የቻይና የኢንተርኔት ኩባንያዎች መረጃቸውን ለመንግሥት አሳልፈው እየሰጡ ነው

አሊባባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሊባባን፣ የቲክቶክ ባለቤት የሆነው ባይትዳንስን እና ቴንሴንትን ጨምሮ ግዙፍ የቻይና የኢንተርኔት ኩባንያዎች የበይነ መረብ አልጎሪዝም (ስለተ ቀመር) መረጃዎቻቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቻይና መንግሥት ተቆጣጣሪዎች አጋርተዋል።

ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) በተለይም ኮምፒውተሮች በተፈለገው መልኩ እንዲሠሩ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ ሥርዓቶች ወይም ቅደም ተከተል ያላቸው ቀመሮች ናቸው።

ስለተ ቀመር የበይነ መረን ተጠቃሚዎች የሚያዩትን እና የሚያዩበትን ቅደም ተከተል ይወስናሉ። በዚህም የማኅበራዊ ሚዲያዎችን ዕድገት ለማፋጠን ወሳኞች ናቸው።

እነዚህ መረጃዎች በኩባንያዎች በጥብቅ ምስጢርነት የሚያዙ ናቸው። 

በአሜሪካ ሜታ እና አልፋቤት የተባሉ ኩባንያዎች ይህንን መረጃ እንዲያሳውቁ በመንግሥት ቢጠየቁም የንግድ ምስጢሮቻቸው መሆናቸውን በመጥቀስ አሳልፎ ላለመስጠት ተከራክረው ተሳክቶላቸዋል።

የቻይና የሳይበር አስተዳደር (ሲኤሲ) የ30 ስልተ ቀመሮችን ዝርዝር የያዘ መረጃ ይፋ አድርጓል።

መረጃ ያለአግባብ መጠቀምን ለመግታት የስልተ ቀመር ዝርዝሩን በመደበኛነት በየጊዜው እንደሚያድሰው ተናግሯል።

ይፋ ከተደረጉት ስልተ ቀመሮች መካከል አንዱ በአሊባባ ባለቤትነት የተመዘገበው የበይነ መረብ መገበያያ መድረክ የሆነው ታኦባኦን ነው።

በማንዳሪን ቋንቋ የተዘጋጀው ሰነድ እንደሚያትተው ከሆነ የታኦባኦ ስልተ ቀመር “ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን እንዲገዙ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበው ዲጂታል አሻራ እና ቀደም ሲል ባከናወኑት ፍለጋ ላይ ተመርኩዞ” ብሏል።

ዱይን የቻይናው ቲክቶክ ማለት እንችላለን። በባይትዳንስ የሚተዳደረው ዱይን የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማወቅ የመረጡትን፣ የአስተያየት የሚሰጡበትን እና የወደዱትን ተንቀሳቃሽ ምስል ከግምት አስገብቶ ነው ተብሏል።

በትሪቪየም ቻይና የቴክኖሎጂ ፖሊሲ ጥናት ኃላፊ የሆኑት ኬንድራ ሼፈር እንዳሉት መረጃውን “ጥልቀት የሌለው” ሲሉ ገልጸዋል።

“ስልተ ቀመሮቹ ራሳቸው የገቡ አይመስልም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እነዚህ እያንዳንዳቸው ስልተ ቀመሮች የምዝገባ ቁጥር ተሰጥቷቸዋል። ስለዚህ ሲኤሲ የማስፈጸሚያ ጥረት በአንድ የተወሰነ ስልተ ቀመር ላይ ብቻ ሊያተኩር ይችላል” ብለዋል።

በምሥራቅ ቻይና የፖለቲካ ሳይንስ እና የሕግ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ጥናት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዣይ ዋይ የቀረበው መረጃ “በእርግጠኝነት ከታተመው የበለጠ ዝርዝር ነው” ብለው ያምናሉ።

“ይህም አንዳንድ የንግድ ሚስጢሮችን ስለሚያካተትት፣ ይህንን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አይቻልም” ሲሉም ለብሉምበርግ ተናግረዋል። 

ባይትዳንስ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

አሊባባ፣ ቴንሴንት፣ ኔትኢዝ እና ባይዱም ለቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

የቻይና ባለሥልጣናት በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ ቁጥጥሩን እያጠናከሩ ነው።