ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ የመመለሴ ዕድል “በጣም በጣም ሰፊ ነው” አሉ

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእአአ 2024 ወደ ዋይት 'የመመለሴ ነገር በጣም በጣም ሰፊ ነው' አሉ።

ፕሬዝዳንቱ በአዮዋ ግዛት ለሪፓብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ባደረጉት ንግግር ከሁለት ዓመት በእአአ 2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ “በጣም፣ በጣም፣ በጣም ዳግም ላደርገው እችላለሁ” ሲሉ በቀጣይ ፕሬዝዳንታዊ ውድድር ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ትራምፕ በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሲሰጡ ይህ የመጀሪያቸው አይደለም። ከዚህ ቀደም በፔንሲልቬኒያ እና ቴክሳስ ግዛቶች ዳግም ዕጩ ሆነው ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር።

ትራምፕ ይህን ያሉት በአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመን አጋማሽ ላይ በሚደረገው “ሚድተርም” የምርጫ ቅስቀሳ ለሪፓብሊካን ፓርቲ እጩዎች ቅስቀሳ ባደረጉበት ወቅት ነው።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም በዚህ ምርጫ ድምጽ ለማግኘት ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ።

አሜሪካውያን የፊታችን ማክሰኞ በዚህ የሚድተርም ምርጫ የሚሰጡት ድምጽ በአሜሪካ ኮንግረስ እና ቁልፍ በሆኑ የግዛት አስተዳደሮች ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪም ሚድተርም ምርጫዎች ከሁለት ዓመታት በኋላ ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት የአሜሪካን ፖለቲካ ቅርጽ ሊያስቀይሩ ይችላሉ።

ሪፓብሊኩ ትራምፕ ትናንት ሐሙስ ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግራቸውን ሲያደርጉ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳሉት ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ በ2020 ፕሬዝዳታዊ ምርጫ የተሸነፉት ተጭበርብረው እንደሆነ ተናግረዋል።

“ሁለቴ ተወዳደርኩ (በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ)” ያሉት ትራምፕ፤ “ሁለቱንም አሸንፊያለሁ፤ ከመጀመሪያው በላይ በሁለተኛው በተሻለ መልኩ አጠናቅቂያለሁ፤ በ2016 ካገኘሁበት በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድምጾችን በ2020 አግኝቻለሁ” ያሉት ትራምፕ፤ በ2020 አገኘሁት ያሉት ድምጽ በአሜሪካ ታሪክ የትኛውም ዕጩ ካገኘው በላይ መሆኑን ተናግረዋል። 

“ስለዚህም አሁን አገራችንን ስኬታማ፣ ደኅንነቷ የተጠበቀ እና የከበረች ለማድረግ በጣም፣ በጣም፣ በጣም ዳግም ላደርገው (ልወዳደር) እችላለሁ” ብለዋል። 

ትራምፕ ይህን ሲሉ ታዳሚው በጭብጨባ ድጋፉን ገልጾላቸዋል። ትራምፕም “ተዘጋጁ” ሲሉ መልሰዋል።

 እአአ በ2020 በተካሄደው ምርጫ ትራምፕ 72 ሚሊዮን ድምጽ፤ ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ደግሞ 81 ሚሊዮን ማግኘታቸውን ይፋዊ አሃዞች ያሳያሉ።

ትናንት ሐሙስ በኒው ሜክሲኮ እና ካሊፎርኒያ ቅስሰቀሳ ሲያደርጉ የቆዩት ጆ ባይደን በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ዳግም ለመሳተፍ ከአማካሪዎቻቸው ጋር ስብሰባ ሲቀመጡ መቆየታቸው ተገልጿል።

ይህም ባይደን እና ትራምፕ ዴሞክራት እና ሪፓብሊካን ፓርቲ ወክለው ዳግም በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊፋጠጡ ይችላሉ የሚለውን ግምት ከፍ አድርጓል።

ትራምፕ ሪፓብሊካን ፓርቲ ወክለው ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ ጠንከራ ፈተና ላይገጥማቸው ይችላል። በፓርቲ ውስጥ ትራምፕን ሊቀናቀኑ ከሚችሉት መካከል ምክትላቸው የነበሩት ማይክ ፔንስ እና የፍሎሪዳው ገዢ ሮን ዲሳንቲስ ተጠቃሽ ናቸው።