የየመኑ ተገንጣይ ቡድን መሪ 'በሶማሊያ በኩል ወደ አቡዳቢ ሸሽቷል' መባሉን ተከትሎ ሞቃዲሾ ምርመራ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, X
የሶማሊያ የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ የደቡብ የመን ሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባይዲ የአየር ክልሏን ያለፈቃድ ተጠቅሟል መባሉን ተከትሎ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።
የኢሚግሬሽንና የዜግነት ኤጀንሲ (አይሲኤ) ሐሙስ ታሕሳስ 30 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ የአየር ክልልና የአውሮፕላን ማረፊያዎች የአገሪቱን ሕግ ወይም ፈቃድ በመጣስ የ"ተፈላጊ ፖለቲከኛ"ን ጉዞን ለማመቻቸት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ከሌሎች አገራት ባለሥልጣናት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የተገንጣይ ቡድኑ መሪ በጀልባ ወደ በርበራ ካመራ በኋላ በሞቃዲሹ በኩል ወደ አቡዳቢ መሄዱን ዘግቧል።
የዜና ወኪሉ በየመን በሳዑዲ አረቢያ የሚመራውን ጥምረት ጠቅሶ እንደዘገበው የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባይዲ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በሶማሊላንድ በኩል አድርጎ አምልጧል።
የአማፂ ቡድኑ መሪ ያመለጠው በሪያድ የሰላም ንግግር ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እያለ ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ ዩኤኢ ከአገር እንዲወጣ ረድታዋለች በማለት ወቅሳለች።
የሶማሊያ መንግሥት ግን አይዳረስ አል ዙባይዲ በጀልባ ወደ ሶማሊላንድ ስለማምራቱ የጠቀሰው ነገር የለም።
የሶማሊያ የኢሚግሬሽን ኤጀንሲ ዙባይዲ በሞቃዲሾ የአየር ክልል በኩል መውጣቱ ከተረጋገጠ፣ እርምጃዎቹ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የኢሚግሬሽን ሕጎች ላይ ከባድ ጥሰት መፈፀማቸውን እንደሚያመለክቱ ተናግሯል።
ተፈላጊ ሰዎችን ማዘዋወር ወይም ያለ ፈቃድ በግዛቱ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም የተናጠል እንቅስቃሴዎችን ማመቻቸት “ተቀባይነት የሌለው” መሆኑን አፅንዖት ሰጥቷል።
ሐሙስ ዕለት ሳዑዲ አረቢያ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን የየመን ተገንጣይ ቡድን መሪ የሆነው እና በአገር ክህደት ወንጀል የሚፈለግ ግለሰብን ከአገር ወጥቶ ወደ አቡዳቢ እንዲሸሽ በማድረግ ወንጅላታለች።
የሳዑዲ መከላከያ የደቡብ የመን የሽግግር ምክር ቤት መሪ አይዳረስ አል ዙባዲ ከየመን በጀልባ ወደ ሶማሊያ መሸሹን ተናግሮ ነበር።
ሞቃዲሾ ሳዑዲ አረቢያ በየመን ያለውን ሁኔታ ለመፍታት በሪያድ ለመወያየት ያቀረበችውን ጥሪ “ተገቢ የፖለቲካ ሂደት” እንደሆነ በመግለጽ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
ኤጀንሲው አል ዙባይዲ “ይህንን ሂደት ለማምለጥ፣ የውጭ ድጋፍ በማግኘት ጭምር፣ የሚያደርገው ማንኛውም ጥረት ቀጣይነት ያለውን የዲፕሎማሲ ጥረት በቀጥታ የሚቃረን ይሆናል” ሲል አክሏል።
ጥሰት መፈጸሙ ከተረጋገጠ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እና የዓለም አቀፍ ሕግን መጣስን እንደሚያመለክት ኤጀንሲው ጨምሮ አስጠንቅቋል።
ኤጀንሲው “በምርመራው ግኝቶች ላይ በመመስረት ጥሰቶች መኖራቸው ከተረጋገጠ ሙሉ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ተገቢ እርምጃዎች ይወሰዳሉ” ብሏል።





















