ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ ሉዓላዊ የፍልስጤም መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ትጥቅ እንደማይፈታ አስታወቀ
ሐማስ የፍልስጤም ሉዓላዊ መንግሥት ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማው አድርጎ እስካልተመሰረተ ድረስ ትጥቅ ለመፍታት እንደማይስማማ በድጋሚ አረጋገጠ።
ሐማስ ይህንን ያለው በጋዛ የተኩስ አቁም ድርድር ወቅት እስራኤል ካቀረበቻቸው ቁልፍ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ለሆነው በሰጠው ምላሽ ነው።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ሐማስ የጦር መሳሪያውን ለመፍታት "ፍላጎቱን ገልጿል" ሲሉ ለተናገሩት አስተያየት የተሰጠ ምላሽ ነው ብሏል።
እስራኤል የሐማስን ትጥቅ መፍታት ግጭቱን ለማስቆም ለሚደረገው ማንኛውም ስምምነት ቁልፍ ሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ አድርጋ ታቀርባለች።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ ሲደረግ የነበረው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ባለፈው ሳምንት ተቋርጧል።
ፈረንሳይ እና ካናዳን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት ለፍልስጤም ግዛት ዕውቅና ለመስጠት ማቀዳቸውን ካስታወቁ በኋላ ባለፉት ጥቂት ቀናት የአረብ መንግሥታት ሐማስ ትጥቅ እንዲፈታ አሳስበዋል።
እንግሊዝ እስከ መስከረም ድረስ እስራኤል አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን ካላሟላች ለፍልስጤም እውቅና እንደምትሰጥ ተናግራለች።
በአሜሪካ፣ በዩኬ እና በአውሮፓ ኅብረት በሽብርተኝነት የተመዘገበው ሐማስ በመግለጫው "ዋና ከተማዋን ኢየሩሳሌም ያደረገች ገለልተኛ እና ሙሉ በሙሉ ሉዓላዊ ፍልስጤም" እስካልተመሰረተች ድረስ "ትግሉን እና የጦር መሳሪያዎቹን" አሳልፎ እንደማይሰጥ ተናግሯል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ሌተናል ጀነራል ኢያል ዛሚር ትናንት አርብ በጋዛ ውስጥ በሐማስ የተያዙ ታጋቾችን በፍጥነት ለማስለቀቅ ድርድር ካልተሳካ ምንም ፋታ እንደማይኖር አስጠንቅቀዋል።
ቅዳሜ ዕለት በሐማስ የታገተው ኢቪያታር ዴቪድ ቤተሰቦች፣ ከላይ ራቁቱን ሆኖ ደካማ ብርሃን ባለው ዋሻ ውስጥ ሆኖ ቪዲዮ ከለቀቀ በኋላ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሐማስ ለፕሮፓጋንዳ ዘመቻው እንዳይጠቀምበት በሚል የጠየቁት ቤተሰቦቹ፣ እሱን ለማስለቀቅ የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርጉ የእስራኤል መንግሥት እና አሜሪካን ተማጽነዋል።
የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት በጋዛ እያሽቆለቆለ ባለው የሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጫና እየገጠመው ባለበት ወቅት ዊትኮፍ እስራኤልን ጎብኝተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች በጋዛ ውስጥ ሰው ሠራሽ የሆነ የጅምላ ረሃብ እንዳለ አስጠንቅቀዋል።
አክለውም ሁሉንም የእርዳታ አቅርቦቶች ወደ ጋዛ መግባቱን የምትቆጣጠረው እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል።
እስራኤል በእርዳታ አቅርቦት ላይ ምንም ገደብ እንደሌለ እና "ረሃብ የለም" ስትል ተናግራለች።
ቅዳሜ ዕለት ዊትኮፍ አሁንም በጋዛ ከሚገኙት የእስራኤል ታጋቾች ቤተሰቦች ጋር በቴል አቪቭ ተገናኝተዋል።
በይነመረብ ላይ የተለጠፈ ተንቀሳቃሽ ምስል የዋሽንግተን ተደራዳሪው ተቃውሞ በሚደረግበት አደባባይ ሲደርሱ የታጋቾቹ ቤተሰቦች ደጋፊዎች በጭብጨባ እርዳታ ሲማፀኑ ታይተዋል።
ዊትኮፍ የሰላም ጥረት ከከፊል ስምምነት ይልቅ ግጭቱን በማስቆም እና ታጋቾችን በሙሉ ወደ ቤት በማምጣት ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል።
እንደ የዊትኮፍ ጉዞ፣ ሐሙስ ዕለት ከኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው አርብ ዕለት በደቡባዊ ጋዛ በስፋት ትችት የሚቀርብበትን የእርዳታ ጣቢያ ጎበኝተዋል።
ከግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ ቢያንስ 1,373 ፍልስጤማውያን ምግብ ፍለጋ ወደ እርዳታ ጣቢያዎች ሲሄዱ መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የቅርብ ጊዜ አኃዛዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አብዛኞቹ በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፉ የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን (GHF) ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅራቢያ በእስራኤል ጦር ተገድለዋል ብሏል።
እስራኤል ሐማስን በእርዳታ ማከፋፊያዎቹ አቅራቢያ ብጥብጥ አስነስቷል በማለት የወነጀለች ሲሆን፣ ወታደሮቿ ሆን ብለው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ እንደማይከፍቱ ተናግራለች።