አክራሪው የጀርመን ፓርቲ ‘መጤዎችን’ በሙሉ ከጀርመን ለማባረር መምከሩ ቁጣን ቀሰቀሰ

አክራሪው ፓርቲ የጀርመን ዜግነት ያላቸው ጭምር እንዲባረሩ ይፈልጋል

የፎቶው ባለመብት, INA FASSBENDER /AFP

የምስሉ መግለጫ, አክራሪው ፓርቲ የጀርመን ዜግነት ያላቸው ጭምር እንዲባረሩ ይፈልጋል

በጀርመን ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ ‘መጤዎችን’ ጠራርጎ ከአገሪቱ ለማባረር መምከሩን ተከትሎ በርካቶች ቁጣቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጡ።

መንግሥት ይህን ፓርቲ ከፖለቲካ መድረክ ለማገድ በሚቻልበት ሁኔታ እየተነጋገረ ነው።

‘አማራጭ ለጀርመን’ ወይም በምሕጻሩ ኤኤፍዲ (AfD) የሚባለው ይህ የቀኝ አክራሪ ፓርቲ በር ዘግቶ የተወያየው ስደተኞችን በተለይም ከጀመርን ሕዝብ ጋር ያልተቀላቀሉ፣ ቋንቋ ያልቻሉ፣ የጀርመን ዘር ግንድ የሌላቸውን ለቅሞ ከጀመርን በሚባረሩበት ሁኔታ ላይ ነው።

ፓርቲው 'መጤ' ብሎ ካስቀመጣቸው ውስጥ ቋሚ የመኖርያ ፍቃድና የጀርመን ዜግነት ያላቸውንም ይጨምራል።

ለብዙ ጀርመናዊያን ዜናው ይበልጥ አስደንጋጭ የሆነው በዚህ የቀኝ አክራሪ ፓርቲ ምሥጢራዊ ጉባኤ ላይ ጉምቱ የጀርመን ፖለቲከኞች ሳይቀሩ መገኘታቸው ነው።

ይህ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ በአገሪቱ ከፍተኛ ድምጽ እያገኘ የመጣ ፓርቲ ሲሆን በሕዝብ የፖለቲካ ትርታ መለኪያ በጀርመን 2ኛው ተመራጭ ፓርቲ ነው።

ይህ በበርሊን አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ተደረገ የተባለ ዝግ ስብሰባ 20 ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የናዚ ደጋፊዎች ተገኝተውበታል።

የቀድሞዋ መርሒተ መንግሥት አንጌላ መርከል ፓርቲ፣ ክሪስቲያን ዲሞክራት (ሲዲዩ) በዚህ ጉባኤ ሁለት አባላቱ መገኘታቸው መጋለጡ ሕዝቡን ይበልጥ ቁጣ ውስጥ ከቶታል።

በጉባኤው ዋንኛው መነጋገሪያ የነበረው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጀርመን ደም የሌላቸው ስደተኞችን እንዴት ለቃቅሞ ወደመጡበት መመለስ ይቻላል የሚል ነበር ተብሏል።

‘መጤዎችን’ ከጀርመን ጠራርጎ የማስወጣቱ እቅድ ቋሚ የመኖርያ ፈቃድና ጀርመናዊ ዜግነት (ፓስፖርት) ያላቸውንም የሚጨምር ነው።

ይህ ምሥጢራዊ ጉባኤ ከተጋለጠ በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቁጣቸውን ለመግለጽ ትእይንተ ሕዝብ እያደረጉ ነው።

በተለይም በበርሊንና በሐምቡርግ፣ በዶርትሙንድ እና በፍራንክፈርት በድምሩ ከ300ሺህ ሕዝብ በላይ አደባባይ ወጥቷል።

“ደንግጫለሁ፣ ከዚህ በኋላ እዚህ የመኖር እቅድ የለኝም። ደኅንነት አይሰማኝም። ከጀርመን መውጣት እፈልጋለሁ” ብሏል አንድ ቤተሰቡ ከደቡባ አሜሪካ የመጣ ጀርመናዊ ዜጋ ለቢቢሲ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተቃውሞ ትእይንተ ህዝቡ ከመቶ በላይ ከተሞች ዛሬ እሑድ ቀጥሎ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

መራሒ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ለተቃውሞ ሰልፈኞቹ ምስጋና አቅርበዋል።

‘አማራጭ ለጀርመን’ ወይም በምሕጻሩ (ኤኤፍዲ) ፓርቲ ቀኝ አክራሪ ሲሆን የፓርቲው መሪ አሊስ ዋይድል ይህ በምሥጢር ተደረገ የተባለው ጉባኤ ፓርቲው ያላሰናዳው ስብሰባ ነው በማለት ራሳቸውን ከጉዳዩ ለማራቅ ሞክረዋል።

‘የጀርመን ዜግነት የያዘ ሰው የኛው ሰው አድርገን ነው የምንቆጥረው፤ ለዚያም ነው ፓስፖርቱ ለማንም መዥረጥ ተደርጎ መሰጠት የለበትም የምንለው” ብለዋል።

ከዚህ በተረፈ ፓርቲያቸውን ለማገድ የሚደረግ እንቅስቃሴን አጥብቀው አውግዘዋል።

መጤዎችን ጠራርጎ የማባረር እቅድን የነደፈው የኦስትሪያው ቀኝ አክራሪ ማርቲን ሴልነር እንደሆነ ታውቋል።

እቅዱ በሰሜን አፍሪካ አንድ ሞዴል አገር መመሥረትና 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ‘መጤዎችን’ ወደዚያ ወስዶ የማስፈር ዝርዝር መርሐ ግብር የያዘ ነው።

ይህ ግለሰብ ዩኬ ከዚህ ቀደም አገሯ እንዳይገባ አግዳዋለች።

‘ኦልተርኔቲቭ ፎር ዶችላንድ’ የሚባለው ይህ ፓርቲ ከፖለቲካ ተሳትፎ መታገድ አለበት የሚለው ክርክር አሁን በጀርመን ሰፊ መነጋገሪያ ሆኗል።

ይሁንና ሰፊ የሕዝብ ተቀባይነት ያለውን ፓርቲ ከፖለቲካ መድረክ ማገድ ይቻላል ወይ የሚለው ሌላ መነጋገሪያ ሆኗል።

ይህ ፓርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሆኑ ደግሞ ሌላ አዲስ ስጋት ፈጥሯል።

ፓርቲው ሰኔ ላይ በሚደረገው የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ሊያሸንፍ እንደሚችል ይገመታል። በቀጣይ በጀመርን ምርጫም በርካታ ወንበሮችን ሊያሸንፍ እንደሚችል ይጠበቃል።

የጀርመን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ናንሲ ፋእዘር ዲሞክራሲያችንን ለመከላከል የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም ሲሉ በዚህ አክራሪ ፓርቲ ላይ አንዳች ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድበት ፍንጭ ሰጥተዋል።

በ1940ዎቹ በጀርመን የናዚ ፓርቲ በተመሳሳይ መልኩ 4 ሚሊዮን አይሁዶችን ወደ ማዳጋስካር ወስዶ ለማስፈር በሚቻልበት ሁኔታ ተወያይቶ ነበር።

ይህ ሐሳብ እየዳበረ ሄዶ ነው በ1942 ዓ/ም አይሁዶችን ከአውሮፓ ምድር ጨርሶ ለማጥፋት የዘር ማጥፋት እቅድ የጸደቀው።

አሁንም ተቀራራቢ ምልክቶች በጀርመን እየታዩ በመሆኑ ነው ድንጋጤና ቁጣ የተፈጠረው።