አሜሪካዊው ሮበርት ፕሪቮስት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመረጡ

ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ

በአሜሪካ ቺካጎ ተወልደው ያደጉት የ69 ዓመቱ ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት፣ ፖፕ ሊዮ ተብለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመረጡ።

ካርዲናል ፕሪቮስት በፔሩ ጳጳስ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በሚሺነሪነት አገልግለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ጣልያንኛ እና ስፓኒሽኛ የሚናገሩ ሲሆን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎታቸው እንዲሁም አዳማጭነታቸው ይጠቀሳሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት እአአ በ2023 ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የቫቲካን የጳጳሳት አለቃ አድርገው በመሾም ቀጣዩን የጳጳሳት ትውልድ በመምረጥ ውስጥ ቁልፍ ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርገዋል።

ካርዲናል ፕሮቮስት ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ተብለው ለመጠራት መወሰናቸው ተገልጿል።

ለሁለት ቀናት አዲሱን ሊቀጳጳስ ለመምረጥ የተሰባሰቡት የቤተ ክርስቲያኗ ካርዲናሎች ከተሰበስቡብት ቤተ መቅደስ አናት ላይ አዲስ ሊቀ ጳጳስ መመረጡን የሚያሳየው ነጭ ጭስ የታየው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ነበር።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካርዲናሎች በምሥጢር በሚሰጡት ድምጽ ለመመረጥ በዕጩነት ከቀረቡት ካርዲናሎች መካከል ሁለት ሦስተኛውን ድምጽ ያገኙት የሃይማኖት አባት ቀጣዩ ሊቀ ጳጳስ ይሆናሉ።

አሜሪካዊው ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ በቫቲካን አዲሱን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ ለሁለተኛ ቀን የተሰባሰቡት ካርዲናሎች በምሥጢር ድምጻቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ነው አዲስ ሊቀ ጳጳስ መሆናቸ ይፋ የተደረገው።

ድምጽ መስጠት ከሚችሉት 133 ካርዲናሎች መካከል የ89ኙን ይሁንታ ያገኙት ሊቀ ጳጳስ በቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በረንዳ ላይ ብቅ በማለት ለሕዝብ ታይተዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰባሰቡ የእምነቱ ተከታዮች ሊቀ ጳጳሱን ሲመለከቱ ደስታቸውን በጩኸት እና በእንባ ገልጸዋል።

ዕድሜያቸው እስከ 80 ዓመት የሚሆን 133 ካርዲናሎች ቀጣዩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ማን ሊሆን እንደሚገባ ከተወያዩ በኋላ ይሆናሉ ያሏቸውን በዛሬው ዕለት መርጠዋል።

ሚያዝያ 13/2017 ዓ.ም. ሕይወታቸው ያለፈው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን የተኩት አባት አሜሪካዊው ካርዲናል ሮበርት ፕሮቮስት ሆነው ተመርጠዋል።

አዲሱ የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ

በጣልያንኛ እና በስፓኒኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ንግግራቸውን ያደረጉት ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ "ይህ ሰላም የመላበት ሰላምታዬ ለሁላችሁም ልብ እና ቤተሰብ . . . እንዲሁም በዓለም ላሉ ሕዝቦች እንዲደርስ ይሁን" በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የመጀመሪያው አሜሪካዊ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆነው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር "እግዚአብሔር ሁላችንንም ይወደናል፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ" ብለዋል።

አዲሱ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ "ሰብዓዊነት በእግዚአብሔር እና በፍቅሩ የሚደረስበት ድልድይ ክርስቶስን ይፈልጋል። አግዙን፤ እርስ በርሳችሁም ተረዳዱ። ድልድይ እንገንባ" ብለዋል።

በንግግራቸው በሞት የተለዩትን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን ያስታወሱት ተተኪያቸው ለሕዝቡ እርሳቸው እንዳደረጉት ምዕመናኑን መባረክ እንደሚፈልጉ ተናግረው ቡራኬ ሰጥተዋል።

ድምጻቸውን የሰጧቸውን ካርዲናሎች ያመሰገኑት ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ "እግዚአብሔር ወዳዘጋጀልን ቤታችን ሁላችንም በጋራ እንጓዛለን" ካሉ በኋላ "ለሮማ ቤተክርስቲያን ልዩ ሰላምታ ይድረስ" ብለዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት የእምነቱ ተከታዮች አንድነት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሊቀ ጳጳሱ ሁሉም በጸሎት እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል።

አዲስ ሊቀ ጳጳስ መመረጡን የሚያሳይ ነጭ ጭስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአዲስ ጳጳስ መመረጥ መጀመሪያ ላይ የተበሰረው ካርዲናሎች ከተሰበሰቡበት ቤተ መቅደስ ጣራ ላይ በታየው ጭስ ነበር

የአዲሱ ጳጳስ ምርጫ

የአዲሱ ሊቀ ጳጳስ ማንነት ይፋ ከመሆኑ በፊት በምስጢር ድምጽ የሚሰጡት ካርዲናሎች እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሁለት ቀን ወስዶባቸዋል።

ይህም ማለት በዕጩነት የቀረቡት እና ሁለት ሦስተኛው መራጭ የተስማማባቸው አባት ብዙዎችን መማረክ ችለዋል ማለት ነው።

ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ እና ቤኔዲክት 16ኛ ሲመረጡም አብላጫውን ድምጽ ማግኘታቸው የታወቀው በሁለተኛው ቀን ነበር።

ነገር ግን ቤተክርስቲያኒቱን ለረዥም ዓመት በሊቀ ጳጳስነት ያገለገሉት ጆን ፖል ዳግማዊ እአአ በ1978 በሦስተኛው ቀን ነበር መመረጣቸው የታወቀው።

በሲስቴይን ቤተ መቅደስ የተሰባሰቡ 133 ካርዲናሎች ተራማጅ፣ ወግ አጥባቂ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ አንድ ያመጣሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው አባቶች መካከል አንዱን በአብላጫ ድምጽ መምረጥ ይጠበቅባቸው ነበር።

አዲሱን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ የተሰባሰቡት 133 ካርዲናሎች ከ71 የተለያዩ አገራት የተገኙ ናቸው።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰባሰበው የእምነቱ ተከታይ አዲሱ ጳጳስ ማን መሆናቸውን ለማየት በጉጉት እየጠበቀ ነው።

የካርዲናሎቹ ምርጫ በመላው ዓለም በሚገኙ 1.4 ቢሊዮን ተከታዮች ዘንድ እና በቤተክርስቲያኒቷ ላይ ተጽዕኗቸው የገዘፈ ነው።

በአሁኑ ምርጫ ከተሳፉት 80 በመቶ የሚሆኑት ካርዲናሎች የተመረጡት በሟቹ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የተሾሙ ናቸው።

አብዛኞቹም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊቀ ጳጳስ የመርጡ ሲሆን፣ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ምልከታም ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡ ምዕመናን በአዲሱ ጳጳስ ምርጫ ደስታቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡ ምዕመናን በአዲሱ ጳጳስ ምርጫ ደስታቸውን ሲገልጹ

ጳጳሱ ሲመረጡ የተደረገው. . .

በዕጩነት ከቀረቡት ካርዲናሎች መካከል አንደኛው አስፈላጊውን ድምጽ አግኝተው ከተመረጡ "ይህንን ቀኖናዊ ምርጫ ተቀብለው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቀ ጳጳስነት ይቀበላሉ?" ተብለው ተጠይቀዋል።

ተመራጩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ተብለው ሊጠሩበት የሚፈልጉትን ስም በመምረጥ የጵጵስና ካባ እንዲለብሱ ይደረጋል። የጵጵስና ስማቸውም ሊዮ 14ኛ የሚለውን ስም መርጠዋል።

የቀሩት ካርዲናሎችም ለአዲሱ ጳጳስ እጅ በመንሳት በአገልግሎታቸው ሁሉ ሊታዘዟቸውም ቃል ገብተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን በረንዳ ላይ በላቲን ቋንቋ "ጳጳስ አለን" ተብሎ ይታወጇል።

የአዲሱ ሊቃነ ጳጳሳት ስም ለሕዝቡ ይፋ ሆኖ፣ ጳጳሱ ራሳቸውም በአካል ወጥተው ለሕዝቡ ታይተዋል። አዲሱ ጳጳስም አጭር ንግግር አድርገው ለከተማዋ እና ለዓለም የቡራኬ ቃል አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም በምሥጢራዊ ምርጫ ሂደት የእያንዳንዱ የምርጫ ዙር ውጤትን ጳጳሱ እንዲመለከቱ ይደረጋል።

ሰነዶቹ ታሽገው በቫቲካን ቤተ መዛግብት ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርገው ከዚያ በኋላ ሊከፈቱ የሚችሉት በሊቀ ጳጳሱ ትዕዛዝ ብቻ ነው።

አዲሱ ጳጳስ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲታዩ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ ጳጳስ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲታዩ