በማላዊ በአንድ አልቢኖ ግድያ ወንድሙን እና አንድ ቄስን ጨምሮ አምስት ሰዎች በእስር ተቀጡ

አልቢኖ ያለባቸውን ሰዎች መግደል ከባእድ አምልኮ ጋር ይያያዛል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አልቢኖ ያለባቸውን ሰዎች መግደል ከባእድ አምልኮ ጋር ይያያዛል

በማላዊ የአካል ክፍሎቹን ለመሸጥ ያቀዱትን አልቢኖ በመግደል ወንጀል የተከሰሱ አምስት ሰዎች የዕድሜ ልክ እስራት ከከባድ የጉልበት ሥራ ጋር ተወሰነባቸው።

ማክዶናልድ ማሱምቡካ አልቢኒዝም (በተፈጥሮ ቆዳ፣ ዓይን እና ጸጉርን ነጭ የሚያድርግ ክስተት) የነበረበት ሲሆን የተገደለውም በአውሮፓውያኑ በ2018 ነበር።

የዕድሜ ልክ ቅጣት ከተላለፈባቸው መካከል አንዱ የማሱምቡካ ወንድም ነው።

አልቢኖዎችን መግደል ከጥንቆላ ሥነ ሥርዓቶች ጋር የተቆራኘ ነው። አልቢኒዝም ያለባቸው ሰዎች መልካም ዕድል ያመጣሉ የሚል የተሳሳተ እምነት በስፋት ይታያል።

በማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ከተላለፈባቸው መካከል የካቶሊክ ቄስ የሆኑት ቶማስ ሙሆሻ ናቸው። ቄስ ሙሆሻ ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር የ30 አመት እስራት ተከናንበዋል።

ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ዶርቲ ኒያካውንዳ ካማንጋ በቅጣቱ ዙሪያ ከግምት ካስገባቻቸው ምክንያቶች መካከል ሟቹ በቅርብ ሰዎች መከዳቱን፣ ግድያው በጥንቃቄ የታሰበበት እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ መገደሉን መሆኑን ጠቀሙዋል።

እአአ በ2018 ካህኑ በግድያው መሳተፉን የሚገልጽ ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰማ በኋላ የማላዊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሙሆሻን ከክህነት አግዶታል።

ባለፉት አስር ዓመታት ማላዊ በአልቢኖዎች ላይ ያነጣጠረ ተደጋጋሚ ጥቃት አስተናግዳለች። አጥንቶቻቸው እና የአካል ክፍሎቻቸው ሐብትን ወይም መልካም ዕድልን ጠያመጣል በሚል ነው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት።

እንደ ኦፊሴላዊ አሃዝ ከሆነ ከ 2014 ጀምሮ በአልቢኒዝም ጋር የሚኖሩ ከ 170 በላይ ሰዎች በተመሳሳይ ጥቃቶች ተገድለዋል ወይም ተጎድተዋል።