"የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ መሆን የለበትም" - የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን

የፎቶው ባለመብት, Presidency of the Republic of Türkiye
ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አገራቸው በአፍሪካ ቀንድ "አዲስ ግጭቶች እና ሕመም መመልከት" እንደማትፈልግ እንዲሁም ቀጣናው "የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ" መሆን እንደሌለበት ተናገሩ።
የቱርኩ ፕሬዝዳንት አክለውም፤ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና "ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም" አይኖረውም ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ የተነገረላቸው የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ይህንን ያሉት ትናንት ማክሰኞ የካቲት 10/2018 ዓ. ም. በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።
ኤርዶዋን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጋራ መግለጫ የሰጡት፤ "ዘለግ ያለ ውይይት" እንዳደረጉ ከተገለጸ በኋላ ነው።
ከ11 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው መደሰታቸውን የገለጹት የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን፤ ሁለቱ አገራት እንደ ባቡር እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ ፋብሪካዎች እንዲሁም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ባሉ ዘርፎች ላይም ትብብር እንዳላቸው አንስተዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ "ኢትዮጵያ በእስልምና ባህል ውስጥ የማይተካ ሚና" እንዳላት ጠቅሰዋል። ቱርክ "ከወዳጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያላትን ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበት ትልቅ ትኩረት" እንደምትሰጥም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ "የመላው ዓለም ዐይን ወደ የአፍሪካ ቀንድ በዞረበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የቆየ የመንግሥት መዋቅር እና ተምሳሌትነት ያለው አስተዳደር ይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል" ብለዋል።
ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር "በእኩል አጋርነት እና በጋራ መግባባት" ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደሚያደርጉ እንዲሁም አገራቸው ከቀጣናው ሕዝብ ጎን እንደምትቆም ገልጸዋል።
ቱርክ በዚህ ቀጣና አዲስ ግጭት እንዲነሳ እንደማትፈልግም ኤርዶዋን በንግግራቸው አስገንዝበዋል። "ቱርክ፤ ቀድሞውንም ስቃይ በደረሰበት በዚህ ቀጣና ውስጥ አዲስ ግጭቶች እና አዲስ ሕመም ፈጽሞ መመልከት አትፈልግም" ብለዋል።
"የዚህ ቀጣና ችግሮች በራሳቸው በቀጣናው አገራት ሊፈቱ እንደሚገባ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ መሆን እንደሌለበት እናምናለን" ሲሉም የቱርክን አቋም ገልጸዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ካደረጉት ጉዞ "አዎንታዊ ውጤት" ይገኛል ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ኤርዶዋን፤ ጉብኝታቸው "ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት አስተዋጽኦ" ይኖረዋል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ጠቅሰዋል።
ቱርክ፤ ኢትዮጵያ በምትገኝበት አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ በተለይም "ለአገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ትኩረት እንደምንሰጥ" ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን አንስተዋል።
"በዚህ ረገድ እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷ ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም እንደማይኖረው በድጋሚ መግለጽ እወዳለሁ" ሲሉ እስራኤል ታኅሣሥ መጨረሻ የወሰደችውን እርምጃ በድጋሚ ተችተዋል።
ለሶማሊላንድ ዕውቅና ያስገኛል የተባለው የአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ ስምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከተካረሩ በኋላ በቱርክ አሸማጋይነት መስማማታቸውንም ከዚሁ ጋር አያይዘው አንስተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Presidency of the Republic of Türkiye
ፕሬዝዳንቱ፤ "መረጋጋት መመለሱን ተከትሎ፤ የአፍሪካ ቀንድ በኢኮኖሚያዊ ዕድሎቹ ትኩረትን የሚስብ ሥፍራ እንዳይሆን የሚከለክለው ምንም ዓይነት እንቅፋት አይታየንም" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው "የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ንግግር በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች" መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። ዐቢይ ንግግር እንደተደረገባቸው ከገለጿቸው ጉዳዮች አንዱ የባሕር በር ጉዳይ ነው።
ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች እንደሆነ ገልጸው፤ "የዚህ ዕድገት ቀጣይነት መረጋገጥ የሚችለው" አገሪቱ የባሕር በር ማግኘት ስትችል እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር የባሕር በር ተከልክላ፣ በዓለም ላይ ካለው ልምምድ እና አካሄድ ውጪ በጠላቶቻችን ደባ ለረዥም ጊዜ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና እንድትቆይ መደረጉ ትክክል አለመሆኑን [ተወያይተናል]" ብለዋል።
ኢትዮጵያ "በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር" እንድታገኝ "እንደ ቱርክ ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጆች በዲፕሎማቲክ መስኩ ጫና በመፍጠር" እገዛ እንዲያደርጉ መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።
ዐቢይ አክለውም፤ "ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ከዚህ አንጻር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠንከር ያለ ውይይት አድርገናል" ብለዋል።
ኤርዶዋንን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን "በደንብ የሚገነዘቡ" ሲሉ የገለጹት ዐቢይ፤ ፕሬዝዳንቱ "በዚህ ቀጣና ውስጥ ኢትዮጵያ ሁነኛ (anchor) አገር መሆኗን እና ሚናዋን መወጣት እንዳለባት የሚያምኑ" እንደሆኑም ተናግረዋል።
"ቱርክ ከአውሮፓ አንጻር እና በእስያ መካከል ባላት ጉልህ ጂኦግራፊ እና የኢኮኖሚ ሚና የአፍሪካ ዕድገት ውስጥ የበኩሏን ሚና እንድትጫወት ብዙ ውይይት አድርገናል፤ ተግባብተናል" ብለዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች የአገራቱን የንግድ ግንኙነት ለማስፋፋት እንደተስማሙ ተገልጿል። በኢትዮጵያ እና በቱርክ መካከል ያለውን ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ መጠን "ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር መሙላት እንዲችል" ማድረግ እንደሆነ ዐቢይ ተናግረዋል።
የፀረ ሽብር ትግል እና እንዲሁም የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤን (ኮፕ) በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መነጋገገራቸውንም አክለዋል።















