በኢትዮጵያ በኤምፖክስ በሽታ የመጀመሪያው ሞት ተመዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢትዮጵያ ውስጥ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) ከተያዙ ሰዎች ውስጥ የአንዱ ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ብዛት ስድስት ደርሷል።
የጤና ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ውስጥ በኤምፖክስ በሽታ የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡን ያስታወቀው ቅዳሜ ግንቦት 23/2017 ዓ.ም. ባወጣው ዕለታዊ መረጃ ነው።
ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኤምፖክስ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ያስታወቁት ባለፈው ሳምንት እሁድ ግንቦት 17 ነበር።
በበሽታው የተያዙት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የተገኙት ከኬንያ ጋር በምትጎራበተው ሞያሌ ከተማ አስተዳደር እንደነበር ተገልጿል። በበሽታው የተያዙት የ21 ቀን ዕድሜ ያለው ህጻን ልጅ እና እናቱ እንደሆኑም ሁለቱ ተቋማት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ወደ ጎረቤት ሀገር ተጎዞ ነበር ከተባለው የህጻኑ አባትም ጋር "የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦችን የመለየት እና ክትትል የማድረግ ስራ" መጀመሩንም መግለጫው ጠቅሷል።
በበሽታው የተያዙት "ታማሚው ህጻን እና እናቱ አስቀድሞ በተዘጋጀው የለይቶ ማከሚያ ተገቢው የህክምና ክትትል" እየተደረገላቸው አንደሆነ የጠቀሰው መግለጫው፤ "የከፋ የጤና እክል አልገጠማቸውም" ብሎ እንደነበር ይታወሳል።
በበሽታው ሁለት ሰዎች መያዛቸው ይፋ ከተደረገ በኋላ አንድ ተጨማሪ ሰው በኤምፖክስ እንዳለበት የተረጋገጠው ማክሰኞ ዕለት ነው።
ረቡዕ ዕለት ይህ ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ብዛት ስድስት ደርሷል። ይህ የታማሚዎች ቁጥር እስከ አርብ ድረስ በተመሳሳይ መልኩ መቀጠሉን ጤና ሚኒስቴር በየቀኑ የሚያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ጤና ሚኒስቴር ቅዳሜ ምሽት ባወጣው ዕለታዊ መረጃ በበሽታው ተይዘው ከነበሩ ስድስት ሰዎች ውስጥ የአንድ ግለሰብ ህይወት ማለፉን ይፋ አድርጓል። በበሽታው ተይዘው ከነበሩት ሰዎች መካከል የየትኛው ግለሰብ ህይወት እንዳለፈ ሚኒስቴሩ አልገለጸም።
ከዚህ በተጨማሪ ቅዳሜ ዕለት ብቻ በበሽታው እንደተያዙ በመጠርጠራቸው የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ብዛት ዘጠኝ እንደሆነ ተመላክቷል። ከረቡዕ ዕለት ጀምሮ በአጠቃላይ የተከናወኑ የላቦራቶሪ ምርመራዎች ብዛት ስድስት የነበረ ሲሆን ትናንት የተደረጉት ምርመራዎች ይህንን ቁጥር ወደ 15 አሳድገውታል።

ሞንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox)፤ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ ሽፍታ፣ ሳል፣ የጀርባ እና የጡንቻ ሕመምን እንዲሁም የቆዳ ቁስለት እና ድካም ይታይባቸዋል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት ከተከሰተ በኋላ ከፊት ጀምሮ ቀሪውን የሰውነት ክፍልን የሚያዳርስ እንዲሁም በአብዛኛው በእጅ መዳፍ እና በእግር መረገጫን የሚሸፍን ሽፍታ ያጋጥማቸዋል።
በሰውነት ላይ የሚያጋጥመው ሽፍታ በጣም የሚያሳክክ እና የሚቆጠቁጥ ሲሆን፣ በተለያዩ የለውጥ ደረጃዎች ውስጥ አልፎ በመጨረሻም እብጠት በመፍጠር ኋላ ላይም ይከስማል። ቁስለቱም ጠባሳን ትቶ ሊያልፍ ይችላል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ሆኖ የታወጀው ኤምፖክስ፤ እስከ ባለፈው ሚያዝያ ወር ድረስ ጎረቤት ሀገራት ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንን ጭምሮ በዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት ተከስቷል።
በዚህ የሀገራት ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው ኢትዮጵያ፤ በሽታውን ለመከላከል ሲባል "በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሞ" እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
በበሽታው ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች የሚቆዩባቸው "የተለዩ የጤና ተቋማት" እንደተዘጋጁ እንዲሁም የጤና ተቋማት በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማለም "አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳጠናቀቁ" መነገሩ አይዘነጋም።















