ሥልጣን እንዲያስረክብ የተሰጠው ቀነ-ገደብ ያለፈበት የኒጀር ጁንታ የአገሪቱን የአየር ክልል ዘጋ

በመፈንቅለ -መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው የኒጀር ጁንታ ከሥልጣን እንዲወርድ የተሰጠው ቀነ-ገደብ ማብቃቱን ተከትሎ የአገሪቱን የአየር ክልል ዘጋ።

በረራ በመቆጣጠር የሚታወቀው ፍላይትራዳር24 እንደሚለው በአሁኑ ወቅት በኒጀር ሰማይ ላይ ምንም ዓይነት በረራ የለም።

የምዕራብ አፍሪካ አገራት ማሕበር ኤኮዋስ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም እስከ ትናንት እሑድ ምሽት 5፡00 ሰዓት ድረስ ከእሥር ተለቀው ወደ ስልጣናቸው ካልተመለሱ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ነበር።

የጁንታው ቃል አቀባይ እንዳሉት የኒጀር ጦር ሠራዊት አገሪቱን ለመመከት ዝግጁ ሆነው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ፕሬዝደንት ባዙም ሐምሌ 19 በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ የፕሬዝደንቱ ክቡር ዘብ መሪ የነበሩት ጀኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ አዲሱ የሃገሪቱ መሪ ሆነው ብቅ ብለዋል።

የኒጀር ቅኝ ገዥ የነበረችው ፈረንሳይ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የመንግሥት ግልበጣውን ክፉኛ ተቃውሞታል።

በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ እሑድ ዕለት ንግግር ያሰሙት የኒጀር ጁንታ ተወካይ እንዳሉት “የውጭ ኃይሎች” ኒጀርን ለመወረረው እንደተዘጋጁ መረጃ አለ ብለዋል።

ኤኮዋስ የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ ናይጄሪያ ውስጥ ካደረገ በኋላ የማሕበሩ ወታደራዊ ክንፍ ኃላፊዎች ጦራቸውን ወደ ኒጀር ለመላክ እንዳቀዱ ተናግረው ነበር።

“ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አሟልተናል፤ ቁሳቁስም ይዘናል። እንዴት እና መቼ ነው ጦራችንን የምናስገባው የሚለውንም ወስነናል” ሲሉ የኤኮዋስ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ አብድል-ፋታው ሙሳህ ተናግረዋል።

አክለው “በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ እንፈልጋለን። ይህ መልዕክት ለኒጀር እንዲተላለፍ እንሻለን። ያደረጉትን ነገር እንዲቀለብሱ ሁሉንም አማራጭ እየሰጠናቸው ነው” ብለዋል።

የኤኮዋስ ወታደራዊ ክንፍ ከአንድ ሳምንት በፊት በሰጡት ማስጠንቀቂያ እስከ እሑድ እኩለ-ለሊት ድረስ ጁንታው ከሥልጣን እንዲወርድ ያስቀመጡት ቀነ-ገደብ አሁን ተጠናቋል።

ኤኮዋስ፤ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ቶጎ እና ጋናን ጨምሮ 15 የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የተካተቱበት ቀጣናዊ ድርጅት ነው።

የመፈንቅለ-መንግሥቱ መሪዎች ሥልጣን አሳልፈው ለመስጠት ምንም ዓይነት ፍላጎት ያላቸው አይመስልም።

እሑድ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሜይ በሚገኝ ስታድየም ተሰብስበው ለጁንታው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

የኒጀር ጎረቤት የሆኑት ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ማንኛውም ዓይነት ወታደራዊ እርምጃ ጎረቤታቸው ላይ ቢቃጣ በኛ ላይ “የታወጀ ጦርነት” አድርገን ነው የምንቆጥረው ብለዋል።

ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ የኤኮዋስ አባል ቢሆንም በሁለቱ አገራት በተፈፀመው መፈንቅለ-መንግሥት ምክንያት ከማሕበሩ ታግደዋል።

ዩራኒየም የተሰኘው ለኒውክሌር ኃይል እጅግ አስፈላጊ የሆነ ማዕድን የበለፀገችው ኒጀር ፕሬዝደንት የነበሩት ባዙም ከምዕራባዊያን ጋር ጥልቅ ቁርኝነት ነበራቸው።