በኬንያ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ21 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በኬንያ ምዕራባዊ ክፍል ከባድ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ21 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።

የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙኮሜን በኤክስ ገፃቸው 30 ሰዎች በቤተሰቦቻቸው መጥፋታቸው ሪፖርት ከተደረጉ በኋላ እስካሁን እንዳልተገኙ ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ በአደጋው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 25 ሰዎች ደግሞ ለሕክምና በአውሮፕላን እንዲነሱ መደረጉን ተናግረዋል።

አርብ ምሽት በደረሰው አደጋ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስከሬንም በአውሮፕላን ወደሌላ ቦታ እንዲዛወር መደረጉን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሕይወት አድን ጥረቱን እየደገፈ ያለው የኬንያ ቀይ መስቀል በአደጋው ክፉኛ የተጎዱ አካባቢዎችን በመሬት መንሸራተት እና በደራሽ ጎርፍ ምክንያት እስካሁን ድረስ በመንገድ ተደራሽ እንዳልሆኑ አስታውቋል።

የኬንያ መንግሥት የሕይወት አድን ፍለጋ ተልዕኮውን ቅዳሜ ዕለት ገታ አድርጎ እሁድ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪፕቹምባ "ለተጎጂዎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "የወታደራዊ እና የፖሊስ ሂሊኮፕተሮች ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው" ብለዋል።

ኬንያ ሁለተኛው የዝናብ ወቅቷ ላይ የምትገኝ ስትሆን በጣም ዝናባማ ከሆነው ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዚህ ወቅት አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ለሳምንታት ብቻ ታስተናግዳለች።

የአገሪቱ መንግሥት በዝናባማ ወራት የሚሞሉ ወንዞች አቅራቢያ እና የመሬት መንሸራተት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎቹን ደኅንነት ወዳለው አካባቢ እንዲዛወሩ አርብ ዕለት አሳስቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኬንያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የኡጋንዳ አካባቢ ከረቡዕ ዕለት ጀምሮ በደረሰ ድንገተኛ ጎርፍ እና የመሬት መንቀጥቀጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ቅዳሜ ዕለት የኡጋንዳ ቀይ መስቀል አደጋው በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ካፕሶሞ አካባቢ መድረሱን እና አንድን ቤት እና ቤቱ ውስጥ የነበሩ አራት ሰዎችን ጠራርጎ መውሰዱን አስታውቋል።

ቀይ መስቀል የጎርፍ አደጋው በቡላምቡሊ አውራጃ የወንዝ ዳር አቅራቢያ የሚገኙ አብዛኞቹን መንደሮች ክፉኛ መጉዳቱንም ገልጿል።

ተቋሙ እንዳለው በአካባቢው በተከታታይ የዘነበው ከባድ ዝናብ ወንዞች ሞልተው እንዲፈሱ ማድረጉን ተከትሎ ሰፊ የመኖሪያ ቤት፣ የእርሻ እና የመሰረተ ልማት ውድመት አስከትሏል።