ሰሜን ኮሪያ ረዥም ርቀት የሚጓዝ የተከለከለ ባለስቲክ ሚሳኤል መተኮሷ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል መተኮሷን ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን አስታወቁ።
ሚሳዔሉ ለ86 ደቂቃዎች ያክል ተምዘግዝጎ በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል በኩል ውቅያኖስ ላይ መውደቁን እና ይህም ከዚህ በፊት ተሞክሮ እንደማያውቅ ሀገራቱ ገልፀዋል።
አፍንጫውን ወደሰማይ ቀስሮ የተተኮሰው አይሲቢኤም የተባለው ሚሳዔል ወደ ላይ 7 ሺህ ኪሎ ሜትር ደርሶ እንደተመለሰ ተሰምቷል። ይህ ማለት ወደ ጎን ቢተኮስ ከዚህም ያለፈ ርቀት ሊጓዝ ይችል ነበር።
ሐሙስ ዕለት የተተኮሰው ሚሳዔል የተባበሩት መንግሥታትን ሕግ የሚጥስ ነው።
በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነት እጅጉን የሻከረ ሲሆን ፒዮንግያን በሴዑል ላይ የተለያዩ ትንኮሳዎችን እየፈጸመች ነው ተብላ ትወቀሳለች።
ደቡብ ኮሪያ፤ ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ ምርጫ ቀን ሲቃረብ አይሲቢኤም የተባለውን ሚሳዔል ልትተኩስ ትችላለች ስትል ረቡዕ ዕለት መግለጫ አውጥታ ነበር።
የአሜሪካ ምርጫ በቀጣዩ ሳምንት ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ይካሔዳል።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው የሚሳዔል ሙከራው ከዚህ በተሻለ “ርቀት እና ከፍታ” ያለው ሚሳዔል ለማዳበር የተደረገ ነው።
በሚሳዔል ሙከራው ቀን በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ መግለጫ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሙከራው “ለጠላቶቻችን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ያሳያል” ብለው “ተገቢ ወታደራዊ ምላሽ” መሆኑን ገልፀዋል።
“ላረጋግጥላችሁ የምወደው [ሰሜን ኮሪያ] የኒውክሌር አቅሟን ከማዳበር ወደኋላ እንደማትል ነው” ብለዋል ኪም።
ዩናይትድ ስቴትስ የሐሙሱን የሚሳዔል ሙከራ “የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሕግጋትን የጣሰ ነው” ብላለች።
የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ሾን ሳቬት “ሰሜን ኮሪያ ከዜጎቿ ደኅንነት ይልቅ ሕጋዊ ያልሆኑ ጅምላ ጨራሽ እና ባለስቲክ ሚሳዔሎች ለማብላላት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ያሳየ ድርጊት ነው” ብለዋል።
ደቡብ ኮሪያ የሚሳዔል ሙከራውን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደምትጥል አስታውቃለች።
ፒዮንግያንግ ለመጨረሻ ጊዜ መሰል ባለስቲክ ሚሳዔል የተኮሰችው በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2023 ነው። በወቅቱ የመንግሥታቱን ውሳኔ በመጣሷ ብዙ ወቀሳ ደርሶባት ነበር። ሚሳዔሉ ለ73 ደቂቃዎች የተመዝገዘገ ሲሆን 1000 ኪሎ ሜትር ተጉዟል።
ፒዮንግያን የምታብላላው ሚሳዔል “መሐል አሜሪካን ለመታት የሚያስችል ነው” ይላሉ የሰሜን ኮሪያ አጥኚው ኪም ዶንግ-ያፕ።
ጃፓን የሐሙሱን የሚሳዔል ሙከራ ስትከታተል እንደነበር ስታስታውቅ የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት “ከባድ እርምጃ ለመውሰድ” ተስማምተዋል።
ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ፤ ፒዮንግያንግ ወታደሮቿን ወደ ሩሲያ በመላክ ፕሬዝደንት ፑቲን ዩክሬን ላይ ለሚያካሂዱት ጦርነት ድጋፍ አድርገዋል ሲሉ በቅርቡ መውቀሳቸው ይታወሳል።
ፔንታገን እንደሚለው ሰሜን ኮሪያ ወደ ምስራቅ ሩሲያ 10 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቿን ልካለች።
ሰሜን ኮሪያም ሆነች ሩሲያ ስለዚህ ጉዳይ እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።












