
የፎቶው ባለመብት, NewsNation
በፖርትላንድ ኦሪገን የአሜሪካ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው ሁለት ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የከተማዋ የፖሊስ መምሪያ በሰጠው መግለጫ አንድ ወንድና አንድ ሴት ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ እና ሁኔታቸው እንደማይታወቅ አስታውቋል።
የአገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ (ዲኤችኤስ) ክስተቱ አንድ የቬንዙዌላ ወሮበላ ቡድን አባል በመኪናው የጸጥታ ኃይሎችን “ለመግጨት ሲሞከር” መፈጠሩን ተናግሯል።
በሚኒያፖሊስ አንድ የፌዴራል የጸጥታ ኃይል አንዲት ሴትን መግደሉን ተከትሎ በአሜሪካ ከተሞች ውስጥ የፌዴራል የሕግ አስከባሪ ተግባራትን በመቃወም ተቃውሞ መከሰቱን ተከትሎ ያጋጠመ ክስተት መሆኑ ታውቋል።
"የመኪናው ተሳፋሪ እና ዒላማው የተደረገው ግለሰብ ዴ አራጓ ከተሰኘው ቡድን ጋር ግንኙነት ያለው እና በቅርቡ በፖርትላንድ በተፈፀመ የተኩስ ልውውጥ የተሳተፈ ሕገወጥ የቬንዙዌላ ዜጋ ነው" ሲል ዲኤችኤስ በኤክስ ላይ በለጠፈው መግለጫ አስታውቋል።
“የሕግ አስከባሪዎች ለተሽከርካሪው ተሳፋሪ ማንነታቸውን ሲገልጹ፣ አሽከርካሪው ተሽከርካሪውን እንደጦር መሳሪያ በመጠቀም የሕግ አስከባሪ ወኪሎቹን ለመግደል ሞክሯል።”
“አንድ የጸጥታ ኃይል ለህይወቱ እና ለደህንነቱ በመስጋት ጥይት ተኩሷል። አሽከርካሪው ከተሳፋሪው ጋር መኪናውን በመጠቀም ከቦታው ሸሽተው ሄደዋል።
የፖርትላንድ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ፖሊሶቻቸው በጉዳዩ ውስጥ እንዳልተሳተፉ እና የተኩስ ሪፖርቶችን ከተቀበሉ በኋላ መሰማራታቸውን ገልጿል።
በጥይት የተመቱት ሁለት ሰዎች ማንነት አልታወቀም። ፖሊስም ከተኩሱ ቦታ ርቀው መገኘታቸውን አስታውቋል።
"ፖሊሶች ወደ ሆስፒታል ከመወሰዳቸው በፊት የአደጋ ጊዜ የሕክምና ባለሙያዎችን ጠርቷል” ሲል መግለጫው አክሎ “ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም" ሲል ገልጿል።
የአሜሪካ ሚዲያዎች የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ በጥይት የተመቱት የተጋቡ ጥንዶች ናቸው።
የፖርትላንድ ዲስትሪክት አቃቤ ሕግ ናታን ቫስኬዝ በተኩሱ ስፈራ የተገኙት "ለመከታተል፣ ለመርዳት እና ጥልቅ እና የተሟላ ምርመራ መኖሩን ለማረጋገጥ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"ማስረጃዎች ሙሉ በሙሉ የተጠበቁ መሆኑን እና ስለተከሰተው ነገር ሁሉንም እውነታዎች ማግኘት እንደምንችል አረጋግጣለው” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ይህ አስተያየት የተሰጠው በሚኒሶታ የሚገኙ ባለሥልጣናት ኤፍቢአይ የአካባቢውን መርማሪዎች እንደማያካትት ካሳወቁ በኋላ ነው። ረቡዕ ዕለት ሬኔ ኒኮል ጉድ ፖሊሶችን ለመግጨት ሞክራለች በሚል በጥይት መገደሏ ይታወቃል።
“ስለጉዳዩ ለማወቅ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ነን" ሲሉ የፖርትላንድ ፖሊስ አዛዥ ቦብ ዴይ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።
"በሚኒያፖሊስ በተፈፀመው ተኩስ ምክንያት ብዙዎች የሚሰማቸውን ከፍተኛ ስሜት እና ውጥረት እንረዳለን፣ ነገር ግን የበለጠ ለማወቅ እስክሠራ ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ እጠይቃለሁ።"
በሃዘልዉድ የተከሰተውን አጋጣሚ የተመለከተው ምርመራ በኤፍቢአይ በበላይነት እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል።
የፖርትላንድ ከንቲባ ኪት ዊልሰን በበኩላቸው የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስከባሪ አባላት (አይስ) ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በከተማው ውስጥ ያላቸውን ሁሉንም ሥራዎች እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም "አስተዳደሩ እኛን ለመከፋፈል፣ ማህበረሰቦችን እርስ በእርስ ለማጋጨት እየሞከረ ነው። ፖርትላንድ፣ ይህ እርስ በርስ ለመተሳሰር የሚያስችለን ጊዜ ነው” ብልዋል።
ፖርትላንድ ቀደም ሲል ትላልቅ የፀረ-ትራምፕ ተቃውሞዎች የተካሄዱበት ቦታ ነበረች።
ረቡዕ ምሽት የፖርትላንድ ፖሊስ አንድ ተቃዋሚ በቢላዋ ሌላ ግለሰብን ሲያስፈራራ ካገኙት በኋላ በቁጥጥር ስር አውለውታል።
ዴሞክራቱ ሴናተር ሉው ፍሬድሪክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ሐሙስ በተፈጸመው የተኩስ ምርመራ ውስጥ የማይሳተፉ ከሆነ "ማህበረሰቡ ውጤቶች ገለልተኛ አይደሉም በማለት ማመን አይችልም" ብለዋል።
"ለብዙ ሳምንታት ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን እና በመንገድ ላይ ውጥረት የነገሰባቸው ሁኔታዎች ግልጽ ሆነዋል" ሲሉ በትራምፕ አስተዳደር ላይ በከተማው ውስጥ እየተካሄዱ ያሉትን ተቃውሞዎች በመጥቀስ ተናግረዋል።
"የሚያሳዝን ሁኔታ፣ የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ ቀድሞም የሚታይ ይመስለኛል" ብለዋል።