ 1 የአሜሪካን ማዕቀብ በመጣሱ” በቁጥጥር ሥር ውሏል ብሏል።

    “መርከቡ በአሜሪካ ፌዴራል ፍርድ ቤት በወጣበት ማዘዣ መሠረት በሰሜን አትላንቲክ በቁጥጥር ሥር ውሏል” ይላል ዕዙ በኤክስ ገፁ ያጋራው መግለጫ።

    ዩኤስሲጂሲ ሙንሮ የተባለው የአሜሪካ የጦር መርከብ ነዳጅ ጫኝ ታንከሩን ተከታትሎ እንደያዘውም አክሏል።

    በአውሮፓውያኑ 2024 ሕጋዊ ያልሆነ ነዳጅ በማመላለስ ማዕቀብ የተጣለበት መርከብ ባንዲራውንና ባለቤትነቱን ወደ ሩሲያ ቀይሮ ሲንቀሳቀስ ነበር።

    ሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከቡን ለማጀብ ሰርጓጅ መርከብ ጨምሮ የባሕር ኃይሏን ብታሰማራም አሜሪካ መርከቡን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏለች።

    ባለፈው ቅዳሜ የቬንዙዌላውን ፕሬዝደንት በቁጥጥር ስር ያዋለው የትራምፕ አስተዳደር ከቬንዙዌላ የሚወጡና የሚገቡ መርከቦች ላይ ማዕቀብ የጣለው ባለፈው ወር ነበር።

    መርከቡ ከዚህ ቀደም የቬንዙዌላን ነዳጅ ያመላልስ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ምንም ዓይነት ነዳጅ እንዳልጫነ ተዘግቧል።

  9. ማሪናራ የተባለው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በአሜሪካ እየታደነ ያለው ለምንድነው?

    ማሪናራ የተሰኘው ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከዚህ ቀደም ቤላ 1 በተባለ ስሙ የሚታወቀው ነዳጅ ጫኝ መርከብ ባለፈው ወር ወደ ቬንዙዌላ እየሄደ እንደሆነ ተዘግቦ ካሪቢያን ላይ ታይቶ ነበር።

    የአሜሪካ ባሕር ጠረፍ ጠባቂ ኃይል አባላት (ኮስት ጋርድ) መርከቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ማዘዣ አውጥተው ሲጠባበቁት ነበር። መርከቡ የአሜሪካን ማዕቀብ ጥሷል፤ የኢራንን ነዳጅ ጭኗል ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ትወቅሳለች።

    ነዳጅ ጫኙ መርከብ ይሄኔ ነው ስሙን ብቻ ሳይሆን ሰንደቅ ዓላማውን ወደ ሩሲያ ቀይሮ የሚመጣበትን መንገድ ትቶ በሌላ አቅጣጫ መጓዝ የጀመረው።

    ከዚህ ቀደም በሐሰተኛ መንገድ በጉያና ሰንደቅ ዓላማ ይንቀሳቀስ ነበር። የቬንዙዌላን ነዳጅ በማመላለስ የሚታወቀው መርከብ አሁን ምንም ነገር እንዳልጫነ ተነግሯል።

    የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሰሜን አትላንቲክ የተሰማሩ ሲሆን፣ ሩሲያ ደግሞ መርከቡን ከአሜሪካ ኃይሎች ለመጠበቅ በሰርጓጅ መርከብ ታግዛ ለማጀብ ተንቀሳቅሳለች።

    መርከቡ በድንገት አቅጣጫውን ወደ ደቡብ ቀይሮ በአሁኑ ወቅት ከአይስላንድ ጠረፍ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ቢቢሲ ያረጋገጠው መረጃ ያሳያል።

  10. “በሕገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ከሀገር ሊወጡ የነበሩ” 7900 ሰዎች መያዙን የአፋር ክልል ፖሊስ አስታወቀ

    የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ቢል አህመድ

    የፎቶው ባለመብት, Afar Police/FB

    የአፋር ክልል ፖሊስ በሕገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ 8 ሺህ ገደማ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

    ባለፉት 6 ወራት ብቻ 7900 ሰዎች በሕገ-ወጥ መንገድ በአፋር በኩል ከሀገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

    የፖሊስ ኮሚሽነር ቢልኤ አህመድ “በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ሰዎች መነሻቸው እና መድረሻቸው አፋር ክልል አለመሆኑ ሁኔታዎች አስቸጋሪ አድርጎብናል” ማለታቸውን የክልሉ ፖሊስ በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ቢሆንም የክልሉ ፖሊስ የዝውውር መስመር ናቸው ባላቸው ቦታዎች ላይ ቁጥጥር እና ፍተሻ በማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ነበር የተባሉ ሰዎችን መያዙን ገልጿል።

    በፖሊስ የተያዙት ሰዎች “አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎላቸው በአፋር ክልል ወጪ ወደመጡባቸው ከተማዎች ተመልሰዋል” ይላል መግለጫው።

    ኮሚሽነሩ በአብዛኛው የሕገ-ወጥ ዝውውር መነሻዎች ከአማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ከአማራ ክልል ጋር ሁኔታውን ለመቆጣጠር እየሠራን ነው ብለዋል።

    ማክሰኞ ዕለት ከሀገር ሊውጡ የነበሩ 85 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የጭነት መኪና ተገልብጦ 22 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

    የግለሰቦቹ የመጨረሻ መዳረሻ በግለፅ ባይታወቅም መስመሩ በጂቡቲ አድርገው፤ በቀይ ባሕር በኩል ወደ የመን ቀጥሎም ወደ ሳዑዲ አራቢያና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚጓዙ ስደተኞች የሚጠቀሙበት ነው።

  11. የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶማሊያን ሊጎበኙ ነው

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋንግ ዪ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት ለሚቆይ ይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሶቶ ሊጓዙ መሆኑን መሥሪያ ቤታቸው አስታወቀ።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመጨረሻ ጊዜ በሶማሊያ ጉብኝት ያደረጉት በአውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ እንደሆነ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    ከዛሬ ታኅሣሥ 29 እስከ የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ጥር 4/2018 ዓ.ም. የሚቆየው ጉዞ፤ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲሱ አውሮፓውያን ዓመት የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉብኝት እንደሚሆን መግለጫው ያስረዳል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላለፉት 36 ተከታታይ ዓመታት፤ የዓመቱ የመጀመሪያ የውጭ ጉዞ መዳረሻቸውን ወደ አፍሪካ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሷል። ዋንግ ዪ ወደ አራቱ አገራት የሚጓዙት በቀረበላቸው ግብዣ አማካኝነት ነው ተብሏል።

    ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አፍሪካ መዳረሻዎች መካከል በቀዳሚነት የተጠቀሰችው ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ “በአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት በሚካሄደው የቻይና-አፍሪካ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት” እንደሚገኙ ተገልጿል።

    መግለጫው ሶማሊያን በሁለተኛነት ጠቅሷል። እንደ ሬውተርስ ዘገባ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሶማሊያ የተጓዘው በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ሲሆን የአሁኑ ጉብኝት ከ40 ዓመታት ገደማ በኋላ የመጀመሪያው ይሆናል።

    እስራኤል ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ የመጀመሪያውን የአገርነት እውቅና ከሰጠች በኋላ የሚደረገው ይህ ጉብኝት፤ ለሞቃዲሾ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል።

    የእስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና ከሰጠች በኋላ ለሶማሊያ ያላትን ድጋፍ በድጋሚ ያረጋገጠችው ቤይጂንግ፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ዙሪያ ተፅዕኖዋን ለማጠናከር ትሻለች። ይህ ቀጣና ወደ ቀይ ባሕር መግቢያ ከመሆኑም በላይ በስዊዝ ካናል በኩል ወደ አውሮፓ ገበያ ለሚጓዘው የቻይና ንግድ ወሳኝ መተላለፊያ መስመር ነው።

  12. ሩሲያ በአሜሪካ እየታደነ ያለውን ነዳጅ ጫኝ ታንከር ለማጀብ ሰርጓጅ መርከብ አሰማራች

    በአሜሪካ ኃይሎች እየታደነ ያለው መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Hakon Rimmereid via Reuters

    ሩሲያ የአሜሪካ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እያደረጉበት ላለው በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የሚጓጉዝ የነዳጅ ጫኝ መርከብን ለማጀብ ሰርጓጅ መርከብን ጨምሮ የባሕር ኃይሏን ማሰማራቷን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘገበ።

    በአሁኑ ሰዓት ምንም ዓይነት ጭነት ያልያዘው ይህ መርከብ፤ ከዚህ ቀደም የቬንዙዌላን ድፍድፍ ነዳጅ ሲያጓጉዝ ቆይቷል። ማክሰኞ ዕለት በስኮትላንድ እና በአይስላንድ መካከል እየተጓዘ እንደነበረም ተገምቷል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማዕቀብ ተጥሎባቸው ነገር ግን ወደ ቬንዙዌላ በሚገቡ እና በሚወጡ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ "እገዳ" እንዲጣል ባለፈው ወር ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር። የቬንዙዌላ መንግሥት የትራምፕን ትዕዛዝ "ዘረፋ" ሲል ገልጾታል።

    ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በአሜሪካ ኃይሎች ተያዙት የአገሪቱ የቀድሞ መሪ ኒኮላስ ማዱሮ፤ የቬንዙዌላ መንግሥት መርከቦችን በመጠቀም ወደ አሜሪካ ዕፅ ያስገባሉ የሚል ተደጋጋሚ ክስ ከትራምፕ ሲቀርብባቸው ነበር።

    የአሜሪካ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እያደረጉበት ያለው "ማሪኔራ" የተሰኘው ይህ መርከብ ከዚህ ቀደም "ቤላ 1" በሚል ስም ይንቀሳቀስ ነበር።

    ባለፈው ወር ላይ የአሜሪካ የባሕር ጥበቃ ዘብ ባለፈው በካሪቢያን ባሕር ላይ እየተጓዘ በነበረውን "ቤላ 1" መርከብ ላይ ለመውጣት ሞክሮ ነበር። ባሕር ጥበቃ ኃይሉ ይህንን ያደረገው መርከቡ ወደ ቬንዙዌላ እያመራ ነው በሚል ጥርጣሬ እንደሆነ ተገልጿል።

    የአሜሪካን ማዕቀብ በመጣስ የኢራንን ነዳጅ ጭኗል የሚል ውንጀላ የቀረበበት ይህ መርከብ፤ በቁጥጥር ሥር እንዲውል የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶበት ነበር።

    ይሁን እንጂ መርከቡ በድንገት አቅጣጫውን የለወጠ ሲሆን ስሙንም "ማሪኔራ" በሚል ቀይሯል። ሲጓዝበት የነበረውን የጉያና ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ የሩሲያን እንደሰቀለም ተዘግቧል።

    የአሁኑ መርከቡ ወደ አውሮፓ የተቃረበበት እንዲሁም ወደ 10 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደራዊ ትራንስፖርት አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች ወደ ቀጣናው የደረሱበት ጊዜ ተገጣጥሟል።

    ሩሲያ በበኩሏ በመርከቧ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ "በስጋት እየተከታተልኩ ነው" ብላለች።

    ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት ለሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጹት ከሆነ፤ የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡ ላይ የመውጣት ዕቅድ አላቸው። የአሜሪካ መንግሥት መርከቡን ከማስጠም ይልቅ በቁጥጥር ስር ማዋልን እንደሚመርጥም ምንጮቹ ገልጸዋል።

  13. በዩክሬን የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ ጦራቸውን ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገለፁ

    የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ፣ የፈረንሳዩ ማክሮን እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ፤ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት የምትደርስ ከሆነ ወታደሮቻቸውን ለማሰማራት ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ስምምነት ተፈራረሙ።

    በፓሪስ ከዩክሬን አጋሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ዩኬ እና ፈረንሳይ ወደፊት ሊኖር የሚችል ወረራን ለመከላከል "በዩክሬን ዙሪያ ወታደራዊ ማዕከላትን እንደሚመሰርቱ" ተናግረዋል።

    በኋላ ላይ ደግሞ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ሊሰማሩ እንደሚችሉ ይፋ አድርገዋል።

    በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአውሮፓ አገራት፤ ለዩክሬን ጠንካራ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ ተስማምተው፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመከታተል ረገድ አሜሪካ ግንባር ቀደም እንድትሆን ሐሳብ አቅርበዋል።

    ነገር ግን ለሰላም ስምምነቱ እንቅፋት የሆነው ዋናው የግዛት ጉዳይ አሁንም በውይይት ላይ ነው።

    ሩሲያ፤ ዩክሬን ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም የውጭ አገር ጦር "ሕጋዊ ዒላማ" እንደሚሆን በተደጋጋሚ አስጠንቅቃለች።

    ሞስኮ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ስለተፈረመው ስምምነት እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

    የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እአአ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ላይ በከፈቱት ሙሉ ወረራ፤ በአሁን ሰዓት 20 በመቶ የአገሪቱን ግዛት በቁጥጥራቸው ሥር አስገብተዋል።

    ማክሰኞ ዕለት በፓሪስ በተካሄደው ውይይት ላይ ከ"በጎ ፈቃደኞች ጥምረት" የተውጣጡ መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተሳትፈዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ከስብሰባው በኋላ በነበረ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ “የሰላም ስምምነት የሚደረስ ከሆነ ወደ ዩክሬን የሚላኩ ኃይሎችን ለማሰማራት ስምምነት ፈርመናል። ይህ ከዩክሬን ጎን ለረዥም ጊዜ ለመቆም ያለን ቁርጠኝነት ወሳኝ አካል ነው" ብለዋል።

    የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ከአሜሪካ ጋር በመሆን ክትትል ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

  14. በኢራን በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ

    የኢራን ፖሊስ የግራንድ ባዛር የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል
    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፖሊስ የግራንድ ባዛር የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል

    ባለፉት 10 ቀናት በኢራን በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ።

    መቀመጫውን ከኢራን ውጭ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች የዜና ኤጀንሲ (ሂራና) እንደዘገበው ከተገደሉት መካከል 34ቱ ተቃዋሚዎች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

    የኢራን ባለሥልጣናት በይፋ የሟቾችን ቁጥር ባያሳውቁም ሦስት የደህንነት ሠራተኞች መገደላቸውን ተናግረዋል። ቢቢሲ ፐርሺያን እስካሁን የ20 ሰዎችን ሞት እና ማንነት አረጋግጧል።

    በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በተቀሰቀሰው እና 27ቱ የኢራን ከተሞች ተስፋፍቶ በቀጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከ60 በላይ ሰልፈኞች መቁሰላቸውን እና 2,076 ሰዎች መታሰራቸውን ሂራና ገልጿል።

  15. ትራምፕ፤ ቬንዙዌላ እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ነዳጅ ለአሜሪካ “ታስረክባለች” አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከሥልጣን ያስወገደው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ቬንዙዌላ እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ነዳጅ ለአሜሪካ “ታስረክባለች” አሉ።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ነዳጁ በገበያ ዋጋ እንደሚሸጥ እና ከሽያጩ የሚገኘውንም ገንዘብ ራሳቸው እንደሚቆጣጠሩ ተናግረዋል። ከነዳጁ የሚገኘው ገቢ ለቬንዙዌላ እና ለአሜሪካ ሕዝብ ጥቅም እንደሚውልም አክለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት፤ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በሚሆን ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ቬንዙዌላ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ከገለጹ በኋላ ነው። አሜሪካ ኩባንያዎች በቬንዙዌላ በሚኖራቸው እንቅስቃሴ ወደ ለአገሪቱ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ያገኛሉ ብለዋል።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተንታኞች፤ የቬንዙዌላን የነዳጅ ምርት ከዚህ ቀደም ወደነበረው ለመመለስ በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እና ምናልባትም አስር ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል አስረድተዋል።

    ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ልጥፍ፤ “የቬንዙዌላ የሽግግር ባለሥልጣን ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ጥራት ያለው እና ማዕቀብ የተጣለበት ነዳጅ ለአሜሪካ እንደሚያስረክቡ ሳበስር ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል።

    “ይህ ነዳጅ በገበያ ዋጋ ይሸጣል። እኔም እንደ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነቴ፤ ገንዘቡም ለቬንዙዌላ እና ለአሜሪካ ሕዝቦች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ እቆጣጠረዋለሁ!” ሲሉ ጽፈዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያስታወቁት፤ የቬንዙዌላ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዴልሲ ሮድሪጌዝ የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። በሌሊት በዋሽንግተን የጸጥታ ኃይሎች ከአገራቸው ተይዘው የተወሰዱት ኒኮላ ማዱሮ በአንጻሩ፤ በተመሰረተባቸውን የእፅ ዝውውር እና የጦር መሳሪያ ወንጀል ክስ የተነሳ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

    ሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኤንቢሲ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ነዳጅ አምራች የሆነችው ቬንዙዌላ መኖሯ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ያደርጋል” ብለዋል።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ የዋነኞቹን የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ተወካዮች በዚህ ሳምንት ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የመገናኘት እቅድ ይዘዋል።

  16. ቬንዙዌላን የሚመራት ማን ነው?. . . ፕሬዝዳን ትራምፕ መልስ. . .

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    • ከኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ጊዜ ቬንዙዌላን እየመራት ያለው ማን ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ” የሚል መልስ ሰጥተዋል
    • ትራምፕ አሜሪካ ከቬንዙዌላ ጋር ጦርነት ውስጥ አይደለችም በማለት "ጦርነት ላይ ያለነው ዕጽ ከሚሸጡት. . . እስረኞችን እየለቀቁ ወደ አገራችን ከሚልኩት ጋር ነው”

    የቬንዙዌላ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ማሪና ኮሪና ማቻዶ

    • ማቻዶ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት ትራምፕ በማዱሮ ላይ ለወሰዱት እርምጃ ምሥጋና አቅርበዋል
    • ለወራት ተደብቀው የቆዩት ተቃዋሚዋ በቶሎ ወደ ቬንዙዌላ መመለስ እንደንሚፈልጉ ገልጸዋል
    • ጨምረውም ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቷ ዴልሲ ሮዴሪጌዝ “ሊታመኑ የሚችሉ አይደሉም” ብለዋል

    የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን

    • ለመገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ “ቬንዙዌላ ውስጥ ጦር ሠራዊት የለንም፤ ያንንም አገር በወረራ አልያዝንም” በማለት አሜሪካ ጦርነት ውስጥ እንዳልሆነች ተናግረዋል
    • አክለውም "ይህ የሥርዓት ለውጥ አይደለም" ከዚያ ይልቅ "የአንድ ሥርዓትን ባህሪ መለወጥ አስፈላጊ የሆነበት ነው”
  17. የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሶማሊያ የተቃወመችውን ጉብኝት በሶማሊላንድ አደረጉ

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን እና ፕሬዝዳንት አብዲራህማን

    የፎቶው ባለመብት, @gidonsaar

    የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን እና ፕሬዝዳንት አብዲራህማን

    ለሶማሊላንድ የመጀመሪያውን የአገርነት ዕውቅና የሰጠችው የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር በሐርጌሳ ጉብኝት አደረጉ።

    ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትመለከታት ሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጉብኝት "ሕገወጥ እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው" ስትል ጉብኝቱን ተቃውማለች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እራሷን ከሶማሊያ በመነጠል ነጻ አገርነቷን ወዳጀችው ሶማሊላንድ ለጉብኝት ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ዕውቅናውን ከሰጡ ከአስር ቀናት በኋላ ነው።

    ጊዲዮን ሳር በሐርጌሳ ባደረጉት ጉብኝት ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልናት ጋር ውይይት ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን አስካሁን በይፋ የተነገ ነገር የለም።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ያናገራቸው ምንጭ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሶማሊላንድ ጉብኝት ማድረጋቸውን አረጋግጠው ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ከጉብኝቱ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን በኤክስ ገጻቸው ላይ ጉብኝታቸውን የሚገልጹ ፎቶግራፎች አጋርተው ከፕሬዝዳንቱ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    በተጨማሪም እስራኤል ለማን ዕውቅና እንደምትሰጥ እና ከየትኛው መንግሥት ጋር ግንኙነት እንደሚኖራት የምትወስነው ራሷ ብቻ ናት በማለት ለሶማሊላንድ ለሰጠችው ዕውቅና ያላትን አቋም አሳውቀዋል።

    በቀጣይም የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ በእስራኤል ጉብኝት እንዲያደርጉ የቀረባለቸውን ግብዣ እንደተቀበሉ ገልጸዋል።

    የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በጉብኝቱ ወቅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና በሶማሊላንድ ባለሥልጣናት መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን እና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸው መገለጹን አመልክቷል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጉብኝት "ሕገወጥ" በማለት ሶማሊያ ተቃውማ መግለጫ አውጥታለች።

    የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሚኒስትሩን ጉዞ "የሶማሊያን የግዛት ሉዓላዊነት እና አንድነትን የሚጥስ ነው" በማለት በተባበሩት መንግሥተት አባል አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው ሲል ጉብኝቱን ተቃውሟል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ጉብኝት የተደረገው ከሳምንት በፊት እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና ሰጥታ ተቃውሞ እና ውዝግብ ከተከሰተ በኋላ ነው።

    የእስራኤልን ውሳኔ ሶማሊያ እና የተለያዩ አገራት እንዲሁም ድርጀቶች ተቃውመውታል። ጉዳዩም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት በተጠራ ስብሰባ ውይይት ተደርጎበታል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር
  18. የአሜሪካ እርምጃ "ዓለም አቀፍ ሕግን" የሚጥስ ነው" የተመድ ኮሚሽን

    የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ማዱሮ በአሜሪካ የጸጥታ ኃይሎች ታይዘው ሲራመዱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን አሜሪካ ቬንዙዌላ ውስጥ የፈጸመችው ጥቃት "የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆችን የሚጥስ ነው" አለ።

    የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ጄኔቭ ውስጥ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ "በማንኛውም አገር የግዛት እንድነት ወይም ፖለቲካዊ ነጻነት ላይ ኃይል መጠቀምም ሆነ ማስፈራራት አይገባም" ብለዋል።

    ይህ የመንግሥታቱ ድርጅት አካል ተቃውሞ የተሰማው ሰኞ ዕለት በተካሄደው የድርጅቱ ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአሜሪካ አጋሮች ሳይቀሩ የትራምፕ ወታደራዊ እርምጃን መቃወማቸውን ተከትሎ ነው።

    ከእነዚህም መካከል የፈረንሳይ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ የማዱሮ በአሜሪካ መያዝ "አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት መርኅ እና ኃይል ካለመጠቀም መርኅ ጋር የሚቃረን ነው" በማለት ጠንከር ያለ ተቃውሞ አሰምተዋል።

    ባለፉት ሦስት ቀናት የአሜሪካንን እርምጃ በተከታታይ ስታወግዝ የነበረችው ቻይና ዛሬም የትራምፕን ውሳኔ "ግድየለሽ" በማለት ተቃውማዋለች።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው "ከቀጣናው አገራት ጋር በጋራ የአካባቢውን ሰላም እና መረጋጋት ለመጠበቅ" እንደምትሠራ ተናግረዋል።

    ባለፈው ቅዳሜ ከመኖሪያቸው ከሚስተቻው ጋር ተይዘው ሰኞ ዕለት አሜሪካ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የቻይና ወዳጅ ናቸው።

  19. የአሜሪካ መንግሥት በቬንዙዌላ ነዳጅ ላይ ከኩባንያዎች ጋር ንግግር ጀመረ

    የነዳጅ ማውቻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን በቬንዙዌላ የነዳጅ ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ንግግር እየተካሄደ መሆኑን ለቱርክ የዜና ወኪል፣ አናዶሉ ተናገሩ።

    የአሜሪካ መንግሥትን በመወከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እና የኤነርጂ ሚኒስትሩ ክሪስ ራይት ውይይቱን እየመሩት መሆናቸውን የገለጹት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ባለሥልጣን፤ ነገር ግን የትኞቹ ኩባንያዎች ተሳተፊ እንደሆኑ ከመናገር ተቆጥበዋል።

    “ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቬንዙዌላ ውስጥ ስላሉት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ከአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያዎች ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል" በማለት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

    የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሽግግር እስኪካሄድ ድረስ አሜሪካ አገሪቱን እንደምትመራ እና የነዳጅ ተቋማቷን በመጠገን ሥራቸውን እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።

    “በዓለም ላይ የትም ቦታ ላይ የሌሉ የአሜሪካ ግዙፍ ነዳጅ አምራች ኩባንያዎች ወደ ቬጀንዙዌላ ገብተው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማውጣት በከፍተኛ ደረጃ የተበላሹትን የአገሪቱን የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ይጠግናሉ” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

  20. የኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንኖች ይዘውት በታየው ካርታ ላይ የኤርትራ ተቃውሞ

    የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ባለፈው ሳምንት ማብቂያ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ይዘውት በታየው ካርታ ምክንያት ኤርትራ ኢትዮጵያ ላይ ተቃውሞዋን አሰማች።

    የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል የወጣውን ካርታ ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አሰብ እና አካባቢውን ወደ ኢትዮጵያ የሚያካትተው ካርታ "ትኩረት ለመሳብ" የሚደረግ ከመሆኑ በተጨማሪ "ጠብ ጫሪነት ነው" ብለዋል።

    ስለ ፎቶው የተጠየቁት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄነራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን “መውጣት አልነበረበትም” ሲሉ በስህተት የተለጠፈ መሆኑን እንደገለጹ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

    “ፎቶው የተቋሙ አይደለም፤ በተቋም የተሰጠ አቅጣጫ” እንዳልሆነ የተናገሩት ሜጀር ጄነራል እንዳልካቸው፤ በግለሰቦች “ተነሳሽነት” የተፈጸመ እንደሆነ አስረድተዋል።

    ዕሁድ ዕለት በተካሄደ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ምረቃ ላይ ከፍተኛ መኮንኖች ይዘውት የታየው እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተሠራጭቶ የነበረው ምሥል እንዲነሳ ተደርጓል።

    ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከ30 ዓመታት በፊት አገሪቱ ያጣችውን የባሕር በር መልሳ ማግኘት አለባት የሚል አቋም በስፋት እያራመዱ በሚገኙበት ጊዜ ነው ካርታው በወታደራዊ ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የታየው።

    የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር ለዚህ በሰጡት ምላሽ "የኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት በ2026 አዲስ ዓመት ጅማሬ ግድየለሽ ጠብ ጫሪነት እና በጦርነት አጀንዳ ተጠምደዋል" ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

    ኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የራሷ የሆነ የባሕር በር የማግኘት አጀንዳን በማንሳት በተለያዩ መልኮች ጥረት እያደረገች መሆኗን አሳውቃለች። ባለሥልጣናቱም አገሪቱ ያላግባብ አጣችው ያሉትን የባሕር በር መልሳ እንደምታገኝ በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነው።

    አቶ የማነ ይህንን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፍላጎትን "ግድየለሽ እና አደገኛ" በማለት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ሐሰተኛ መረጃን በማሠራጨት ከስሰዋል።

    ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች የይገባናል ጥያቄ እያነሳችበት ያለው የአሰብ ወደብ ኤርትራ ነጻ አገር አስከ ሆነችበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ዋነኛው የባሕር በር አገልግሎት ይሰጥ ነበር።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ወደብ ለማግኘት ብላ በኤርትራ ላይ ጦርነት የመክፈት ዕቅድ የሌላት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር ማግኘት ግን "የኅልውና ጉዳይ ነው" ማለታቸው ይታወቃል።