ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአውሮፓ እና በአሜሪካ አገራት የተከሰተው ከባድ የሙቀት ማዕበል እና ኢትዮጵያውያን
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በማጋጠሙ ነዋሪዎች ከመደበኛ እንቅስቃሴያቸው ከመገታታቸው በተጨማሪ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ታዘዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪነታቸው በጣልያን የሆኑ ኢትዮጵያውያንም በአውሮፓ እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል በጣም በነዋሪው ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑ እንደሚሉት አሁን የተከሰተው ከባድ ሙቀት ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ለተላመደው ሕዝብ ሕይወቱን አስቸጋሪ አድርጎበታል።
ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል በርካታ የዓለማችንን አገራት እያደረሰ ነው። በተለይ በደቡብ አውሮፓ አገራት የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፍተኛ ሙቀት ተጋልጠዋል።
በደቡብ አውሮፓ የሚገኙ ከተሞች ዛሬ ላይ እስከ 46 ዲግሪ ሴሊሺየስ ሙቀት ተመዝግቦባቸዋል።
ከፍተኛው የሙቀት ማዕበል የሰደድ እሳትም እየቀሰቀሰ ነው። በስፔን፣ በግሪክ እና በስዊትዘርላንድ እሳት ተቀስቅሶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።
በተለይ በደቡብ አውሮፓ አገራት የቤት ውስጥ የአየር ማቀዝቀዣ መሳሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋሉ በመሆናቸው የኤሌክትሪ ኃይል መቆራረጥ እያገጠመ ነው።
ከፍተኛ ሙቀት እየተመዘገበባቸው ከሚገኙ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ጣሊያን ነች። የዓለም ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፣ በጣልያኗ ሲሲሊ እአአ 2021 ላይ ተመዝግቦ ከነበረው የአውሮፓው ከፍተኛ ሙቀት 48.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሙቀት ተከስቷል በማለት አዲስ ሪኮርድ መዝግቧል።
ነዋሪነታቸውን በጣልያን ያረጉት ኢትዮጵያውያንም ምንም እንኳ ወቅቱ የሙቀት ቢሆንም፣ አሁን ላይ ያለው የሙቀት ማዕበል ከዚህ ቀደም አይተው የማያውቁት እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሼክ ሙዓዝ ኑሯቸው በጣልያኗ ሚላን ከተማ ነው። እርሳቸው በሚኖሩባት ሚላን የሙቀት መጠኑ ከ40 ዲግሪ ሴሌሺዬስ መሻገሩን እና በመንግሥት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ መሆኑን ይገልጻሉ።
“ከባድ ሙቀት አለ። ለምሳሌ ትናንት [ሰኞ ሐምሌ 10] ሙቀቱ 40 ደርሶ ነበር። እንደውም ወደ ሲሲሊ ሙቀቱ ከዚህ የባሰ እንደሆነ ነው የምሰማው። በቀጣይ ሳምንት ሙቀቱ እስከ 50 ዲግሪ ሴሊሺዬስ ሊደርስ እንደሚችል የሚናገሩ ሰዎች አሉ” ይላሉ።
እኚህ የሚላን ነዋሪ እንደሚሉት በዚህ የሙቀት ጊዜ ለሕጻናት እና አዛውንቶች ጥንቃቄ እንዲደረግ የአገሪቱ መንግሥት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን እየሰጠ ነው።
ሼክ ሙዓዝ በጣሊያን አብዛኛው ወቅት ቀዝቃዛ መሆኑን አስታውሰው ረዥም ጊዜ በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ውስጥ ለቆየ ነዋሪ ይህ ሙቀት በጣም ከባድ ሆኗል ይላሉ።
“ይህ አገር በብዛት ቀዝቃዛ ነው። በዓመት አብዛኛው ወራት ቀዝቃዛ ናቸው። ለዚህ ነው በተለየ ሁኔታ ሞቃት የሆነው። በአረብ አገራት ሙቀቱ 50 ዲግሪ ሴሊሺዬስ እንኳ ገብቶ ሕዝቡ ሰለለመደው ኑሯቸውን ይቀጥላሉ። እዚህ ግን ሙቀቱ 40 እንኳን ከተሻገረ በጣም እንጎዳለን። ለምን ከተባለ ሰውነታችን አልተላመደውም” በማለት ያስረዳሉ።
ከጣልያን ባሻገርም በሌሎች የአውሮፓ አገራትም ተመሳሳይ ከባድ ሙቀት ተከስቷል። በተመሳሳይ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያም እንዲሁ የሙቀቱ ሁኔታ በእጅጉ አሻቅቧል።
ባለፈው ሳምንትም በዓለም ዘመናዊ ታሪክ የዓለም ሙቀት መጠን መመዝገብ ከተጀመረበት በኋላ ከፍተኛው ነው የተባለ የሙቀት መጠን ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ. ም. ተመዝግቧል።
አሜሪካውያን አጥኚዎች እንዳሉት ይህ ሞቃት ቀን ምዝገባው ከተጀመረበት የ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ወዲህ ከፍተኛው ነው።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ለሞቃቱ ቀን መንስኤው ኤል ኒኖ የሚባለው ሞቃት የአየር ሁኔታና የሰው ልጆች የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት መብዛት ነው።
በአሜሪካ ብሔራዊ የከባቢ አየር ትንበያ ማዕከል የሚሠሩ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፣ ባለፈው ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ ከፍተኛው ሙቀት ተመዝግቧል።
ይህ ዓመት ከገባ አንስቶ ተመራማሪዎች በመሬትና በባሕር ያለውም የሙቀት መጠን መጨመር አስግቷቸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው ለሌላኛው የጣልያን ነዋሪ አብዛኛው ሰው ሥራ የሚሰራው በቤት ውስጥ ሆነ እንጂ በዚህ የሙቀት ጊዜ ከቤት ውጪ መውጣት የሚታሰብ አይደለም ይላል።
አብዶሃ የተባለው የሚላን ነዋሪ በተለይ ለባሕር ዳርቻ ቅርቡ በሆኑ የጣልያን ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ለከፍተኛ ሙቀት ተጋላጭ መሆናቸውን ጨምሮ ይናገራል።
“ከባድ ሙቀት ነው ያለው። ሚላን እንዲያውም ከባሕር ዳርቻ ርቃ ያለች ከተማ ነች። ሰው ከቤት ውስጥ ሆኖ ስለሚሰራ እንጂ ውጭ መሆን በጣም ከባድ ነው” ይላል አብዶሃ።
ሙቀት በርካታ የዓለማችን ክፍልን ያስጨንቅ እንጂ በሌላው የዓለም ክፍል ደግሞ የእስያ አገራት በካበድ ዝናብ እና በጎርፍ እየተጥለቀለቁ ነው።
ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና በሰሜን ምሥራቅ አሜሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ዝናብ እና ጎርፍ ከተከሱባቸው አገራት መካከል ይገኙበታል።
የዓለም ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ይህ ክስተት አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያሳያል ይላል።
እነዚህ በተለያየ ዋልታ ላይ ያሉ የአየር ንብረት ለውጦች በሰዎች ጤና ላይ፣ በሥነ ምኅዳር ላይ፣ በአገራት ምጣኔ ሃብት፣ በግብርና እና በውሃ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ይላሉ የዓለም ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ፔቴሪ ታላሳ።