ጉግል የመረጃ ፍለጋ ገበያውን ብቻውን መቆጣጠሩ ሕጋዊ አይደለም ሲሉ አሜሪካዊው ዳኛ ወሰኑ

የጉግል አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊው ዳኛ ጉግል የተባለው የበይነ መረብ መረጃ ማሰሻ ተፎካካሪዎቹን በልጦ ብቻውን ገበያውን መቆጣጠሩ ሕጋዊ አይደለም ሲሉ ወስነዋል።

በዓይነቱ የመጀመሪያው የተባለው ይህ ውሳኔ የጉግል ኩባንያ ባለቤት ለሆነው አልፋቤት የተሰኘው ተቋም ትልቅ ኪሳራ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ነው በአውሮፓውያኑ 2020 ጉግል 90 በመቶ የሚሆነው የበይነ መረብ ፍለጋ ተቆጣጥሮታል ሲል ክስ ያቀረበው።

ጉግል በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ ክስ ከቀረበባቸው በርካታ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አንዱ ሲሆን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢንዱስትሪው ፉክክር ያለበት እንዲሆን ይፈልጋሉ።

ይህ ክስ በበይነ መረብ የመረጃ ፍለጋ እና በኦንላይን ማስታወቂያ ቁጥር አንድ የሆነው ጉግል እና ባለቤቱ ኅልውና ላይ የተቃጣ ነው ተብሎ ሲነገር ቆይቷል።

አልፋቤት እና ጉግል ምን ዓይነት ቅጣት ይጠብቃቸዋል የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም። ድርጅቱ የሚቀጣው ቅጣት ወደፊት በሚደረጉ ችሎቶች ይታወቃል ተብሏል።

የአሜሪካ መንግሥት የጠየቀው “የአሠራር ለውጥ” እንዲመጣ ነው። ይህ ማለት ወደፊት ምናልባት ድርጅቱ እንዲከፋፈል ግድ ሊለው ይችላል ማለት ነው።

አሜሪካዊው ዳኛ አሚት ሜህታ ውሳኔያቸውን ሲያሳልፉ ጉግል በተንቀሳቃሽ ስልኮችም ሆነ በሌሎች በይነ መረብ መጎብኛዎች ትልቁ የመረጃ ፍለጋ መሣሪያ ለመሆን በሚል በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ከፍሏል ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ጉግል ሁሉን ጠቅልሎ የያዘ ነው። ይህንን “ሞኖፖሊ” ማስቀጠል ይፈልጋል ሲሉ ዳኛ ሜህታ 277 ገፅ ባለው ውሳኔያቸው ላይ ፅፈዋል።

የጉግል ባለቤት የሆነው አልፋቤት ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ አሳውቋል።

“ይህ ውሳኔ የሚያረጋግጠው ነገር ቢኖር ጉግል ምርጡ የመረጃ ፍለጋ ማዕከል መሆኑን ነው። ነገር ግን በቀላሉ ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ አትችሉም እየተባልን ነው” ይላል ኩባንያው የለቀቀው መግለጫ።

የአሜሪካው አቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ “ለአሜሪካዊያን ታሪካዊ ድል ነው” ሲሉ የዳኛውን ውሳኔ አድንቀዋል።

“የትኛውም ኩባንያ፤ ምን ያክል ግዙፍ አሊያም ተፅዕኖ ፈጣሪ ቢሆን ከሕግ በላይ አይደለም ብለዋል አቃቤ ሕጉ ሰኞ በለቀቁት መግለጫቸው።

የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ፣ አማዞን እና አፕልን የመሳሰሉ ግዙፍ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ገበያውን በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል ተብለው ከተከሰሱ መካከል ናቸው።

ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ለ10 ሳምንታት ያክል ጉዳዩ በችሎት ፊት ከታየ በኋላ ነው ሰኞ ዕለት ጉግል ለአፕል፣ ሳምሰንግ፣ ሞዚላ እና ሌሎች ኩባንያዎች ቢሊዮን ዶላሮች ከፍሎ ብቸኛው የመረጃ ፍለጋ ድር ለመሆን ሞክሯል ዳኛው ውሳኔ ያሳለፉት።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ጉግል የመረጃ ፍለጋ ገበያውን ለመቆጣጠር በዓመት ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር ይከፍላል፤ ይህ ደግሞ በገበያው ያለውን የበላይነት እያሰፋው የመጣ ጉዳይ ነው።

ባለሥልጣናቱ አክለው እንደሚሉት ጉግል ይህን በማድረጉ ሌሎች ተፎካካሪ የሚባሉ ድርጅቶች አቅምና ዕድል እንዳያገኙ ሆነዋል።

የጉግል የመረጃ መፈለጊያ ድር ለኩባንያው ዋና የገበያ ምንጭ ሲሆን ምስጋና ‘ጉግል ሰርች’ ላይ ለሚታዩ ማስታወቂያዎች ይሁንና በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላሮች ያጋብሳል።

የጉግል ጠበቃዎች ሰዎች የጉግልን የመረጃ መፈለጊያ ድር የሚወዱት ለአጠቃቀም ምቹ ስለሆነ ነው፤ በዚህ ምክንያት ጉግል ደግሞ የበለጠ ምቹ ለማድረግ መዋዕለ ንዋይ ያፈሳል ሲሉ ተከራክረዋል።

“ጉግል እያሸነፈ ያለው የተሻለ ስለሆነ ነው” ብለዋል የጉግል ጠበቃ ጆን ሽሚድትላይን ችሎቱ ላይ ባቀረቡት የመዝጊያ ንግግራቸው።

ኩባንያው የማስታወቂያ ቴክኖሎጂን በተመለከተ ሌላ ክስ የሚጠብቀው ሲሆን ችሎቱ በሚመጣው መስከረም ይከፈታል። ጉግል ገበያውን ተቆጣጥሮታል ተብሎ አውሮፓ ውስጥ መቀጣቱ ይታወሳል።