በከተሜዎች ዘንድ ‘ፋሽን’ እየሆነ የመጣው ተራራ መውጣት

ቢኒያም ሸሪፍ ድሮ ራሱን ለማዝናናት እንጦጦ እና የካ ተራሮችን ይወጣ ነበር፤ እሑድ-እሑድ፤ ለዚያውም ብቻውን።

ተራራ ቧጦ በወጣ ቁጥር የሆነ ልዩ ስሜት ይወረዋል። ደስስስስስ የሚል።

ደስታውን አለማጋራት ንፉግነት ሆኖ ተሰማው።

የሆነ ቀን ጓደኞቹን “በናታችሁ አብረን እንሂድ” አላቸው።

ሰባት ሆነው 6 ኪሎ ጋ መጡ። መጡና እንጦጦን ወጡ። ወጡና በሱሉልታ በኩል ወረዱ።

“እህ! እንዴት ነው ታዲያ” አላቸው ቢኒያም።

አልደበቁትም። ከዚያ ቀደም ተሰምቷቸው የማያውቅ ደስስስስ የሚል ስሜት እንደተሰማቸው ነገሩት።

ተራራ የወጣ ሰው ሲወርድ አዲስ ሐሳብ እንደ ፏፏቴ ይንዠቀዠቅለታል ይባላል።

ጓደኛሞቹም ሱሉልታን ሲወርዱ አዲስ ሐሳብ አብሯቸው ወረደ።

“ለምን በየሳምንቱ አዳዲስ ሰው ይዘን አንመጣም?” አሉ።

ያን’ለታ ‘አዲስ ሃይኪንግ’ ተወለደ።

ይህ የሆነው የዛሬ 10 ዓመት አካባቢ ነው።

30 ሰዎች ተራራ ላይ ተጠፋፋን

ቢኒያም በማግስቱ ፌስቡክ ላይ “ተራራ አብሮኝ መውጣት የሚፈልግ ካለ ይደውልልኝ” ብሎ ጻፈ።

30 ሰው መጣ፤ 30 ሰው በአንድነት እንጦጣ ላይ ወጣ።

ነገር ግን ሰዎች ደስታቸው ልክ አጣ። ቢኒያምን አልሰማ አሉት።

የመጣው ሰው ተደስቶ ስለነበር ግማሹ ሲሮጥ፣ ግማሹ ወደመሰለው አቅጣጫ ሲራመድ ቡድኑ ተበታተነ።

“ያ ጉዞ ለእኔ ከባድ ነበር፤ ሰውን ማስተባበር አቃተኝ” ይላል ቢኒያም ዕለቱን ሲያስታውስ።

ብቻ ተራራ የመውጣቱ ነገር በየሳምንቱ ቀጠለ።

የተራራ ወጪዎች ቁጥርም ጨመረ። የሚቧጠጡ ተራሮችም በዙ። እነሱን ፍለጋ የሚኬደው ኪሎ ሜትሩም ረዘመ። ባሌ ተራራ ድረስ መኬድ ተጀመረ።

ይሁን እንጂ ለቢኒያም ነገሩ ረዥም ዓመታት የቢዝነስ መልክ አልያዘለትም።

“ተራራ የምንወጣ ሰዎች ብር የምናዋጣው ምግብ ለማብሰል እና ለጋራ ወጪዎች እንጂ ቢዝነስ ለመሥራት አልነበረም” ይላል።

“ተባብረን ምግብ እናበስላለን፤ ተባብረን ድንኳን እንዘረጋለን፤ ተጋግዘን ተራራ እንወጣለን።”

ነገሩን ለብዙ ዓመታት ወደ ቢዝነስ ለምን እንዳልቀየረው ሲናገር፣ “እኔንጃ ብቻ፤ እኔም የራሴ ጥሩ ሥራ አለኝ፤ ፍቃድ ለማውጣትም የሚመች ነገር አልነበረም፤ ብቻ….” ብሎ በእንጥልጥል ይተወዋል።

ተራራ መውጣት ‘ፋሽን’ እና ቢዝነስ?

ከቢኒያም በኋላ ሌሎች በርከት ያሉ ወጣቶች ዘርፉን በስፋት ተቀላቅለዋል። በየሳምንቱ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የጉዞ ዱካቸውን (Itinerary) በማስቀመጥ ተራራ የመውጣት ጥቅል ይሸጣሉ።

አሁን አሁን፤ ዕድሜ ለእነ ቢኒያም፤ ዐርብ-ዐርብ ብን ብሎ ወደ ዱባይ በሮ ሰኞ ይመለስ የነበረ ከተሜ ሁሉ “ሃይኪንግ ካልወሰዳችሁኝ” ማለት ጀምሯል።

አዲሱ ፋሽን ተራራ ወጥቶ መውረድ ሆኗል።

አንደኛ በዱባይ ረዥም አሳንሰር እንጂ ረዥም ተራራ የለም። ረዥም ፎቅ እንጂ ረዥም አቀበት የለም።

በዚያ ላይ ምንም ዓይነት የመስታወት ክምር የልብ አያደርስም። ቢያፈጡበት መልሶ ያፈጣል። በዚያ ላይ የሰው ወርቅ አያደምቅ ነው ነገሩ።

በዚያ ላይ መስታወት ይሰለቻል። ተፈጥሮ ግን ቢደጋግሟትም ሰርክ አዲስ ናት።

በዚያ ላይ ሁሉ የሚሆነው በእናት አገር ነው። እናት ደግሞ አትሰለችም።

በዚህ የተነሳ የአገር ውስጥ ተራራ ጉዞ በብዙዎች እየተወደደ መጣ።

“ጣመን ድገመን” የሚሉ በረከቱ።

ከቢኒያም በኋላ ብዙዎቹ እንደ ቢዝነስ ለገቡበትም የተሳታፊዎቹ ቁጥር አበረታች እየሆነ ስለመጣ ነው።

በሳምንት በድምሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደተለያዩ ሥፍራዎች ያቀናሉ።

ቢኒያም በ10 ዓመታት ተሞክሮው እንደታዘበው በርካታ ከተሜ ገጠሩን ብዙም አያውቅም።

ብዙ ከተሜ በአገር ውስጥ ፊልም ካልሆነ ገጠሩን አያውቅም።

ገጠሩን ብቻ ሳይሆን የቅርብ ተራሮችን የጎበኘ ብዙ ከተሜ የለም።

ነጣ ያለ ማክያቶ መጠጣትን እንጂ ተራራ መውጣትንም ከተሜው ብዙም እንደ መዝናኛ አይመለከተውም።

“እንዲያውም ያኔ የጀመርነው ሰሞን ብዙ ሰው ‘ሃይኪንግ’ ስንለው፣ ‘ምነው ፈረንጅ ነን አላችሁ?’ እያለ ይሳለቅብን ነበር” ይላል ቢኒያም።

ለብዙዎች ተራራ መውጣት ቅብጠት፣ መሞላቀቅ፣ የሞላላቸው ፈረንጆች ብቻ የሚያደርጉት ተግባር ሆኖ ይታያቸው ነበር።

ሌሎች ደግሞ ሐሳቡን ራሱ በቅጡ አይረዱትም። ሃይኪንግ ምንድነው? ትሬኪንግ ምንድነው የሚለው ገና በወጉ አልሰረጸም።

ተራራ ለመንፈሳዊ ጉዞ ብቻ ነው በስፋት የሚታወቀው።

“አንዳንድ ሰዎች ከተራራው ጫፍ ምን አለ? ይሉኛል” ይላል ቢኒያም።

ከተራራው ጫፍ ያለው የተራራው ጫፍ ነው።

“ከዚያስ? ወጥተን ስንጨርስስ??”

የዋሕ ጥያቄም ይመስላል። ከባድ የፍልስፍና ጥያቄም ይመስላል። ለእንዲህ ዓይነት ጥያቄ ምን ተብሎ ይመለሳል?

አዲስ አበቤው ያልተገለጠለት የአዲስ አበባ ጸጋ

አዲስ አበባ ያለው ሕዝብ ሲታይ በሌላ ክልል ሰው የሚኖር አይመስልም።

ከተማዋ ተጨንቃ ቁና ቁና እየተነፈሰች ነው። ነዋሪዎቿም እንደዚያው። ጥሩ አየር ለመተንፈስ ግን ብዙ ርቀት መሄድ እንደሌለባቸው የሚያውቁ ብዙ አይደሉም።

እንደመታደል ሆኖ አዲስ አበባ በተራሮች የተከበበች ናት።

ከሦስት ሺህ ሜትር በላይ የሆኑ አምስት ተራሮች አሉ። እንጦጦ፣ የረር፣ ሞግሌ፣ ፉሪ ወዘተ። ሱጳ ደን ራሱ ብዙ ሩቅ አይደለም። 40 ኪሎ ሜትር ነው። ማራኪ ጥቅጥቅ ያለ ደን ነው።

ይህ ሁሉ ኖሮ ግን የአዲስ አበባ ሰው በጭስ ታፍኖ ይገባል - ይወጣል። እነዚህን ተራሮች ድርሽ ብሎባቸው የማያውቅ ሚሊዮን ነዋሪ አለ።

ይህ ነው ለእነ ቢኒያም ፋሽንም ቢዝነስም እየሆነላቸው የመጣው።

ተራራ ላይ ብዙ ሰው የሚዋደደው ለምንድን ነው?

በአዲስ ሃይኪንግ ብቻ በየዓመቱ ከ500 ያላነሰ ሰው ተራራ ይወጣል። ታዲያ ብዙ ሰዎች ቤተሰብ ይሆናሉ። አንዳንዶች ደግሞ በቃ የተራራ ፍቅራቸው ይጋባባቸውና ይጋባሉ።

ሦስት ጉልቻ የመሠረቱ፣ ወልደው የከበዱም አሉ። ከተራራ የጀመረ ፍቅር ከባድ ነው።

ቢኒያም “ለምን እንደሆነ አላውቅም ጉዞ ላይ ሰው ቶሎ ይዋደዳል” ይላል።

ለምን እንደሆነ ባያውቅም ግን መገመት አያቅተውም።

“እኔንጃ ሰዎች በጉዞ ላይ ሲሆኑ መልካም ስሜት ይኖራቸዋል፤ ያ ስሜት መሰለኝ የሚያዋድዳቸው” ይላል።

ለምሳሌ የሆነ ጊዜ ወንዱ የሆነ ጉዞ ላይ መጣ፤ ሴቷ ሌላ ጉዞ ላይ መጣች።

ሁለቱም ሦስተኛ ጉዞ ላይ ተገናኙና አወሩ፤ ተዋወቁ።

አራተኛው ጉዞ ላይ ተጋብተዋል።

“የሆነ ጊዜ ላይ መልዕክት ላኩልኝ። ተጋብተናል፤ እናመሰግናለን” ብለው።

ከትዳር በኋላ ተራራ መውጣት ተው ማለት ነው?

ብቻ ተራራ ላይ ብዙ ሰው ይዋደዳል።

ተራራ ላይ የ‘ታገቢኛለሽ’ ጥያቄ

ቢኒያም በርከት ያሉ የታገቢኛለሽ ጥያቄዎች በጉዞው ላይ ገጥመውታል።

አንኮበር ስንሄድ አንድ ልጅ ጠዋት ተነስቶ “ጥያቄ ላቀርብ አስቤ ነበር፤ አግዙኝ” አለን።

በቃ ምን ማድረግ እንዳለበት አመቻችተን ጠበቅነው።

በአጋጣሚ በጣም ያማረ ሆነለት። ልጅቷም እሺ አለችው።

ምን አረጋችሁለት?

“እሷ ሰልፊ እንድታነሳ እንዲጠይቅ ነገርነው። እሷ ሳታይ ካሜራ አመቻቸን። ከዚያ ሰልፊ እንዲነሱ ጠይቃት አልነው። ቀለበቱን በሰልፊ ካሜራው ውስጥ ስታየው የሚኖራትን ስሜት ለመያዝ ነው የሞከርነው፤ ተሳካልን።”

ልጅቱ ቀለበቱን ስታይ ደንግጣ ፎቶ ማንሳቱን ትታ ነው ወደእሱ የዞረችው እና የሳመችው።

የቢኒያም አንዳንድ አስቂኝ ገጠመኞች

ቢኒያም ባለፉት 10 ዓመታት ብዙ አይቷል። በተራራ መውጣት እና መውረድ ውስጥ የገጠሙትን ሁለት ገጠመኞች እንዲያጋራን ጠየቅነው።

ብዙውን ጊዜ ከጉዞው በፊት ሰዎች ምን መጫማት እንዳለባቸው፤ መያዝ ያለባቸውን ቁሳቁስ ቀድሞ ያሳውቃቸዋል።

ነገር ግን የሃይኪንግ ጫማ ውድ ስለሆነና አቅም የሌለውን ሰው ስሜትም ላለመጉዳት፤ የሚመቻችሁን ጫማ ተጫምታችሁ ኑ ይላል።

“አንድ ልጅ ሹል የሱፍ ቆዳ ጫማ አድርጎ መጣ” ቢኒያም ሳቁ ዛሬም ድረስ አለ።

ሌላኛው ገጠመኙን ርዕስ ስጠው ቢባል፡ ‘አረቄ ጠጥቶ መቆም ያቃተው ልጅ’ የሚል ይሆናል።

ለቢኒያም ምርጡ መዳረሻ አንኮበር እና ጓሣ ነው።

እዚያ ሁለት ቀን አዳር አለ።

ጓሣ ውብ ነው ይላል ቢኒያም። ጓሣን ለቱሪስቶች በማስተዋወቅ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ሞክሼውን ቢኒያም አድማሱን ከፍ አድርጎ ይዘክራል።

ቢኒያም አድማሱ የባሌ ተራራ እሳትን ለማጥፋት ሲታገል ነው በእሳት ተበልቶ የሞተው።

ሞቱን ተከትሎ በርካታ ሽልማቶች እና እውቅናዎች በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ኤምባሲዎች ጭምር ተበርክቶለታል።

“ጓሣ በሄድኩ ቁጥር ስሜ ቢኒያም ነው ስላቸው፣ ገበሬዎቹ ስለ ቢኒያም አድማሱ ያወሩልኛል፤ ስለእሱ መልካምነት አውርተው አይጠግቡም” ይላል።

ወደ ገጠመኙ እንመለስ።

በአንኮበር አካባቢ ለብርዱ አረቄ ማቅረብ ወግ ነው። አንድ የገበሬ ቤት ጎራ ይላሉ። አረቄ ይቀርባል። አብሮት የነበረ ተጓዥ ወጣት ታዲያ ቋ ያረጋል።

የሚገርመው በሕይወቱ ከወተት እና ከውሃ ውጭ መጠጥ ቀምሶ አያውቅም። ሦስት መለኪያ ፉት አለና ያለበትን ረሳ።

“በቃ ራሱን ሳተብን፤ ተደናገጥን፤ የሞተ ነው የመሰለን” ይላል ቢኒያም።

ከዚያ አብረው የነበሩት ተራራ ወጪዎቹ ሁሉም የእኔ የሚሉትን መፍትሄ ሰነዘሩ።

ግማሹ ወተት በአፉ ሲጨምር፤ ግማሹ ክብሪት ሲለኩስ፤ ግማሹ ሲጸልይ ድንገት አረቄ የላፈው ልጅ ብድግ ብሎ ቆመ። እንደ መኪና ‘መንጭቆ ተነሳ።’

ተራራ ወጪዎቹ ሁሉም በደስታ አጨበጨቡ። ለልጁ መቆም እውቅና እንዲሰጣቸው ሽሚያ ውስጥ ገቡ።

“የእኔ ወተት ነው - የእኔ ጸሎት ነው፤ የእኔ ክብሪት ነው ያነቃው፣ ባልዲ ውሃ ባልደፋበት ኖሮ…”

ነገር ግን መንጭቆ የተነሳው ልጅ ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ድንገት በአፍጢሙ ክብንል ብሎ ተደፋ።

ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጠረ። ይህ የሆነው ከአንኮበር ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ጠዋት ላይ በዝግጅት ሳሉ ነበር።

በመጨረሻ ልጁን በፈረስ ጭነው ብዙ ተንገላቱ።

እኩለ ቀን ላይ እንደ ‘አላዛር ተነሳ’ ተባለ። በልጁ ምክንያት የዚያ ሁሉ ተራራ ወጪ ፕሮግራም ተመሰቃቅሎ ከመሸ አዲስ አበባ ደረሱ።

ከዚህ በላይ አስቂኙ ነገር ይላል ቢኒያም “ይህ ከሆነ ከዓመታት በኋላ የገጠመኝ ነገር ነው ነው።”

ምን ገጠመህ?

“አንድ ጋዜጠኛ አንዳንተ ስለ ሃይኪንግ ቃለ መጠይቅ እያደረገልኝ ነው፤ የዚህን ልጅ እና የአረቄውን አስቂኝ ታሪክ አወራለሁ። ካፌ ውስጥ ነበር ቃለ መጠይቁ። እና ድንገት ቀና ስል ጥግ ላይ አንድ ልጅ ማክያቶ ፉት ይላል። ማመን አቃተኝ፤ ያ አረቄ ጠጥቶ ሊሞትብን የነበረው ልጅ ራሱ ነው። እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ይፈጠራል ብዬ ስላላሰብኩ ነገሩ እስከዛሬም ይገርመኛል።”

አገራችን ሰላም ቢሆንልን ኖሮ. . .

ቢኒያም ከዚህ የአረቄ ገጠመኝ ሌላ ባለፉት 10 ዓመታት አንድም ሰው በጉዞ ወቅት አደጋ ስላልደረሰበት ፈጣሪውን ያመሰግናል።

“ስንት ነገር አለ፤ የመኪና አደጋ አለ፤ መታገት አለ፤ ግን እኛ ግን ምንም ደርሶብን አያውቅም” ይላል።

አንድ ጊዜ ብቻ አንዲት ሴት ተራራ ልትወጣ መጣታ ተዝለፍልፋበት ትዝ ይለዋል።

“ለካንስ ወልዳ ከተነሳች ገና 4 ወሯ ነበር፤ አልነገረችንም። በቃ ተሸክመናት ተራራውን ወጣን።”

ቢኒያም ዘግይቶም ቢሆን የነገረን ነገር ይህ የሃይኪንግ ቢዝነስ የሙሉ ጊዜ ሥራው አለመሆኑን ነው።

ባምቢስ በሚገኘው ጥላ ጂም ውስጥ ከፍተኛ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ነው።

ለዚሁ ስልጠና ካናዳ በሄደበት ጊዜ በምሥራቅ ካናዳ ተራሮችን በመውጣት አሳለፈ።

አገሩ ሲመለስ የሙሉ ጊዜ ተግባሩ ሊያደርገው አስቦ ነበር። የአገሪቱ ሰላም አስተማማኝ አልሆን አለው።

እንኳን ለዓመት ለሳምንትም ማቀድም አስፈሪ እየሆነ መጣ።

“ሙሉ በሙሉ ሃይኪንግ ውስጥ ጨክኜ ልገባ እልና እፈራለሁ…። ቱሪዝም ውስጥ የገቡ ጓደኞቼ ራሱ እየወጡ ነው። በዚህ ሁኔታ እንዴት ታቅዳለህ?”