በስዊድን የወሮበላ ቡድኖች ጥቃት በመጨመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጦር አዛዡ ጋር ሊመክሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
በስዊድን የወሮበላ ቡድኖች የሚያደርሱት ጥቃት እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጦር አዛዣቸው ጋር ለመነጋገር ጠርተዋቸዋል።
ምክክራቸውም የጦር ኃይሉ እነዚህን ጥቃቶች ለመቀነስ እንዴት ሊያግዝ ይችላል በሚለው ላይ ያተኩራል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩና በጦር ኃይሉ መሪ ምክክሩ ላይ የፖሊስ አዛዡም የሚሳተፉ ሲሆን የጦር ኃይሉ ምን አይነት ተሳትፎ ሊኖር ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ ይመክራሉ።
በስዊድን ዋና ከተማ ስቶኮልም ለ 12 ሰዓታት በዘለቀ የወሮበሎች ጥቃት ሁለት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከስቶኮልም ሰሜናዊ አቅጣጫ በሚገኝ ሌላ ከተማ ላይ 25 ዓመት ሴት ቤት ውስጥ ሳለች በደረሰ ፍንዳታ ተገድላለች። በዚህ ምክንያት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጦር አዛዣቸውን የጠሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክርስትሮሺን “ወሮበሎቹን አድነን እንይዛችዋለን። እናሸንፋቸዋለን” ሲሉም ተደምጠዋል።
የጦር ኃይሎች አዛዡ ማይክል ባይዴን በበኩላቸው ለአንድ የስዊድን ጋዜጣ በስጡት አስተያየት ጦራቸው ፖሊስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሆኖም የጦር ኃይሉ ፖሊስን ለመርዳት ምን አይነት ተሳትፎ እንደሚያደርግ አልታወቀም። ቀደም ብሎ የተደረጉ ንግግሮች ግን ወታደሮች የተወሰነ የፖሊስን ተግባር እንዲያከናውኑና ወታደራዊ ቁሶቹን ወንጀል ለመከላከል እንደሚውሉ አመላክተዋል።
ሆኖም ሊወሰድ የታቀደ እርምጃ የችግሩን መስረታዊ ምክንያት ከመፍታት ይልቅ ምልክቶቹ ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል የተቹትም አሉ።
በስዊድን የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከገባ ወዲህ እስካሁን 12 ሰዎች በወሮበላ ቡድኖች ጥቃት የተገደሉ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 2019 ወዲህ ከፍ ያለቁጥር የተመዘገበበት ነው።
የሰሞኑን ጥቃት በተመለከተ የስዊድን መገናኛ ብዙሃን ባሰራጩት ዘገባ ፎክስትሮት የተባለ የወሮበላ ቡድን የተሳተፈበት ነው ብለዋል። የዚህ ወሮበላ ቡድን አባላት እርስ በእርሳቸው ግጭት ውስጥ ግብተው ሁለት ተቀናቃኝ ቡድን ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ክርስትሮሺን ስዊድን እንዲህ ያለ ነገር ገጥሟት አያውቅም ያሉ ሲሆን “ሌላ የአውሮፓ ሀገር ይህንን የመሰለ ሁኔታ አላስተናገደም” ሲሉም ገልጸዋል።
ከስቶኮልም በስተሜን አቅጣጫ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፉሌሮ ከተማ በደረሰው ፍንዳታ አንድ ከወሮበላ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው የተባለ ሰው ጎረቤት የሆነችን ሴት ገድሏል።
ሟቿ “እጅግ በተለመደው ከምሽት እንቅስቃሴ በኃላ የተኛች ቢሆንም መልሳ እንዳትነቃ ሆናለች” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ከጥቂት ሰዓታት በኃላ ደግሞ በሌላ ቦታ በ20ዎቹ እድሜ የሚገኝ ወጣት በተከፈተበት ተኩስ ተገድሏል።
በሌላ ክስተት ደግሞ የ18 ዓመት ወጣት በስቶኮልም ስፖርት ማዘውተሪያ አቅራቢያ የተገደለ ሲሆን ስፍራው በስዎች የተሞላ እንደነበር መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ባለፈው ዓመት ከ60 በላይ ሰዎች በስዊድን በተከፈተባቸው ተኩስ የተገደሉ ሲሆን እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ዓመት ደግ ተመሳሳይ ወይም ከዚያም የከፋ እንዳይሆን ተስግቷል።












