የቱርክ ርዕደ መሬት፡ የ5 ዓመቱ ታዳጊ ከአራት ቀናት በኋላ በፍርስራሽ ውስጥ በህይወት ተገኘ

ታዳጊው

የ5 ዓመቱ ታዳጊ አርስ ከቀናት በፊት የተፈጠረው አደጋ ምን ያህል አስከፊ እንደነበረ ገና የተረዳው አይመስልም። በአዋቂዎች የሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝቶ በትንሽዬ መኪና ይጫወታል።

ወደፊት በቱርክ ርዕደ መሬት በተአምር ከተረፉ ሰዎች አንዱ እንደሆነ ሲያውቅ ይደንቀዋል።

መደነቅ ብቻ ግን አይደለም ልቡን ሊሰብረው ይችላል። ምክንያቱም ከአደጋው እሱ የመትረፍ ዕድል ይኑረው እንጂ የ7 ዓመት ዕድሜ ያላት እህቱ ሂራኒር እና የ9 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድሙ አልፕ እና አባቱ በርዕደ መሬቱ ህይወታቸው አልፏል።

ተአምረኛው ህጻን ከ105 ሰዓታት ወይም ከአራት ቀናት በኋላ በርዕደ መሬቱ ክፉኛ ከተጎዳችው ካሃራማንማራስ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ፍርስራሽ ውስጥ በነፍስ አድን ሰራተኞች ህይወቱ ተርፏል።

ታዳጊው ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል ሲገባ የሰውነቱ ሙቀቱ ወደ 28 ዲግሪ ሴልሽየስ ወርዶ ነበር። ይህንን የሙቀት መጠን ባለሙያዎች ለህይወት አስጊ ብለው የሚመድቡት ነው።

የአረስን ጸጉር እየደባበሱ ሆስፒታል እያስታመሙት የሚገኙት አያቱ መሃመት ናቸው።

“ታማኝ ልጅ ነው። ጠንካራ ስብእናም አለው። ቅን ልጅ ነው። አልተበላሸም” ይላሉ።

አያቱ ምንም እንኳን እድሜያቸው 72 ዓመት ቢደርስም በቀረው ጊዜያቸው አራስን እንደሚንከባበከቡት ይናገራሉ።

“የነፍስ አድን ሰራተኞች ህይወቱን ለመታደግ ጥሩ ስራ ሰርተዋል። እናም በፈጣሪ ሞገስ ወደ ሕይወት መልሰውታል” ሲሉም አክለዋል።

አረስ በጥሩ ሁኔታ እያገገመ ይገኛል።

መልካሙ ነገር የአረስ እናትም ከአደጋው ተርፋለች። ሆኖም ያ ርዕደ መሬት ተከስቶ ህይወታቸው ከተመሰቃቀለ በኃላ እናት ልጅ አልተገናኙም። እሷ በሌላ ሆስፒታል ህክምናዋን እየተከታተለች ሲሆን እንደምታገግም ይጠበቃል።

አራስ ህክምናው እየተከታተለ ያለበት የጽኑ ህሙማን ክፍል ከእስራኤል በመጡ ሃኪሞች የተቋቋመ ነው።

ታዲያ በዚህ ሆስፒታል የ5 ዓመቱ ታዳጊ የተረፈበት አጋጣሚ ብቻ አይደለም አስገራሚው። ከሱ በ60 ዓመት የሚበልጡ አዛውንት ከርዕደ መሬት በስገራሚ ሁኔታ ተርፈዋል።

ሳሚር የተባሉት ሰው በሶሪያው ርዕደ መሬት ከተከሰተ በኃላ ለ6 ሌሊቶች በፍርስራሾች ውስጥ ቆይተዋል። ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኃላ ሀኪሞች ህይወታቸውን ታድገዋቸዋል። ሆኖም ሁለቱም እግሮቻቸው ተቆርጠዋል።

ሰዎች ለመታደግ ርብርብ በሚያደርጉ የህክምና ባለሙያዎች ሳምንቱ አሰቃቂና አድካሚ ነበር።

የህጻናት ሃኪሙ ዶክተር መሃመት ቺያን የስራ ባልደረቦቹን ለማገዝ ከኢስታሙብል ከተማ ወደ ካሃራማንማራሰ በተቻለው ፍጥነት ነበር የተጓዘው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“በጣም መጥፎ ሁኔታ ነው። በጣም ብዙ ህጻናት ወላጆቻቸውን አጥተዋል። አላውቅም። ለኔ እጅግ በጣም ከባድ ነው. . . ለኔ በጣም ከባድ ነው” ሲል ይናገራል።

በርዕደ መሬቱ እጅግ የተጎዳችው ካሃራማንማራሰ ከሚያስፈልገው እጅግ ዝቅ ያለ ዓለም አቀፍ የህክምና ደጋፍ እየተደረገላት ነው።

ቱርኮጎሉ በተባለችው ከተማ የብሪታኒያ ዶክተሮችን ህክምና ሚሰጡበት ቀያይ የህክምና ድንኳኖች በቱርክ ከተተከሉ ሌሎች ድንኳኖች ጎን ይታያሉ።

የዩኬ ሃኪሞች በመሬት መንቀጥቀጡ ውድመት በደረሰበት የከተማው ሆስፒታል ላይ የመስክ ሆስፒታል እየገጣጠመ ይገኛሉ።

ርዕደ መሬቱ በተከሰተ በሰዓታት ውስጥ የድንገተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ያኔውኑ ህይወታቸው አልፎ ሊሆን ይችላል። አሁንም ግን 80 ሺህ ሰዎች በርካታ የህክምና አገልግሎቶች እጥረት ገጥሟቸዋል።

ዶክተር ብርዮኒ ፖይንቶን በዩኬ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በሚደረግለት ግብረ ሰናይ ድርጅት ወደ ቱርክ ከሄዱ የህክምና ባለሙያዎች አንዷ ሲሆኑ ጠቅላላ ሀኪም ናቸው።

“እዚህ የራሳቸውን ደንኳን ተክለው ህክምና እየሰጡ ካሉ የቱርክ ሃኪሞች ጋር እየሰራን ነው። ታካሚዎችንም እያገዘን እያከምን ነው ግን እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው” ብላለች።

አክላም “ከዚህ ሁሉ ሰቆቃ ጋር ቀደም ብሎም ከባድ በሽታ የለባቸው ሰዎችን እያን ነው። ደህና አይደሉም። የሚያገግሙበት መሳሪያዎች የሉም። እንደዚህ አይነት ታካሚዎችን በምንችለው መጠን በርከት አደርገን ህክምና እየሰጠን ነው” ስትል ገልጻለች።

በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ሰዎች ለማከም ከዓለም ዙሪያ የመጡ በርካታ ሃኪሞችና ነርሶች አሁን በቱርክ ይገኛሉ።

ሆኖም በግለሰቦችም ላይ ይሁን በሀገር ደረጃ አሰቃቂው አደጋ ያስከተለው የአእምሮ ጉዳት ጥልቅ ነው።