ኢትዮጵያ የገቡት የቮልክስዋገን ኤሌክትሪክ መኪኖች ዋስትና የላቸውም ተባለ

ከእውቅና ውጪ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል የተባሉት አይዲ 4 እና አይዲ 6 ክሩዝ ቮልክስዋገን ኤሌክትሪክ መኪኖች ዋስትና የላቸውም ተባለ።

ባለፈው ሳምንት የታዋቂው የጀርመን መኪና አምራች ቮልክስዋገን ስሪት የሆኑት የኤሌክትሪክ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እግድ መተላለፉ ይታወሳል።

ቅንጡዎቹ መኪኖች ለኢትዮጵያ ገበያ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይቀርቡ የታገዱት በመኪና አምራቹ ጥያቄ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አማካይነት ሲሆን፣ የእግዱ ምክንያት ግን ግልጽ ሳይደረግ ቆይቷል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ መኪና አምራቹን ቮልክስዋገንን የጠየቀ ሲሆን፣ ኩባንያው እግዱ ከሕጋዊ ጉዳዮች እና ከዋስትና ጋር የተያያዙ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጿል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን በበኩሉ መኪኖቹ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ያገድኩት መኪኖቹ በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ ለመነዳት ብቁ (roadworthy) መሆናቸውን ማረጋገጥ ስለሚኖርብኝ ነው ብሏል።

ዋስትና እና ፍቃድ የላቸውም

የጀርመኑ መኪና አምራች ቮልክስዋገን መኪኖቹ በኢትዮጵያ ገበያ እንዳይሸጡ አዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ በኩል ነው ጥያቄውን ያቀረበው።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርም ጥያቄውን ተከትሎ መኪኖቹ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ጊዜያዊ እገዳ መጣሉን ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫው አረጋግጧል።

በዓለም ዙሪያ ታዋቂ የሆነው ቮልክስዋገን እነዚህ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እግድ እንዲያጣል ጥያቄ ያቀረበው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።

የኩባንያው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ለቢቢሲ በኢሜይል በሰጠው ምላሽ በቻይና የሚመረቱ የቮልክስዋገን ID.4፣ ID.6 X እና ID.6 CROZZ የተባሉት መኪኖች መቅረብ ያለባቸው ለቻይና ገበያ ብቻ መሆኑን እና ከቻይና ውጪ እንደማይሸጡ በሕግ መደንገጉን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ለቻይና ተብለው የተሰሩ ቮልክስዋገን አይዲ መኪኖችን ከቻይና ውጪ ያሉ ደንበኞች የሚገዙ ከሆነ ለተሸከርካሪዎቹ የዋስትና መብት አያገኙም ብሏል ኩባንያው።

ማስጠንቀቂያ ለገዢዎች

ኩባንያው ሕጋዊ ፍቃድ የሌላቸው መኪና ሻጮች፣ መኪኖቹ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳላቸው በመግለጽ ለደንበኞቻቸው እየሸጡ እንደሆነ ደርሼበታለሁ ብሏል።

ነገር ግን አይዲ.4፣ አይዲ.6 ኤክስ እና አይዲ.6 ክሩዝ ለቻይና ብቻ ተብለው የተመረቱ በመሆናቸው መኪኖቹ ከቻይና ውጪ የሚያስፈልጋቸው ዋስትና የላቸውም ብሏል።

እነዚህ ከእውቅና ውጪ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል የተባሉት መኪኖች በኢትዮጵያ “የቮልክስዋገን እውቅና ባላቸው ሻጮች ወይም ቮልክስዋገን ባጸደቃቸው ሰርቪስ ማድረጊያ ተቋማት ውስጥ ሁሉንም አይነት የመኪና ‘ሰርቪስ’ እና የጥገና አገልግሎት ሊያገኙ አይችሉም” ብሏል ኩባንያው።

ፍቃድ የሌላቸው ሻጮች እነዚህን መኪኖችን ሕጋዊ እና ይፋዊ ባልሆነ መንገድ በተደጋጋሚ በሌሎች አገራት ለመሸጥ እየሞከሩ ነው ያለው ኩባንያው፤ ደንበኞች መኪኖችን ከመግዛታቸው በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ኩባንያው አገራት እነዚህን መኪኖች ወደ አገር ውስጥ እንዳያስገቡ ማሳሰቢያዎችን እያላከ መሆኑን ገልጾ፤ “ደንበኞች አይዲ መኪኖችን ሲገዙ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ከሕጋዊ ወኪሎች ብቻ እንዲገዙ ያሳስባል” ብሏል።

ያልተጠናቀቀ መመሪያ

ቮልክስዋገን ተሸካርካሪዎቹ ላይ እግድ እንዲጣል ጥያቄ ያቀረብኩት በሕጋዊ እና ከዋስትና ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ናቸው ይበል እንጂ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ግን መኪኖቹን ያገድኩት ለኢትዮጵያ መንገዶች ብቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ስለሚኖርብኝ ነው ብሏል።

ተሸከርካሪዎቹ “የደኅንነት ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ብለን አናስብም፣ ይሁን እንጂ በቅርብ ቀናት ከኤምባሲው ጋር ተነጋግረን ለሁሉም መልስ እንሰጣለን” ያሉት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ትራንስፖርት እና አሸከርካሪ ተሽከርካሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ከድልማግስት ኢብራሂም ናቸው።

እነዚህ ተሸከርካሪዎች በኢትዮጵያ ገበያ እንዲቀርቡ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው እንዴት ከቻይና ሊመጡ ቻሉ በሚል ከቢቢሲ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

በምላሻቸውም የእግድ ጥያቄው ከኩባንያው የመጣው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚቻልባቸው መመሪያዎች እና ደንቦች እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት መሆኑ አስታውሰው፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስገቢያ ፍቃድ ገና በዝግጅት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ በፊት ወደ አገር ውስጥ የገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ሲሰተናገዱበት በነበረው መመሪያ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ላይ ወደ አገር ቤት ገብተው ለሽያጭ ያልቀረቡትን ቮልክስዋገን መኪኖችን በተመለከተ ለመነጋገር ከጀርመን ኤምባሲ ጋር በዚህ ሳምንት ቀጠሮ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ለቻይና ገበያ የታለሙት መኪኖች

የጀርመኑ ግዙፍ መኪና አምራች ኩባንያ እአአ 2030 በቻይና ለገበያ ከሚያቀርባቸው መኪኖች መካከል 50 በመቶ ያክሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች ለማድረግ ውጥን አለው።

ይህንንም ለማሳካት ነው እነዚህን አይዲ መኪኖች ከእአአ 2021 አጋማሽ ጀምሮ በቻይና ማምረት የጀመረው።

እነዚህ ዘመናዊ መኪኖች እንደየዓይናታቸው በኢትዮጵያ ገበያ ከ4.2 ሚሊዮን እስከ 5.4 ሚሊዮን ብር ገበያ ላይ ቀርበዋል።

እነዚህ የአይዲ ዝርያ የሆኑት መኪኖች ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ እየተመረቱ እስካሁንም ለገበያ እየቀረቡ ሲሆን፣ ከ177 እስከ 225 የፈረስ ጉልበት አላቸው።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩት እነዚህ መኪኖች አንድ ጊዜ ባትሪያቸው በ240 ኪሎ ዋት ኃይል ቻርጅ ከሆነ እስከ 580 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ ይችላሉ።

ከአምስት እስከ 7 ሰዎች የመጫን አቅም ያላቸው መኪኖቹ በቀላሉ በማቆሚያ ስፍራ ለማቆም የሚያስችሉ ከፊት እና ከኋላ ካሜራዎች ተገጥሞላቸዋል። የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ የድምጽ እና የአቅጣጫ ጠቋሚ ሥርዓቶችም ተገጥሞላቸዋል።