የጽንስ ማቋረጫ መድኃኒትን የፈጠሩት ፈረንሳያዊ ሳይንቲስት አረፉ

ሳይንቲስቱ ኤቲየን ኤሚል ባውሊዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለጽንስ ማቋረጥ እንክብል የፈጠሩት ፈረንሳያዊ ሳይንቲስት በ98 አመታቸው አረፉ።

ሳይንቲስቱ ኤቲየን ኤሚል ባውሊዩ በእንክብል መልኩ መወሰድ የሚችል አር ዩ 486 ወይም ማይፌፕሪስቶን የተሰኘውን የጽንስ ማቋረጫን ያገኙ ናቸው።

መድኃኒቱ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሴቶች በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም ከቀዶ ጥገና ውጭ አማራጭ የሰጠ እንደሆነም ይመሰከርለታል።

ዶክተሩ ባውሊዩ አርብ ዕለት በፓሪስ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸውን ማለፉን ባለቤታቸው አረጋግጠዋል።

"ምርምሩ፤ በሳይንስ መላቅን ለማሳየት ባለው ቁርጠኝነት፣ ለሴቶች ነጻነት ባለው ጽኑ እምነት እና የሰው ልጅ የተሻለ እና ረጅም ዕድሜ እንዲኖር ለማስቻል ባለው ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው" ስትል ባለቤታቸው ሲሞን ሃራሪ ባውሊዪ ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሳይንቲስቱን "የጀግንነት ችቦ" ሲሉ አሞግሰው "ሴቶች ነጻነታቸውን እንዲጎናጸፉ ያስቻለ ባለ ተራማጅ አዕምሮ" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

አክለውም "እሱን ጨምሮ ጥቂት ፈረንሳያውያን ናቸው ዓለምን በከፍተኛ መንገድ መቀየር የቻሉ" ሲሉ ፕሬዚዳንቱ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

የፈረንሳይ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ሚኒስትር አውሮር በርጌ በበኩላቸው ዶ/ር ባውሊው "በህይወቱ ዘመን ሁሉ ይመራ የነበረው በአንድ መርህ ነው፤ ይህም የሰው ልጅ ክብር ነው" ሲሉ ያላቸውን አክብሮት በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ሳይንቲስቱ በአውሮፓውያኑ 1926 በፈረንሳይዋ ስትራስበርግ ተወለዱ።

የናዚን ወረራ በመቃወም በ15 ዓመታቸው ለፈረንሳይ ተሰልፈዋል።

ከተመረቁ በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት የወሊድ መከላከያ ክኒን አባት ከሚባሉት ዶ/ር ግሪጎሪ ፒንከስ ጋር ሰርተዋል።

ፈረንሳይ ከተመለሱ በኋላ የጽንስ ማቋረጫ እንክብሉን የፈጠሩ ሲሆን ይህም አስር ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል። ሳይንቲስት ጽንስን ማቋረጥ ከሚቃወሙ ከፍተኛ ትችቶች እና ዛቻ ቢደርስባቸውም የዓለም መንግሥታት መድኃኒቱን እንዲፈቅዱ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

እንክብሉ እንዲሸጥ በአውሮፓውያኑ 1988 ተቀባይነት ሲያገኝ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከፍተኛ ቅሬታን አስከትሏል።

እስካሁንም ድረስ ጽንስን ማቋረጥ በሚደግፉ እና በሚጻረሩ መካከል እንክብሉ የውዝግብ መንስዔ ሆኖ ቀጥሏል።

መድኃኒቱ ከ100 በሚበልጡ አገራት ቢፈቀድም፣ ማይፌፕሪስቶንም አሁንም አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች በርካታ አገራት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ወይም የተከለከለ ነው።

የዓለም ጤና ድርጀት በአውሮፓውያኑ 2010 ማይፌፕሪስቶንን ወደ አስፈላጊ መድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ አካቶታል።

ዋዮሚንግ የተሰኘችው የአሜሪካዋ ግዛት በአውሮፓውያኑ 2022 የጽንስን ማቋረጫ እንክብሉን የከለከለች የመጀመሪያዋ ግዛት ስትሆን፤ ይህንንም ተከትሎ ዶ/ር ባውሊዩ "ለሴቶች ነጻነት" በርካታ የህይወት ዘመናቸውን እንዳሳለፉ ገልጸው እንዲህ ዓይነቱ እገዳ የተሳሳተ እርምጃ ነው ብለዋል።

ሳይንቲስቱ በቅርብ ጊዜያት ጥናታቸው አተኩሮ የነበረው የአልዛይመር በሽታን ለመከላከል የሚያስችል እንዲሁም የከባድ ድብርት ህክምና ላይ ነበር።