ሕንድ ከ16 ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያን ለማገድ እያጤነች ነው

ስልክ ላይ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን መተግበሪያ የሚመለከት ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለሙያዎች እንደሚሉት በሕንድ ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያን ማገድ ሕጋዊ ተግዳሮት ሊገጥመው ስለሚችል ቀላል አይሆንም
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በሕንድ ከ16 ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያን በማገድ ዙሪያ ክርክሮች እየተካሄዱ ሲሆን የበርካታ ግዛቶች ሚኒስትሮች በቅርቡ በአውስትራሊያ ተግባራዊ የሆነውን ሕግ እያጤኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

በቅርቡ በደቡባዊ ግዛት የሚገኙ ቢያንስ ሁለት ሚኒስትሮች እገዳው ሕፃናትን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማራቅ ውጤታማ እንደሆነ እየፈተሹ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት በሕንድ የምጣኔ ሃብት አማካሪ በተመራ ቡድን የተሰራ ዓመታዊ የምጣኔ ሃብት ዳሰሳ የፌደራል መንግሥት ሕፃናት የሚጠቀሟቸውን ማኅበራዊ ሚዲያዎች በእድሜ ክልል እንዲገድብ መክሯል።

የዳሰሳ ጥናቱ ምክር ሃሳብ ግን የመንግሥትን ሃሳብ ያላካተተ ቢሆንም የፖሊሲ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ ነው።

ሆኖም ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነት እገዳ በሕንድ ቀላል እንደማይሆን እና ሕጋዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በቅርቡ አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያን በማገድ ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።

በዚህ ሕግ መሠረት ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ የተጠቃሚዎችን የእድሜ ክልል ማረጋገጥ የሚገባቸው ሲሆን ከተቀመጠው የእድሜ ክልል በታች ያሉ ተጠቃሚዎች ገጾችን እንዲዘጉ ያስገድዳል።

እርምጃው በርካታ ትችቶችን ያስተናገደ ሲሆን የአውስትራሊያ የበይነ መረብ ተቆጣጣሪ እርምጃው የተወሰደው "በፍላጎት ላይ ያልተመሰረተ እና በቸልተኝነት" ነው ሲሉ ባለፈው ወር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፈረንሳይ የታችኛው ምክር ቤት ሕግ አውጭዎችም ባለፈው ሳምንት ከ15 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን ከማኅበራዊ ሚዲያ የሚያግድ ረቂቅ ሕግ አፅድቀዋል። ሆኖም ረቂቅ ሕጉ በምክር ቤቱ አባላት መጽደቅ ይጠበቅበታል።

ዩናይትድ ኪንግደምም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እያሰበች ነው።

በሕንድ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲታገድ ሃሳብ ያቀረቡት አንድህራ ፕራዳሽ ግዛትን የሚያስተዳድረው ቴሉጉ ዲሳም ፓርቲ ሕግ አውጭ የሆኑት ልስክ ዲቫራያሉ ናቸው።

ሃሳቡ የመንግሥትን ፖሊሲ እና ሕግ ሊሆን የማይችልበትን እድል ያላንፀባረቀ ቢሆንም ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የሚያደርገውን ክርክር መልክ ያስይዛል ተብሏል።

በሌላ በኩል የአንድራህ ፕራዲሽ መንግሥት ዓለም አቀፍ ማዕቀፎችን የሚያጠኑ የሚኒስትሮች ቡድን ያቋቋመ ሲሆን ኤክስን የሚያስተዳድረው ሜታ፣ ጉግልን እና ሸርቻትን ጨምሮ በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ለምክክር ጋብዟል። የማኅበራዊ ሚዲያ ድርጅቶቹ የምክክር ግብዣው ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።

የግዛቷ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የሆኑት ናራ ሎክሽ ባለፈው ሳምንት በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "ሕፃናት ግድየለሽ ለሆነ አጠቃቀም ተትተዋል፤ ይህም ትኩረት የሚሰጡበትን ጊዜ እና ትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል" ብለዋል።

" ማኅበራዊ ሚዲያዎች ደኅንነቱ የተጠበቀ እና በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት አነስተኛ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን" ሲሉም አክለዋል።

ሌሎች ግዛቶችም ተመሳሳይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ፍላጎት አሳይተዋል።

ሆኖም በቅርቡ በአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት በተጠና ጥናት ውስጥ የተካተቱ 1 ሺህ 277 ታዳጊ ሕንዳውያን እድሜን መሠረት ያደረገ ገደብ እና ይህንን የማረጋገጫ ሥርዓት በአገሪቷ የዲጂታል ምሕዳር ላይ ተጨማሪ ፈተናዎችን ሊያስከትል እንደሚችል አመልክተዋል።

በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የተከፈቱት በቤተሰብ አባላት እርዳታ ወይም ጓደኞች በመሆናቸው እና ከተጠቃሚዎቹ የኢሜይል አድራሻ ጋር የማይገናኙ በመሆናቸው ባለቤትነትን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብሏል ጥናቱ።

የተወሰኑ ወላጆች ግን የእገዳውን ሃሳብ በመልካም ተቀብለውታል። ሌሎች ደግሞ ጥልቅ የሆኑ ጉዳዮችን አንስተዋል።

ከስምንት ዓመት በታች የሆኑ ሁለት ልጆች ያሏቸው የደልሒ ነዋሪ ጂትንደር ያዳቭ " ወላጆች ራሳቸው ለልጆቻቸው በቂ ጊዜ አይሰጡም። ልጆች በሆነ ነገር እንዲጠመዱ ስልክ ነው የሚሰጧቸው። ችግሩ የሚጀምረውም እዚህ ላይ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም የማኅበራዊ ሚዲያ እገዳው ይረዳል ብለው እንደማያስቡ ነዋሪዋ ገልጸዋል።

" ወላለጆች ለልጆቻቸው በቂ ጊዜ ካልሰጡ አሊያም ፈጠራ በተሞላበት ነገር እንዲጠመዱ ማድረግ ካልቻሉ በስተቀር እንዲህ ዓይነት እገዳዎችን ማለፍ የሚችሉበትን መንገድ ሁልጊዜም መፈለጋቸው አይቀርም" ብለዋል።