አውስትራሊያ ለፍልስጤም እውቅና ልትሰጥ እንደምትችል ጠቆመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገሪቱ ለፍልስጤም እውቅና ልትሰጥ እንደምትችል ጠቆሙ።
የአውስራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ ካንቤራ ለፍልስጤም እውቅና ልትሰጥ የምትችለው ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።
ፔኒ ዎንግ በፍልስጤም አስተዳደር ውስጥ ሐማስ ምንም አይነት ተሳትፎ አይኖረውም ብለዋል።
ካንቤራ ለእስራኤል እና ለፍልስጤም ግጭት መፍትሄው የሁለት ነጻ አገራት መመስረት ብቻ ነው ስትል ቆይታለች።
ይህ የአውስራሊያ አስተያየት ገና በጥሬው ያለ ሐሰብ እንደሆነ ቢገለጸም ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም ተመሳሳይ ሃሳብ አንጸባርቃ ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ከእስራኤል ይሁንታ ውጪ ለፍልስጤም እውቅና ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረው ነበር።
በቅርቡ እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ስላለው ወታደራዊ ዘመቻ ስጋቷን ስትገልጽ የቆየችው አውስትራሊያ፤ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን የሁለት ነጻ አገራት ሁነኛ አማራጭ ነው ብላለች።
ዎንግ እስራኤል እና ፍልስጤም ሁለት የተለያዩ አገራት ሆነው መኖር “ማለቂያ የሌለውን ተደጋጋሚ ግጭት ለማስቀረት ብቸኛው አማራጭ ነው” ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አስተዳደር በፍልስጤም አገር መሆን ዙሪያ ጨርሶ ለንግግር አልቀመጥም ማለቱ ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
“ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና በመስጠት ለሠላም የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር እንደ አማራጭ እየተመለከተው ነው” ብለዋል።
የአውስትራሊያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን ይህን ውሳኔ እንደሚቃወሙ እየገለጹ ይገኛሉ።
ተቃዋሚው ሳይመን በርሚንግሃም የአውስትራሊያ መንግሥት ውሳኔ የፍልስጤም ደኅንነትን ሳይረጋገጥ የአገርነት እውቅናን ለመስጠት ማሰብ ሰህተት ነው ብለዋል።
በርሚንግሃም ፍልስጤም አገር ብትሆን አሁን ግጭት እየቀስቀሱ ላሉ “አሸባሪዎች አስቃቂ ግጭት እንዲፈጥሩ ዕድል መስጠት ነው” ብለዋል።
የዚኦኒስት ፌዴሬሽን ኦፍ አውስትራሊያ ፕሬዝዳንት ጄሬሜ ሌኢበለር ደግሞ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና የመስጠት ሃሳብ ገና በጅምር ያለ ነው ብለዋል።
“እውቅና ስለመስጠት ከመነጋገራችን በፊት ሐማስ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ አዲስ የፍልስጤም የአመራር ትውልድ መፈጠር አለበት” ብለዋል።
140 አገራት ለፍልስጤም እውቅና ቢሰጡም ኃያላኑ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና አውስራሊያ እውቅና አይሰጡም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአሁኑ ወቅት “ታዛቢ አገር” በሚል የሚጠራትን ፍልስጤም ሙሉ አባል አድርጎ ለመመዝገብ አቅዷል።
ሐመስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ ደንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እስራኤል እየወሰደች ባለችው የአጸፋ እርምጃ ብዙ ትችት እየቀረበባት ይገኛል።
ሐማስ በድንገተኛ ጥቃቱ 1ሺህ 200 ሰዎችን ገድሎ ከ250 በላይ ታጋቾችን ወደ ጋዛ ወስዶ ነበር።
እስራኤል በበኩሏ በጋዛ እያደረገች ባለችው የአጸፋ እርምጃ አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ33ሺህ በላይ ሰዎችን ገድላለች።
ከዚህ በተጨማሪም ጦርነቱ በጋዛ ባሉ ሰዎች ላይ አደገኛ የረሃብ አደጋን ደቅኗል።












