'አጠራጣሪ' የተባለው ታዋቂው የሆሊውዱ ተዋናይ እና ባለቤቱ አሟሟት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አስከሬናቸው በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘው ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ እና ባለቤቱ 'አሟሟታቸው' አጠራጣሪ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።
የኒው ሜክሲኮ ፖሊስ ይህንን ያለው ከሞቱ የቆዩ መሆኑን የሚመስሉ ምልክቶች በአስከሬናቸው ላይ መታየቱን ተከትሎ መሆኑን ገልጿል።
የኦስካር ሽልማቶች አሸናፊውና የ95 አመቱ ሄክማን አስከሬን የተገኘው ከማዕድ ቤቱ አጠገብ በምትገኝ አነስተኛ ክፍል ሲሆን የ65 ዓመቱ ባለቤቱ ቤትሲ አራካዋ ደግሞ በመታጠቢያ ቤታቸው ውስጥ ነው።
ባለስልጣናቱ በአስከሬናቸው ላይ ምንም አይነት የጉዳት ምልክት ባያገኝም 'አሟሟታቸው አጠራጣሪ እንደሆነ ገልጾ በዚህም ምክንያት ምርመራ ከፍቻለሁ ብሏል።
አክሎም ከተፈጥሯዊ ውጭ በሆነ ምክንያት ህይወታቸው አልፎ ይሆን? የሚለውንም ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ተናግሯል። እስካሁን ለሞታቸው መንስዔ የሚሆን ምክንያት አልተሰጠም።
ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ በተዋናይነት የተጫወተው ዝነኛው ሃክማን 'ዘ ፍሬንች ኮኔክሽን' 'እንዲሁም 'አንፎርጊቭን' በተሰኙ ፊልሞቹ ዝናው ናኝቷል። በፊልሙ ዘርፍ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የኦስካር ሽልማት ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።
ተዋናዩ ከቀደመ ጋብቻው ካፈራቸው መካከል ሶስቱ አባታቸው እንዲሁም ባለቤቱ መሞታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሑፍ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝር መረጃዎችን ይዟል።
የሳንታፌ ግዛት ፖሊስ ጥንዶቹ መሞታቸውን አረጋግጧል።
"የካቲት 19/ 2017 ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ የሳንታፌ ግዛት ፖሊስ ኦልድ ሰንሴት በተሰኘው ሰፈር ወደሚገኘው የጂን ሃክማን እና ቤትሲ አራክዋ መኖሪያ ቤት ፖሊሶችን አሰማራ። በስፍራውም ሲደርሱ ጥንዶቹን ጨምሮ ውሻው ሞተው ተገኝተዋል" ብሏል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ።
የፖሊስ ኃላፊው አዳን ማንዶዛ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ከሞቱ የቆዩ ይመስላሉ። ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚለውን ግምት ማስቀመጥ አልፈልግም" ብለዋል።
አክለውም "ግድያ ነው በሚለው ላይ ምንም ምልክት አላየንም። ነገር ግን ይህንን ዝም ብለን አንተወውም። ይህ ምርመራ ነው። ሁሉንም አቅጣጫዎች እናጤናለን" ሲሉ ተናግረዋል።
በመኖሪያ ቤታቸው ላይ የተገኙት መርማሪ በበኩላቸው ጥንዶቹ ከሞቱ እንደቆዩ ገልጸው ለዚህም የሰጡት ምክንያት ቤትሲ አራካዋ እጅ እና እግሯ " የመበስበስ" እንዲሁም "ግርር" የማለት ምልክቶች ታይተውባቸዋል ብለዋል።
ተዋናዩም "ከሴቷ አስከሬን ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች ታይተውበታል" ብሏል።
በቤትሲ ጭንቅላት አጠገብ ተንቀሳቃሽ ማሞቂያ የተገኘ ሲሆን ይህም ድንገት መሬት ላይ ወድቃ ከሆነ ይዛው ሊሆን እንደሚችል መርማሪዎች ተናግረዋል።
ለተዋናዩ እና ለባለቤቱ የካርቦን ሞኖኦክሳይድ እንዲሁም መርዛማ ንጥረ ነገሮች ምርመራ እንዲደረግ መርማሪዎች ጠይቀዋል።
ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ያሉት መርማሪዎች የሞታቸው መንስዔ እስካሁን አይታወቅም ተብሏል። በሐኪም የታዘዘ የመድኃኒት ጠርሙስ፣ የተበታተኑ ክኒኖች በመታጠቢያ ቤቱ ጠረጴዛ ከቤትሲ አስከሬን አጠገብ ተገኝተዋል።
የጥንዶቹ ጀርመን ሼፐርድ ዝርያ ያለው ውሻ ከቤትሲ አስከሬን አጠገብ በቁምሳጥን ውስጥ ነው የተገኘው።
ተዋናዩ ግራጫ ቀለም ያለው ቱታ፣ ረጅም እጅጌ ያለው ሰማያዊ ቲሸርት እንዲሁም ቡናማ ቀለም ሸበጥ ለብሶ ነው የተገኘው። የጸሐይ መነጽር እና ለድጋፍ የሚሆነው ምርኩዝ በአስከሬኑ አጠገብ ነበር።
መርማሪዎች ተዋናዩ በድንገት እንደወደቀ ይጠረጥራሉ።
የአሟሟታቸው ሁኔታ አጠራጣሪ በመሆኑ "ፍተሻ እና ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አግኝተነዋል" ብሏል በመኖሪያ ቤታቸው ላይ የወጣው የፍተሻ ማዘዣ።
ለፖሊስ ድንገተኛ አገልግሎት የደወለው ግለሰብ የመኖሪያ ቤታቸውን የፊት በር ተከፍቶ እንዳገኘው ተገልጿል።
ነገር ግን ቤታቸው ተሰብሮ የመግባት ምልክት እንዳልተገኘበት መርማሪዎች ተናግረዋል።
በቤታቸው ውስጥ ያልተለመደ የሚባል ነገር አልታየም ተብሏል።
ንብረቶች መበርበራቸውን ወይም እቃዎች መወሰዳቸውን የሚያሳይ ሁኔታዎች እንደሌሉም ተነግሯል።
ሌሎች ሁለት ጤናማ ውሾቻቸው በመኖሪያ ቤታቸው ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል። አንደኛው በግቢው ሁለተኛው በቤት ውስጥ።
በሰፊ ስፍራ የተንጣለለው ቤታቸው 1 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ይገመታል።
በመኖሪያ ቤታቸው የጋዝ መፍሰስ ምልክት እንዳልታየም የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ አስታውቋል። የእሳት አደጋ መስሪያ ቤት በበኩሉ የካርቦን ሞኖኦክሳይድ ጋዝ ወይም መመረዘን የሚያሳዩ ምልክቶች አላገኘሁም ብሏል።
መርማሪው በመኖሪያ ቤታቸው ጥገና የሚያከናውኑ ሁለት ሰራተኞችን አነጋግሯል። አንደኛው ለአደጋ ጊዜ አገልግሎት ስልክ የደወለው ነው።
ሁለቱ ሰራተኞች በጥንዶቹ መኖሪያ ቤት አንዳንድ ጊዜ ጥገና እንደሚያካሂዱ ገልጸው ነገር ግን ተዋናዪ እና ባለቤቱን አይተዋቸው እንደማያውቁ ገልጸዋል።
በዋናነት ከቤትሲ ጋር ቢሆንም ከጥንዶቹ ጋር በአካል እንደማይገናኙና በስልክ እና በአጭር መልዕክት እንደሚገናኙ ጠቁመዋል።
ሁለቱ ሰራተኞች ከጥንዶቹ ጋር መልዕክት የተለዋወጡት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው።
ቢቢሲ ያገኘው የ911 የስልክ ጥሪ ቅጂ የጥገና ሰራተኛው እንዴት ሁለቱን አስከሬኖች እንዳገኛቸው በድንጋጤ ሲናገር ይደመጣል።
ሰራተኛው "እየተንቀሳቀሱ አይደለም፤ እባካችሁ በፍጥነት ሰው ላኩ" ሲል ይደመጣል።
የክላሲካል ፒያኖ ተጫዋች የነበረችው ቤትሲ አራካዋ 64 ዓመቷ ነበር።
ተዋናዩ በአውሮፓውያኑ 1971 ለወጣው አስፈሪ ፊልም 'ዘ ፍሬንች ኮኔክሽን' ጂሚ በተሰኘ ገጸ ባህርይ ባሳየው ምርጥ ብቃት በምርጥ ተዋናይ ዘርፍ የኦስካር ሽልማትን ማሸነፍ ችሏል።
በአውሮፓውያኑ 1992 'አንፎርጊቭን' ፊልም ላይ ባሳየው ብቃት ምርጥ ደጋፊ ተዋናይ በመሆን ሁለተኛውን ኦስካር ማሸነፍ ችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 1967 'ቦኒ ኤንድ ክላይድ' በተሰኘ ፊልም፣ እንዲሁም በ1970ዎቹ 'አይ ኔቨር ሳንግ ፎር ማይ ፋዘር፣ በአውሮፓውያኑ 1988 ሚሲሲፒ ላይ በተጫወታቸው ገጸ ባህርያት ለኦስካር ሽልማት ታጭቶ ነበር።
ሐክማን በፊልም ኢንዱስትሪው ዘርፍ ማንኛውንም ገጸ ባህርይ መጫወት ይችላል ይባላል።
ሐክማን በነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ100 በላይ ገጸ ባህርያትን ወክሎ የተጫወተ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በአውሮፓውያኑ 1970 እና 80ዎቹ የወጡት ሱፐርማን ፊልሞች ተጠቃሾች ናቸው።
ሐክማን ከታዋቂዎቹ አል ፓቺኖ፣ ጂን ዋይልደር፣ ዋረን ቤቲ እና ዲያን ኪተን ጋር ተጫውቷል። እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ታዋቂነትን ባገኙት 'ራን አዌይ ጁሪ'፣ 'ዘ ሮያል ቴኔን ባውምስ' እና በታዋቂው ዳይሬክተር ፍታንሲስ ፎር ኮፖላ በተሰራው 'ዘ ኮንቨርሴሽን' ላይ ተጫውቷል።
ሐክማን በአውሮፓውያኑ 1930 በካሊፎርኒያ ነው ውልደቱ። ወላጆቹ ከከተማ ከከተማ ሲዘዋወሩም ነው የኖሩት።
በ16 ዓመቱ ዕድሜውን ዋሽቶ በአሜሪካ የባህር ኃይል ለአራት አመት ተኩል ያህል አገልግሏል። በቻይና፣ ሐዋይ እና ቻይና ተመድቦ የሰራ ሲሆን በ1951 ከባህር ኃይል ወጣ።
ወታደራዊ አገልግሎቱን ተከትሎ፣ ሐክማን የልጅነት ትወና ህልሙን ለማሳካት ወደ ካሊፎርኒያ ለመመለስ ከመወሰኑ በፊት በኒውዮርክ ኖሯል።
በኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን አጥንቶ በጋዜጠኝነት ስራ ዘርፍ ተሰማርቶ ነበር።












