አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “አካታችነት እና ግልጸኝነት ይጎድለዋል” በሚል ካርድ ፊርማ ማሰባሰብ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, ENDC/FB
የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር አልሞ በ2014 ዓ.ም. የተመሠረተው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የአካታችነት እና የግልጸኝነት” ክፍተቶች እንደታዩበት አስተወቀ።
አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የሆነው ካርድ አደረኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት ኮሚሽኑ ካስቀመጣቸው 11 መርሆዎች ውስጥ “ከፊት ያስቀመጣቸውን ሁለቱን መርሆዎች እየጣሰ ነው” ብሏል።
ድርጅቱ ኮሚሽኑ ከአመሠራረቱ ጀምሮ እስከ ሂደቱ ድረስ “ጉልህ ክፍተቶች” እንደታዩበት ገልጾ፤ ማስተካከያ እንዲያደርግ የሚወተውት ፊርማ እያሰባሰበ ነው።
ባለፈው ሳምንት Change.org በተባለው ድረ ገጽ ላይ በወጣው የማስተካከያ ጥሪ ኮሚሽኑ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ሳይፈቱ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ቅቡልነቱን ያጣል የሚል “ከፍተኛ ስጋት” እንዳለው ገልጿል።
የካርድ የፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር መንግሥቱ አሰፋ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ሲወጣ እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉ ባለድርሻ አካላት “በቂ ምክክር” አልተደረገበትም ሲሉ የመጀመሪያ ያሉትን ጉድለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኮሚሽነሮች አመራረጥም ከጅማሮው አንስቶ “ግልጸኝነት የጎደለው ነው” ያሉት ኃላፊው፤ ለዚህም ማሳያ የሚያነሱት ዕጩ ኮሚሽነሮች የተመረጡበት መስፈርት ግልጽ አለመሆንን እንዲሁም ይፋ በሆነው የመጨረሻ ዝርዝር ላይ ያልተካተቱ ኮሚሽነሮች መሰየምን ነው።
“የዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ የገቡ 42ቱ ኮሚሽነሮች በምን መስፈርት ነው [የተመረጡት] የሚለው ግልጽ አይደለም። ዝርዝር ውስጥ የገቡት ሁሉንም የሚያስማማ ወይም ደግሞ ሁሉን የሚያሳምን በሆነ ሁኔታ አይደለም። በኋላ ደግሞ እዚህ ዝርዝር ውስጥ የሌሉ ሰዎች የኮሚሽኑ አባል ሆነው የተሾሙበት ጊዜ አለ” ሲሉ የግልጽነት መጓደልን ያነሳሉ።
አካታች ምክክር ለማድረግ “አስቻይ የፖለቲካ ሁኔታ” መፈጠር አለበት የሚሉት የፕሮግራም ኃላፊው፤ ለዚህም ተገለሉ የሚሏቸውን ኃይሎች በመጥቀስ ስጋት አድሮብናል ይላሉ።
የምክክር ኮሚሽኑን በይፋ የተቃወሙ ከ10 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ” በሚል ጥምረት መሥርተው በዋነኛነት የገለልተኝነት ጥያቄ ያነሳሉ።
ከ40 በላይ ከሚሆኑ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት እየሠራሁ ነው የሚለው ኮሚሽኑ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን አቋም “ዳር ሆኖ ቆሞ ማየት ነው” ብሎታል።
የአገሪቱ የፖለቲካ እና የግጭት ዐውድ አካታች የሆነ ምክክር ለማድረግ አስቻይ መሆን ላይ ጥያቄ የሚያነሱት የካርድ ፕሮግራም ኃላፊው፤ ዐውዱ የገፋቸው እና ከመንግሥት ጋር የትጥቅ ግጭት እያደረጉ ያሉ ኃይሎችን ያገለለ አገራዊ ምክክር ስኬታማነቱ ላይ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
“. . . ሲንከባለሉ የነበሩ መሠረታዊ አለመግባባቶችን ለመፍታት ከታሰበ አካታችነቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓተ ፆታን ማመጣጠን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸው አካላት፣ ግጭት ውስጥ የሚሳተፉ እና በኋላ ላይ ካላቸው ጥያቄ እና ስጋት የተነሳ ራሳቸውን ከሂደቱ ያገለሉ ሰዎች በተገለሉበት ሁኔታ ውጤታማ ምክክር ማድረግ እና ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት ይቻላል ወይ?” ሲሉ የአካታችነት፣ የግልጸኝነት እንዲሁም የተዓማኒነት ጥያቄን ያነሳሉ።
ባለፈው መጋቢት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለምክክሩ ውጤት የታጣቂዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ከታጣቂዎች ጋር ለመምከር ኮሚሽኑ “የሰላም መንገድ” (ደኅንነት ዋስትና) እንደሚያመቻች ተናግረዋል።
“በሰላም ወደ ምክክሩ መጥቶ፤ ተሳትፎ ወደ መግባባት በሚኬድበት ሂደት ውስጥ በመንግሥት በኩል፤ በሕጉ በኩል የሚደረጉ ጫናዎች ካሉ አዋጁ በሰጠን ሥልጣን መሠረት ከመንግሥት ጋር ተነጋግረን የሰላም መንገድ የሚባለውን ነገር ማመቻቸት እንችላለን” ብለዋል።
ካርድ በጥሪው ኮሚሽኑ ለታጣቂ ቡድኖችን በመገናኛ ብዙኃን ከሚያቀርባቸው ጥሪዎች ባሻገር በይፋ የተነደፈ ዕቅድ አለመኖሩን፤ ካለም ግልጽ አለመደረጉን በመጥቀስ ይህም ምክክሩ ግቡን እንዳይመታ ያደርገዋል ብሏል።
ድርጅቱ በኮሚሽኑ የውክልና ቅሬታ ያነሱ የሃይማኖት ተቋማትንም ጉዳይ የጠቀሰ ሲሆን፤ “ያልተመጣጠነ ተሳትፎ እና ተጽዕኖ” ሲል የገለጸውን ጉዳይንም በሌላ ስጋትነት አንስቷል።
ከግንቦት 21/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የተደረገውን የአዲስ አበባ የአጀንዳ ልየታ መርሃ ግብርን ለአብነት አንስቶ፤ “በብዙዎቹ ቡድኖች ውስጥ የመንግሥትን አቋም የሚያንጸባርቁ ተሳታፊዎች የተመደቡባቸው ናቸው” ብሏል።
በዚሁ መርሃ ግብር የመንግሥት ወይም የገዢውን ፓርቲ ተወካዮች በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካይነት በማሳተፍ “ያልተመጣጠነ ውክልና” እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን በመጠቆም፤ አጀንዳ መለየቱን ወደ አንድ አካል እንዳያደላ የሚያደርግ የቁጥጥር አሠራር ሊኖር ይገባል ሲል አመልክቷል።
የምክክር ኮሚሽኑ በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የአጀንዳ ልየታ ምዕራፍ፣ 121 የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ 228 የተቋማት እና የማኅበራት ተወካዮች፣ 128 የመንግሥት አካላት ተወካዮች፣ 52 የፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ 16 የፓለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም 11 የውይይት አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል።
የተወካዮችን ትክክለኛ ወኪልነት የሚያነሱት ዶ/ር መንግሥቱ አሰፋ “በዘጠኝ ቡድን ከፍለው ተሳታፊዎችን ሲመርጡ በምን መስፈርት ነው? የሚለው በግልጽ የተቀመጠ፤ ለሕዝብ የተነገረ፤ ሰውን ያሳመነ ነው ብለን አናስብም” ሲሉ ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር በአዲስ አበባው መርሃ ግብር መክፈቻ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግርን የጠቀሰው ካርድ፤ እንዲህ ዓይነት አቋሞች የኮሚሽኑን ተዓማኒነት እንደሚጎዳው ጠቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመድረኩ ላይ የመንግሥታቸውን ቀይ መስመር አመልካች ነው የተባለ የሽግግር መንግሥት ምሥረታን ጉዳይ አንስተው፤ “በኢትዮጵያ ከእንግዲህ የሽግግር መንግሥት አይኖርም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሚኖረው በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ብቻ ነው” ብለዋል።
ይህ ንግግራቸውም ለአገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሄ ያበጃል የተባለው የምክክር ጉባኤ ሊደርስበት የሚችለው ውጤት ላይ ተጽዕኖ የሚደርግ አሊያም ውሳኔን የሚያዳክም ተደርጎ ታይቷል።
የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የዘረዘራቸው የአካታችነት እና የግልጽነት ቅሬታዎች ምክክሩ የብዙኃን ተቀባይነት እንዳይኖረው ሊያደርግ ይችላል የሚል “ከፍተኛ ስጋት” አድሮብኛል ብሏል።
“በእንደዚህ ዓይነት ክፍተቶች የታጀበ ሂደት መጨረሻው የቅቡልነት ጥያቄ ከብዙ ቦታዎች [ወገኖች] እንደሚነሳበት ነው የእኛ ስጋት” ብለዋል።
ድርጅቱ ይህን ስጋቱን የሚጋሩ አካላትን በማሰባሰብ ኮሚሽኑ እርምት እንዲወስድ እንደሚጠይቅ የተናገረ ሲሆን፤ የሥራ ዘመኑን ለማጠናቀቁ ከአንድ ዓመት በታች ጊዜ የቀረው ኮሚሽን ይህን ለማድረግም አልረፈደበትም ብሏል።
ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ የኮሚሽኑን ሃሳብ ለማካተት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ ከሳምንት በላይ ቢጠብቅም ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።












