ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመራማሪዎች በሰው ልጅ ዓይን ታይቶ የማያውቅ "አዲስ ቀለም" ማግኘታቸውን ይፋ አደረጉ
የዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ተመራማሪዎች የሰው ልጅ ዓይን አይቶት የማያውቅ አዲስ ቀለም ማግኘታቸውን ይፋ አደረጉ።
"ኦሎ" ሲሉ የጠሩት የቀለም ዓይነት በሰው ልጅ ዓይን ታይቶ አይታወቅም ይበሉ እንጂ ሌሎች ምሁራን ግን ግኝቱን "አከካሪ" ሲሉ ገልጸውታል።
ተመራማሪዎቹ ይህንን አዲስ የቀለም ዓይነት ያገኙት የዓይናችንን ምስል መቀበያ ሬቲና በተለየ ቴክኒክ በማነቃቃት እንደሆነ ተናግረዋል።
ተመራማሪዎቹ ባደረጉት ሙከራ በሬቲና ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ሴሎችን በማነቃቃት ሰማያዊ እና አረንጓዴ ቀለሞችን ማየት መቻላቸውን ቢናገሩም፣ ሌሎች ደግሞ አዲስ ቀለም ስለመሆኑ "ገና አከራካሪ ነው" በማለት ሞግተዋል።
የዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ፕሮፌሰር የሆኑት እና የጥናቱ ተባባሪ ሬን ንግ አርብ ዕለት በሳይንስ አድቫንስ ጆርናል ላይ የታተመው ይህ ግኝታቸውን "አስደናቂ" ሲሉ ጠርተውታል።
ፕሮፌሰሩ እና ባልደረቦቻቸው ውጤቱ ቀለም መለየት ለሚቸገሩ (colour blindness) ሰዎች ላይ ለሚደረገው ተጨማሪ ምርምር ሊያገለግል እንደሚችል ያምናሉ።
በሙከራው ከተሳተፉት አምስት ተመራማሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤንጂ ቅዳሜ ለቢቢሲ ራዲዮ 4 ቱዴይ ፕሮግራም እንደተናገሩት ኦሎ "በገሃዱ ዓለም ከምታዩት ከማንኛውም ዓይነት ቀለም የበለጠ ይደምቃል" ብለዋል።
"በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ከቦታ ቦታ ትዘዋወራለህ እንበል። እና ሮዝ ፣ ፈዛዛ ሮዝ ፣ ደብዘዝ ያለ ሮዝ ብቻ ታያለህ፤ ከዚያም አንድ ቀን ወደ ቢሮ ስትሄድ አንድ ሰው ሸሚዝ ለብሷል። እና እስካሁን ካየሃቸው በጣም ደማቅ ሮዝ ቀለም ነው። እና አዲስ ቀለም ነው። ያንንም ቀይ ብለን እንጠራዋለን" ብለዋል።
ቡድኑ ሙከራ በሚያደርግበት ወቅት ተመራማሪዎች በእያንዳንዱ ተሳታፊ ዓይን ላይ የሌዘር ጨረር መልቀቃቸውን ተናግረዋል።
በጥናቱ ውስጥ አምስት ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን፣ ሁሉም መደበኛ የቀለም እይታ ነበራቸው ተብሏል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ሦስቱ፣ ፕሮፌሰር ንግን ጨምሮ የጥናት ወረቀቱ ተባባሪ ጸሐፊዎች ነበሩ።
በጥናት ወረቀቱ መሰረት ተሳታፊዎቹ መስታወት፣ የሌዘር ጨረር እና ኦፕቲካል መሳሪያዎችን ያካተተ ኦዚ የተባለ መሳሪያ ተመልክተዋል።
መሳሪያዎቹ በዩሲ በርክሌይ እና የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ቡድን የተሠራ ሲሆን በዚህ ጥናት ጥቅም ላይ እንዲውል መሻሻሎች ተደርጎበታል።
ሬቲና በዓይን ጀርባ የሚገኝ እና የእይታ መረጃን በመቀበል እና በማቀናበር ኃላፊነት የሚወስድ የሕብረ ሕዋስ ንብርብር ነው።
ብርሃንን ወደ ኤሌክትሪካዊ ምልክቶች ከቀየረ በኋላ በኦፕቲክ ነርቭ አማካኝነት መልዕክቱ ወደ አንጎል እንዲተላለፍ በማድረግ ማየት ያስችለናል።
ሬቲና ቀለምን መለየት የሚያስችሉ የኮን ሴሎችን ይዟል።
በዓይን ውስጥ ሶስት ዓይነት የኮን ሴሎች አሉ።
እነዚህም ኤስ ፣ ኤል እና ኤም በመባል የሚታወቁ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው ለሰማያዊ፣ቀይ እና አረንጓዴ ሞገዶች ምላሽ ይሰጣሉ።
እንደ የምርምር ወረቀቱ ከሆነ በተለመደው እይታ "ማንኛውም የኤም ኮን ሴል የሚያነቃቃ ብርሃን ጎረቤቱን ኤል እና/ወይም ኤስ ኮንን ማነቃቃት አለበት" ምክንያቱም ተግባሩ ከነሱ ጋር ስለሚደራረብ ነው።
ይኹን እንጂ በጥናቱ ላይ ሌዘር ጨረሩ ኤም ኮንን ብቻ እንዲያነቃቃ ተደርጓል።
"በመርህ ደረጃ በተፈጥሮ እይታ ውስጥ ፈጽሞ የማይከሰት የቀለም ምልክትን ለአንጎል ይልካል" ሲል ጥናቱ ገልጿል።
ይህ ማለት ኦሎ የተሰኘው አዲሱ የቀለም ዓይነት ያለ ልዩ ማነቃቂያ እና እርዳታ በገሃዱ ዓለም በሰው ባዶ ዓይን ሊታይ አይችልም።
በሙከራው ወቅት የታየውን ቀለም እውነተኛነት ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ተሳታፊ ከኦሎ ጋር እስኪመሳሰል ድረስ ምልክት የሚያደርግበት መሳርያ ተገጥሞ ነበር።
አንዳንድ ባለሙያዎች ግን አዲሱ ተገኘ የተባለው ቀለም "የትርጉም ጉዳይ" ነው ይላሉ።
በጥናቱ ያልተሳተፉት የእይታ ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ጆን ባርቡር ጥናቱ "የቴክኖሎጂ ውጤት" ቢሆንም የተመረጡ የኮን ህዋሶችን በማነቃቃት አዲስ ቀለም መገኘቱ "ለክርክር ክፍት ነው" ብለዋል።
ለምሳሌ የቀይ ኮን ህዋሶች (ኤል) በብዛት ከተነቃቁ ሰዎች "ደማቅ ቀይ ማየታቸውን ይናገራሉ"
ነገር ግን የሚታሰበው ደማቅ ቀይ፣ በቀይ ኮን መነቃቃቶች ላይ ተመስርቶ ሊለወጥ እንደሚችል ተገልጿል። ይህም በዚህ ጥናት ውስጥ ከተከሰተው የተለየ አይደለም ብለዋል።
ነገር ግን የጥናቱ ተባባሪ ፕሮፌሰር ኤንጂ ምንም እንኳን ኦሎ "በእርግጠኝነት ለማየት በጣም አስቸጋሪ" ቢሆንም ቡድኑ ግኝቱ ቀለሞችን መለየት አስቸጋሪ ለሚሆንባቸው አንዳንድ ሰዎች ምን ማለት ነው የሚለው ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።