በምያንማር የወንጀል ካምፖች ባለቤት የሆነው ቤተሰብ 11 አባላት ሞት ተፈረደባቸው

ሚንግ የተባለው ቤተሰብ በርካታ አባላት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

የፎቶው ባለመብት, CCTV

የምስሉ መግለጫ, ሚንግ የተባለው ቤተሰብ በርካታ አባላት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

በምያንማር የወንጀል ካምፕ የሚመራ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 11 ሰዎች ሞት ተፈረደባቸው።

የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው፣ ሚንግ የተባለው ቤተሰብ በርካታ አባላት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። አብዛኞቹም የዓመታት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

'ሚንግ ፋሚሊ' የተባለው ቤተሰብ በምያንማር ራስ ገዝ አስተዳደር ሥር የምትገኘውን ላውካይንግ ከተማ ከሚያስተዳድሩ አራት ጎሳዎች መካከል ይገኝበታል።

በቻይና ድንበር ላይ በሚገኘው በዚህ ከተማ የወንጀል ካምፖች ከፍተዋል። በእነዚህ ካምፖች ቁማር፣ የበይረ መረብ ማጭበርበር እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ይከናወናል።

ምያንማር እአአ በ2023 የቤተሰቡን አባላት በቁጥጥር ሥር በማዋል ለቻይና አስተላልፋ ሰጥታለች።

ሲሲቲቪ እንደዘገበው፤ በዌንዦው ከተማ ፍርድ ቤት ውሳኔ ያሳለፈው በ39 የቤተሰቡ አባላት ላይ ነው።

11 የቤተሰቡ አባላት ሞት ሲፈረድባቸው ሌሎች 11 የሚሆኑት የዕድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዋል። የተቀሩት ከአምስት ዓመት እስከ 24 ዓመታት እንዲታሰሩ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።

ከ2015 ጀምሮ የሚንግ ቤተሰብ እና ሌሎች የወንጀል ቡድኖች ከመገናኛ መስመሮች (ቴሌኮሚዩኒኬሽን) ጋር የተያያዘ ማጭበርበር፣ ሕገ ወጥ ቁማር፣ የወሲብ ንግድ እንዲሁም የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቁማር እና በማጭበርበር 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንዳገኙ በፍርድ ቤት ተገልጿል።

አራቱ ቤተሰቦች የከፈቷቸው የቁማር ቤቶች በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላሮችን ያስገኙ ነበር።

በወንጀል ካምፖች ከታገቱ ሠራተኞች ሞት እንዲሁም ሠራተኞች ወደ ቻይና እንዳይገቡ ተኩሶ ከመግደል ጋር በተያያዘም ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ቁማር ሕገ ወጥ በሆነባት ቻይና ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ተገን በማድረግ የቁማር ቤቶችን በመክፈት በወንጀል ድርጊቱ እንደተሰማሩ ተገልጿል።

በእነዚህ ቁማር ቤቶች ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር የማስገባት ድርጊት እና የበይነ መረብ ምዝበራ ካምፖችን መክፈት ውስጥም እጃቸው አለበት።

የተባበሩት መንግሥታት የውጭ አገራት ዜጎችን ያሳተፈ የበይነ መረብ ምዝበራ ወንጀል ሰንሰለት (scamdemic) ዋነኛ ማዕከል ሲል ላውካይንግ ከተማ ነች ሲል ፈርጇል።

ቻይናውያንን ጨምሮ ከ100,000 በላይ የውጭ አገራት ዜጎች በእነዚህ የወንጀል ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙም ድርጅቱ አስታውቋል።

ሠራተኞቹ ታግተው ለረዥም ሰዓታት እንዲሠሩ ይገደዳሉ። በመላው ዓለም በበይነ መረብ እንዲያጭበረብሩም ይገደዳሉ።

በምያንማር ኃያል የሆነው የሚንግ ቤተሰብ ቢያንስ 10,000 ሠራተኞች የያዙ የወንጀል ካምፖች አሉት።

'ታይገር ቪላ' በመባል በሚታወቀው የወንጀል ካምፕ ውስጥ ሠራተኞች ይደበደባሉ እንዲሁም ስቅይት ይፈጸምባቸዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ታጣቂ ቡድኖች የከፈቱት ጥቃት የምያንማር ወታደሮች ወደ ሻን ግዛት እንዲሸሹ ምክንያት ሆኗል።

በእነዚህ ቡድኖች ላይ ጫና የምታሳድረው ቻይና ጥቃቱ እንዲፈጸም መፍቀዷ ይነገራል።

የሚንግ ቤተሰብ መሪ ሚንግ ዡንቻንግ ራሱን እንዳጠፋ ተዘግቧል። ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ደግሞ ለቻይና ተላልፈው ተሰጥተዋል። ድርጊታቸውን መናዘዛቸውም ተገልጿል።

በወንጀል ካምፖቹ ይሠሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ለቻይና መንግሥት መሰጠታቸው ተዘግቧል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቻይና የወንጀል ካምፖች ላይ ጥብቅ እርምጃ ለመውሰድ ቆርጣ መነሳቷን ጠቋሚ ነው ተብሏል።

ታይላንድም የወንጀል ካምፖች ላይ እርምጃ እንድትወስድ በማድረግ የቻይና ሚና ጉልህ ነው።

ሆኖም ግን የወንጀል ካምፖች አሁንም ድረስ በምያንማር እንዲሁም በካምቦዲያም ተስፋፍተዋል።