የፕሪሚዬር ሊግ ግምት፡ አርሰናል ያሸንፋል፤ ዩናይትድ አቻ ይለያያል፤ ቼልሲ ደግሞ ይሸነፋል

ቅዳሜ
ፉልሃም ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ኤሪክ ቴን ሃግ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ ጀምሮ 411 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭ አድርገዋል። ይህን ያህል ወጭ የተደረገበት ቡድን ከዚህ የተሻለ ብቃት ማሳየት ነበረበት ይላል ሱቶን።
ቴን ሃግ ይመቸኛል የሚለው ሱቶን አሰልጣኙ ባለፈው የውድድር ዓመት የተሻለ ነገር ማሳየታቸውን ያምናል። ነገር ግን አሁን አሰልጣኙ ከባድ ጫና ላይ ናቸው።
ፉልሃም አምና የነበራቸውን ዓይነት ብቃት እያሳዩን አይደለም የሚለው ሱቶን በተለይ የቡድን የፊት መስመር አስፈሪ አይደለም ይላል።
ግምት፡ 1 - 1
ብሬንትፈርድ ከ ዌስት ሃም
ሁሌም ዌስት ሃም በተከታታይ ሲሸነፍ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞየስ ትክክለኛው ሰው አይደሉም የሚሉ ወሬዎች ይሰማሉ። ይህ ወሬ አይስማማኝም ይላል ሱቶን።
ሞየስ፤ በዌስት ሃም ቤት የሰራውን ሥራ ሰሞናዊ ደካማ አቋም አይለውጠውም የሚለው ሱቶን ብሬንትፈርድም በተመሳሳይ ደካማ ሳምንታት ማሳለፋቸውን ይገልጣል።
ምንም እንኳ ንቦቹ በሰባት ጨዋታዎች አራት ሽንፈት ቢቀምሱም አሁን መልካም አቋም ላይ ናቸው።
ብሬንትፈርድ ባለፈው ሳምንት ወደ ስታምፈርድ ብሪጅ አቅንተው ቼልሲን አሸንፈው ተመልሰዋል።
ሱቶን ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ብዬ ልገምት አስቤ ነበር ነገር ግን ብሬንትፈርድ ድል እንደሚቀናቸው አምናለሁ ባይ ነው።
ግምት፡ 2 - 0
በርንሊ ከክሪስታል ፓላስ
በርንሊ በሜዳቸው ከአምስት ጨዋታዎች አምስቱን ተሸንፈዋል። አቻም ቢሆን ትልቅ ውጤት ነው።
ምንም እንኳ ከፓላስ ጋር ቢሆንም የሚጫወቱት ጎል አይገባባቸውም ብዬ አላስብም የሚል አስተያየቱን የሰጠው ሱቶን፤ ጨዋታው ብዙ ጎል የሚታይበት ጨዋታ እንዳልሆነ ይገምታል።
ንስሮቹ ክሪስታል ፓላሶች ባለፉት 10 ጨዋታዎች ስምንት ጎል ብቻ ነው ያስቆጠሩት። ነገር ግን ኤቤሬቺ ኤዜ እና ማይክል ኦሊሴ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጭ መሆናቸው ለሮይ ሆጅሰን ፈተና ነው።
ግምት፡ 1-1

ኤቨርተን ከብራይተን
ባለፈው የውድድር ዘመን በአሜክስ ስታድየም ኤቨርተን ብራይተንን 5-1 ሲረመርም በስፍራው ነበርኩ የሚለው ሱቶን ብራይተንን ለማሸነፍ ትልቁ መላ መልሶ ማጥቃት እንደሆነ ይናገራል።
ምንም እንኳ ኤቨርተን በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳቸው ያላቸው ሬከርድ ደካማ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጠቅላላው መነቃቃት አሳይተዋል።
እውነት ለመናገር ይህ ጨዋታ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም የሚለው ሱቶን ሁለቱም ቡድኖች ጎል እንደሚያገቡ ግን ይገምታል።
የኤቨርተኑ አሰልጣኝ ሾን ዳይሽ ባለፈው የውድድር ዘመን የተገበሩትን ስልት ከደገሙ ድል ሊቀናቸው ይችላል ይላል።
ግምት፡ 2 - 1
ማንቸስተር ሲቲ ከቦርንመዝ
ቦርንመዝ ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲሱ አሰልጣኛቸው ኢራዎላ እየተመሩ ድል ቀንቷቸዋል። ቢሆንም አሁንም ብዙ ይቀራቸዋል።
ማንቸስተር ሲቲ በሜዳቸው በሁሉም ውድድሮች ያደረጓቸውን 21 ጨዋታዎች አሸንፈዋል። ይህ ክብረ-ወሰን ቦርንመዝ ምን ያክል ፈተና ፊታቸው እንደተጋረጠ ማሳያ ነው።
ፔፕ ጉዋርዲዮላ የአሰላለፍ ለውጥ አድርገው ሊገቡ እንደሚችሉ ሱቶን ይገምታል።
በግራ ክንፍ ጄሬሜ ዶኩ ወይስ ግሪሊሽ ? ማንም ይሰለፍ ማን ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። ሲቲ በሰፊ ውጤት እንደሚያሸንፍ አምናለሁ።
ግምት፡ 4 - 0
ሼፊልድ ዩናይትድ ከዎልቭስ
ከመጀመሪያዎቹ 10 ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያላቸው ሼፊልድ ዩናይትዶች በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ በጣም ዝቅተኛ ነጥብ ያለው ክለብ ሊሆኑ ይችላሉ።
የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ ለማግኘት ጉጉት ላይ ያሉት ሼፊልዶች በዚህ ሳምንት የሚገጥሙት ወደ አቋማቸው እየተመለሱ ያሉትን ዎልቭሶች ነው።
የዎልቭስ አሰልጣኝ ጋሪ ኦኒል አዝናኝ ኳስ እያሳዩ ነጥብም እያካበቱ ነው። ነገር ግን በጉዳት ምክንያት ፔድሮ ኔቶን ማጣታቸው ጎድቷቸዋል። ቢሆንም ድል ይቀናቸዋል ሲል ሱቶን ይገምታል።
ግምት፡ 0 - 1

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኒውካስል ከአርሰናል
ኒውካስል ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ አቅንቶ በተቀያሪ ተጫዋች በሊግ ዋንጫ ድል ይዞ ተመልሷል።
በተመሳሳይ መርሃ ግብር ወደ ዌስት ሃም ያቀናው ማይክል አርቴታ ቡድኑ 3-0 እስኪመራ ጠብቆ ሳካ፣ ማርቲኔሊ እና ኦዴጋርድን ማስገባቱ ገርሞኛል።
ያንን ውጤት እንዲቀለብሱ ጠብቆ ነው? ወይ ከጅማሬው ማስገባት አሊያም ደግሞ 1-0 እያሉ መቀየር ነው ይላል ሱቶን።
በዚህ ጨዋታ ብዙ ጎል አናይም የሚለው ሱቶን አርሰናል ድል ሊቀናው እንደሚችል ይገምታል።
ግምት፡ 0 - 2
እሑድ

ኖቲንግሃም ፎረስት ከአስተን ቪላ
ኖቲንግሃም በሜዳቸው ሲጫወቱ ከባድ ይሆናሉ የሚለው ሱቶን አስተን ቪላ ግን አሁን ባለው አቋማቸው ማንንም ከመርታት ወደኋላ እንደማይሉ ያስረዳል።
የኡናይ ኤምሪ ቡድን ግሩም ጨዋታ እያሳዩ መሆናቸው በራስ መተማመናቸውን ከፍ እንዳደረገው ይተነትናል።
ፎረስት ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ድል አልቀናቸውም፤ ነገር ግን ከስድስቱ አራቱን አቻ አጠናቀዋል።
ግምት፡ 0 - 2
ሉተን ከሊቨርፑል
ሉቶን በሜዳቸው ብዙ ጎል አይገባባቸውም ይባላል። ቢሆንም ይህ እኔን አያሳምነኝም የሚለው ሱቶን የቶተንሃምን ጨዋታ አስታውሶ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በርካታ ጎል ሊገባ እንደሚችል ይናገራል።
ከሌሎቹ ዘንድሮ ሊጉን ከተቀላቀሉ ቡድኖች በተሻለ ሉተን ታውን ተፎካካሪ ሆነው ታይተዋል።
ነገር ግን የሊቨርፑልን ጫና መሸከም ይችላሉ የሚል ግምት የለውም።
ግምት፡ 0 - 3
ሰኞ

ቶተንሃም ከቼልሲ
ቶተንሃም ይህን ጨዋታ ይረታል ብዬ ባስብም የሆነ ነገር ግን ይቆጠቁጠኛል ይላል ሱቶን።
ይህ ጨዋታ እንዴት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ወረቀት ላይ መገመት እጅግ ቀላል ነው። ስፐርስ ሊጉን እየመሩ ነው፤ ቼልሲ ደግሞ ወጣ ገባ ናቸው።
ነገር ግን የሰማያዊዎቹ አለቃ ፖቼቲንሆ በ2019 ከተባረሩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወደ ሰሜን ለንደን የሚጓዙት።
ያም ሆነ ይህ አሁን ባላቸው አቋም ላይ ተመስርቼ ቶተንሃም ጨዋታውን ያሸንፋል እላለሁ ይላል ሱቶን።
ግምት፡ 2 - 0












