በአየርላንድ በኤቲኤም ስህተት ሰዎች የሌላቸውን ገንዘብ ወጪ አደረጉ

ገንዘብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሪፐብሊክ ኦፍ አየርላንድ ያለው የባንክ ኦፍ አየርላንድ ኤቲኤም ማሽኖች የቴክኒክ ችግር አጋጥሟቸው ደንበኞች ከሚፈቀድላቸው የገንዘብ መጠን በላይ ከኤቲኤም ወጪ ማድረጋቸው ተገለጸ።

ለሰዓታት በቆየው የቴክኒክ ችግር ደንበኞች በ24 ሰዓት ውስጥ ማውጣት ከሚፈቅዳላቸው የገንዘብ መጠን በላይ ወጪ ከማድረጋቸው በተጨማሪ፣ በሂሳባቸው የሌላቸው ገንዘብ ያወጡ የባንክ ደንበኞችም አሉ ተብሏል።

የባንክ ኦፍ አየርላንድ ኤቲኤም ማሽኖች የቴክኒክ ችግር ገጥሟቸው ትርፍ ገንዘብ እየሰጡ መሆኑ ከተሰማ በኋላ፣ በርካቶች ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ከኤቲኤም ማሽኖች ፊት ለፊት ረዣዥም ሰልፍ ሰርተው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ምስሎች አሳይተዋል።

ባንኩ ለሰዓታት የቆየውን የቴክኒክ ብልሽት ማስተካከሉን ገልጾ፣ በቴክኒክ ብልሽት ወቅት ወጪ የተደረጉ ክፍያዎች በሙሉ ከባንክ ደንበኛው ሂሳብ ተቀናሽ ይደረጋል ብሏል።

የባንኩ ቃል አቀባይ በቴክኒክ ችግር ምክንያት ችግር አጋጥሟቸው የነበሩት የባንኩ መተግበሪያ እና የበይነ መረብ (ኦንላይን) ባንኪንግ አገለግሎቶች ወደ ሥራ መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

“ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት አንዳንድ ደንበኞች ከሚፈቀድላቸው መጠን በላይ ወጪ ወይም ወደ ሌላ ሂሳብ ክፍያ መፈጸማቸውን ተረድተናል” ያለው ባንኩ ለተፈጠረው ችግር ደንበኞቹን ይቅርታ ጠይቋል።

የአየርላንድ ፖሊስ በበኩሉ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ባልተለመደ መልኩ በኤቲኤም አካባቢ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ተሰልፍው እንደነበረ ታዝቢያለሁ ብሏል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ዘገባዎች እንዳመላከቱት ሰዎች በኤቲኤም ካርዶቻቸው ካላቸው እና ከሚፈቀድላቸው በላይ ገንዘብ ወጪ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ከሂሳባቸው ወደ ሌላ ባንክ ገንዘብ በማስተላለፍ ከሁለተኛው ወገን ገንዘብ ወጪ አድርገዋል።