መስክ በአሜሪካ ወሳኝ ግዛቶች ለተመዘገቡ መራጮች በየቀኑ 1 ሚሊዮን ዶላር በዕጣ መስጠት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የትራምፕ ደጋፊው ቢሊየነሩ ኤለን መስክ በአሜሪካ ምርጫ ወሳኝ ግዛቶች ለተመዘገቡ መራጮች በየቀኑ 1 ሚሊዮን ዶላር በዕጣ መልክ መስጠት ጀመረ።
የፕሬዚዳንታዊውን ምርጫ በሚወስኑ የአሜሪካ ግዛቶች የሚደረገው ይህ ዕጣ እስከ ምርጫው ዕለት ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. በየቀኑ የሚደረግ ነው ብሏል።
አሸናፊው/ዋ የሪፐብሊካን ዕጩ የሆኑትን ዶናልድ ትራምፕን ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ ባቋቋመው አሜሪካ ፓክ የተሰኘው የምርጫ ዘመቻ ድርጅት የጀመረውን ለሕገመንግሥቱ ድጋፍ የማሰባሰብ ፊርማ ከሚፈርሙት መካከል በዘፈቀደ የሚመረጥ ይሆናል።
የመጀመሪያው ሎተሪ መሳይ ዕጣ ቅዳሜ ማታ በፔንስልቬንያ ከተማ በተካሄደው የስብሰባ ማዕከል ዝግጅት ላይ አንድ ግለሰብ አሸናፊ መሆኑ ተነግሯል። በቀጣዩ ቀን እሁድም የአንድ ሚሊዮን ዶላር ቼክ ለሌላ ግለሰብ ተሰጥቷል።
ሌላኛዋ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የሆኑትን ካማላ ሃሪስን የሚደግፉት የፔንስልቫንያ ገዥ ጆሽ ሻፒሮ የቢሊየነሩን ስትራቴጂ “በጥልቅ የሚያሳስብ” ብለውታል።
ሻፒሮ አክለውም የሕግ አስከባሪ አካላት እነዚህ ክፍያዎችን ሊያዩዋቸው እንደሚገባ ለኤንቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።
ዕጣው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን የሚወስኑት እና ቁልፍ በተሰኙት ፔንስልቫንያ፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ሚቺጋን እና ሰሜን ካሮላይና ግዛቶች የመስክን የፊርማ ማሰባሰብ ላይ ለፈረሙ መራጮች ነው።
የምርጫ ሕግ ባለሙያ የሆኑት ሪክ ሃሰን መስክ ያቀረበው ዕጣ “ግልጽ በሆነ መንገድ ሕገወጥ” ነው ብለው እንደሚያምኑ ጽሁፋቸውን አስፍረዋል።
የአገሪቱ ፌደራል ሕግ ማንኛውም ሰው “ለመራጭነት እንዲመዘገብም ሆነ ድምጽ እንዲሰጥ ክፍያ የከፈለ ወይም ለመክፈል ሃሳብ ያቀረበ፣ ወይም ክፍያ የተቀበለ” 10 ሺህ ዶላር ወይም የአምስት ዓመት እስራት ቅጣት እንደሚጠብቀው ያትታል።
መስክ መራጮች በቅጽ ላይ ፊርማቸውን እንዲያስቀምጡ ብቻ ቢጠይቅም ባለሙያው ከዚህ ጀርባ ያለውን ዓላማ ጥያቄ ውስጥ ከተውታል።
“በነዚህ ቅጾች ላይ መፈረም የሚችለው ማን ነው? በወሳኝ ግዛቶች ላይ የተመዘገቡ መራጮች ብቻ መሆናቸው ሕገወጥ ያደርገዋል” ሲሉ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሪክ ሃሰን ያስረዳሉ።
በነጻነት የመናገር እና የጦር መሳሪያ የመያዝ መብትን ለመደገፍ ቃል በመግባት ፊርማቸውን የሚያስቀምጡት እነዚህ መራጮች ስለምርጫው ውጤት ለማወቅ አድራሻዎቻቸውን ማስፈር አለባቸው።
የቴስላ፣ ስፔስኤክስ መሥራች እና የኤክስ (ትዊተር) ባለቤት ቢሊየነሩ ኤለን መስክ እንዲሁም አሜሪካ ፓክ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
የምርጫ ዘመቻን የሚመሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ፊርማዎችን በማሰባሰብ፣ የዳሰሳ ጥናት፣ እና የእቃ ግዢዎችን የመራጮችን የመረጃ ቋቶችን ለመገንባት የሚጠቀሙበት ታክቲክ ነው።
እነዚህ መረጃዎች በገንዘብም ይሁን በሌሎች መንገዶች ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥቅም ላይ ይውላሉ።
መስክ በፔንስልቪንያ ግዛት በፊርማ ማሰባሰቡ ላይ ፊርማቸውን ለሚያኖሩ መራጮች 100 ዶላር እንዲሁም ሌሎች ፈራሚዎችን ለሚያመጡ 100 ዶላር እየሰጠ ይገኛል።
ማንኛውም ሰው እንዲመርጥ በቀጥታ ካለመክፈሉ ጋር ተያይዞ የመስክ ስልት በአሜሪካ የምርጫ ሕግ ክፍተትን ሊሸፈን ይችላል ተብሏል።
በአሜሪካ ሕግ መራጮች አንድን ሰው እንዲመርጡ ብቻ ሳይሆን በምርጫ ድምጽ በመስጠት እንዲሳተፉ ገንዘብ መክፈል ሕጋዊ አይደለም።
ቢሊየነሩ መስክ ለትራምፕ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚል ነበር አሜሪካ ፓክ የተሰኘውን የዘመቻ ድርጅት በሐምሌ ወር የመሠረተው።
በትራምፕ ምርጫ ዋነኛ ተዋናይ ለሆነው ለዚህ ድርጅት መስክ እስካሁን 75 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል።












