የዓለማችን ቱጃር ቢል ጌትስ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት አብዛኛውን ሀብቱን ሊያከፋፍል ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የማይክሮሶፍት መስራች የሆነው ቢል ጌትስ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ጠቅላላ ሀብቱን ለሌሎች ለመስጠት ማቀዱን አስታወቀ።
ጌትስ የሀብቱን 99 በመቶ፣ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በእርደታ ድርጅቱ በኩል ለመስጠት ማቀዱን ነው ይፋ ያደረገው።
ቢል ጌትስ ሀብቱን ለሌሎች የሚያከፋፍለው በፋወንዴሽኑ በኩል መሆኑን ገልጾ እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር በ2045 ሥራ እንደሚያቆም ተናግሯል።
"ስሞት ሰዎች ስለ እኔ ብዙ ነገር ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን እርግጠኛ የምሆነው 'ከእነ ሀብቱ ሞተ' የሚለው ከወሬያቸው መካከል እንደማይሆን ነው" ሲል ሐሙስ ዕለት በብሎጉ ላይ ለጽፏል።
የ69 ዓመቱ ጌትስ በስሙ ያቋቋመው ፋውንዴሽን እስካሁን ድረስ 100 ቢሊዮን ዶላር ለጤና እና ለልማት ፕሮጀክቶች መስጠቱን ገልጾ፣ በቀጣይ ሁለት አስርት ዓመታት እስከ 200 ቢሊዮን ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል ተንብይዋል።
ቢል ጌትስ በብሎጉ ላይ ታዋቂው አንድሪው ካርኒጌ በ1889 የሀብት ወንጌል ሲል በሰየመው ጽሑፉ ላይ ቱጃሮች ሀብታቸውን ለማኅበረሰቡ መልሰው የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው ማለቱን ጠቅሷል።
ጌትስ "ሀብታም እንደሆነ የሚሞት ሰው እርሱ ክብሩን ጥሏል" ሲል ካርኒጌ የጻፈውን ጠቅሷል።
ጌትስ በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በኩል ሀብቱን መስጠቱን እንደሚያቀላጥፍ ቃል ገብቷል።
ከዚህ በፊት እርሱ እና የቀድሞ ባለቤቱ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ሕይወታቸው ካለፈ በኋላም ለበርካታ አስርታት የበጎ አድራጎት ድርጅቱ እየሰራ እንዲዘልቅ ፍላጎት ነበራቸው።
ይህ የውሳኔ ለውጥ አንዴት እንደመጣ ሐሙስ ዕለት ቢቢሲ ኒውስ አወር ሲጠይቀው በሚቀጥሉት 20 ዓመት ውስጥ የወደፊቱን ተግዳሮቶች በተሻለ ሁኔታ መፍታት የሚችሉ ሌሎች ሀብታም ሰዎች ይኖራሉ ሲል መልሷል።
አክሎም " ለነገሮች ቅድሚያ የመስጠት ጉዳይ ነው" ብሏል።
"ዘላለማዊ ለመሆን ካልሞከርን በስተቀር ብዙ ተጨማሪ ወጪ ልናወጣ እንችላለን። እና ወጪው ከእሴቶቼ ጋር የተጣጣሙ እንደሚሆኑ አውቃለሁ።"
ቢል ጌትስ የሀብቱን 99 በመቶ ቢሰጥም ቢሊየነር ሆኖ እንደሚቀጥል የብሉም በርግ ዘገባ ያሳያል።
የማይክሮሶፍት መስራቹ ቢል ጌትስ የዓለማችን አምስተኛው ሀብታም ነው።
ጌትስ በብሎጉ ላይ ባሰፈረው ረዥም ጽሑፍ ሀብቱን በጊዜ ሰሌዳ ዘርዝሮ ያስቀመጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተጣራ የሀብት መጠኑ 108 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ያሳያል።
ይህንን የሀብቱን መጠን እአአ በ2045 ዜሮ ለማድረስ ማቀዱንም በዚሁ ጽሑፉ ላይ አስፍሯል።
ቢል ጌትስ ከጓደኛው ፖል አለን ጋር በጋራ በመሆን በእአአ በ1975 ማይክሮሶፍትን የመሰረቱ ሲሆን በኮምፒውተር ሶፍትዌር የዓለምን ገበያ መቆጣጠር ችሏል።
ጌትስ ቀስ በቀስ በድርጅቱ ውስጥ ካለው ተሳትፎ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን በ2000 ከአመራርነቱ በ2014 ደግሞ ከሊቀመንበርነቱ ለቅቋል።
ቱጃሩ ቢልጌትስ ገንዘቡን ለሌሎች ለማከፋፈል የተነሳሳው ከባለሃብቱ ዋረን በፌት እና ሌሎች በጎ አድራጊዎች በመመልከት መሆኑን ተናግሯል።
ይኹን እንጂ ተቺዎቹ ቢል ጌትስ ፋውንዴሽኑን ግብርን ላለመክፈል እንደ መሸሸጊያ ይጠቀምበታል ሲሉ ይተቹታል።
ጌትስ በብሎጉ ላይ በጻፈው ረዥም ጽሁፍ ፋውንዴሽኑ ሦስት ዓላማዎችን ዘርዝሯል።
መከላከል የሚቻሉ እና እናቶችን እና ሕጻናትን ገዳይ የሆኑ በሽታዎችን ማጥፋት፣ ወባን እና ኩፍኝን ጨምሮ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ማጥፋት፣ እንዲሁም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከድህነት ማውጣት ናቸው።
ጌትስ አሜሪካ፣ ዩኬ እንዲሁም ፈረንሳይ ለውጪ እርዳታ የሚያውሉትን በጀት መቀነሳቸውን ተችቷል።
"የዓለማችን ሀብታም አገራት ለድሃ ሕዝቦች ይቆሙ እንደሆን ግልጽ አይደለም" ሲል ጽፏል።
"ነገር ግን አንድ ነገር እርግጠኛ የምንሆነው፣ ጌትስ ፋውንዴሽን በሁሉም ስራዎቹ አገራትን እና ሕዝቦች ከድህነት እንዲወጡ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል"
ከቢቢሲ ኒውስ አወር ጋር በነበረው ቆይታ ዶናልድ ትራምፕ የመንግሥት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ በሚል የመሰረቱትን መሥርያ ቤት እንዲመራ የሾሙትን ባለሀብቱን ኤለን መስክ የአሜሪካን እርዳታ በማቋረጥ ሕጻናትን እየገደለ ነው ሲል መተቸቱን በተመለከተ ተጠይቆ "የእርዳታ ማቋረጡ ሕጻናትን ብቻ አይደለም የሚገድለው፣ ሚሊዮን ሕጻናትን ነው" ብሏል።
"የዓለማችን ቱጃር ሰው ይህንን ያደርጋል ብለህ አትጠብቅም" ሲል አክሏል።
ጌትስ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበረው ቆይታ ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ሰርጥ "ለሃማስ" ኮንዶም ለመግዛት የሚውል ነው በሚል ለሆስፒታል ይሰጥ የነበረ የእርዳታ ገንዘብ ስለማቋረጣቸው በማንሳት ተናግሯል።
መስክ በኋላ ላይ ዶናልድ ትራምፕ ያሉት ስህተት መሆኑን ጠቅሶ "ስህተት እንሰራለን" ቢልም እርዳታው ግን ሳይቀጥል ቀርቷል።
"ያንን እርዳታ በማቋረጡ [መስክ] በኤች አይቪ የተጠቁ ሕጻናትን ሄዶ ቢያይ እመኛለሁ።" ሲል ጌትስ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናግሯል።
በአንድ ወቅት ጌትስ እና የቴስላ ባለቤት ኤለን መስክ የዓለማችን የቱጃሮች ሚና መሆን ያለበት ሌሎችን ለማገዝ ገንዘብ መስጠት መሆኑን ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጋጭተዋል።
ቢቢሲ መስክን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቆት የነበረ ቢሆንም ለጊዜው አልተሳካም።
ጌትስ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ ታዳጊ አገራት በጤና ዘርፍ ድጋፍ ያደርጋል።












