የሮሚዮ እና ጁልየት ተዋናዮች እርቃናችን በፊልም ታይቷል በሚል ከ50 ዓመት በኋላ ካሳ ጠየቁ

ፊልሙን ሲሰሩ ገና የ15 እና 16 ዓመት ወጣቶች ነበሩ። አሁን አዛውንት ሆነዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሊዮናርድ እና ኦሊቪያ ፊልሙን ሲሰሩ ገና የ15 እና 16 ዓመት ወጣቶች ነበሩ፤ አሁን አዛውንት ሆነዋል

የዝነኛው ሮሚዮ እና ጁልየት ፊልም ተዋናይ የሆኑት ሊዮናርድ እና ኦሊቪያ የግማሽ ቢሊዮን ዶላር ካሳ ጠየቁ።

ይህን ያህል ገንዘብ ካሳ ይገባናል ብለው ክስ የመሠረቱት ፓራማውን ፒክቸርስ ፊልም አምራች ድርጅትን ነው።

እነዚህ ሁለት ዝነኛ ተዋናዮች በፈረንጆቹ 1968 ነበር በዚህ ፊልም ላይ ፍቅረኛሞች ሆነው የተወኑት።

ያን ጊዜ ገና የ15 እና የ16 ዓመት ወጣቶች ነበሩ።

ሁለቱ እንግሊዛዊ ተዋናዮች ከ50 ዓመት በኋላ ክስ እንዲመሠርቱ ያስቻላቸው ከፊል እርቃናችን ያለፈቃዳችን ለገበያ ቀርቧል በሚል ነው።

በወቅቱ የፊልሙ ዳይሬክተር የነበረው ፍራንኮ ዝፊሬሊ እርቃናችሁ አይታይም አትፍሩ ካለን በኋላ በፊልሙ ግን የተወሰነ ገላችን ያለፈቃዳችን ለዕይታ በቅቷል ብለዋል።

ስለዚህ በወጣትነት ገላችን ተነግዶበታል ያሉት ሁለቱ ተዋንያን፣ ለዚህ ሁሉ ዓመት ከፊልሙ ጠቀም ያለ ትርፍ አጋብሷል ያሉትን ፓራማውንት ኩባንያን ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ስጠን ብለውታል።

ፓራማውንት ስቱዲዮ ለጊዜው ምላሽ አልሰጠም።

የፊልሙ ዳይሬክተር የሞተው በ2019 ነበር።

ከሳሾቹ እንደሚሉት ፊልሙ ከመቀረጹ በፊት ገላቸው እንደማይታይ ዳይሬክተሩ ቃል ከሰጣቸው በኋላ ፊልሙ ሲወጣ ግን በትክክል ቃሉ አልተጠበቀልንም ብለዋል።

የመኝታ ቤት ቀረጻ ላይ ሊዮናርድ መቀመጫዬ በትንሹ ታይቷል ሲል ኦሊቪያ ደግሞ ጡቶቼ ታይተዋል ስትል ከሳለች።

ዳይሬክተሩ በኋላ ላይ ስኬታማ እንድትሆኑ እርቃናቸው በስሱ መታየት አለበት፣ አለበለዚያ ግን ፊልሙ ኪሳራ እንደሚገጥመው አግባብቶናል ሲሉ ከ50 ዓመት በኋላ ከሰዋል።

የ71 እና 72 ዓመት አዛውንት የሆኑት ሊዯናርድና ኦሊቪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ71 እና 72 ዓመት አዛውንት የሆኑት 'ሮሚዮ እና ጁልየት'

ያን ጊዜ ሊዮናርድ 16 ዓመቱ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ክሱን ሲመሠርት የ72 ዓመት ሽማግሌ ነው።

ኦሊቪያ ደግሞ ያኔ ፊልሙን ስትሠራ የ15 ዓመት ኮረዳ የነበረች ሲሆን፣ አሁን የ71 አዛውንት ናት።

የክሱ ሰነድ እንደሚያመለክተው ክሱ ወሲባዊ ብዝበዛ፣ ትንኮሳ እና ማጭበርበርን ይጨምራል።

እነዚህ ሁለት አዛውንት ተዋንያን ፊልሙ ገላችንን በማሳየቱ ሞራላዊ ጉዳት ደርሶብናል፣ በሥነ ልቦናም ተጎድተናል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ሮሚዮ እና ጁልየት የተሰኘው ሲኒማ በሼክስፒር ሥራ ላይ መሠረት ያደረገ እና በወቅቱ ትልቅ ስኬትን የተጎናጸፈ ሲሆን ለዓመታት ለዕይታ ሲበቃ የኖረ ነው።

አራት ጊዜ ለኦስካር ሽልማት ታጭቷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አሸንፏል።

ክሱ የተመሠረተው በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ነው።

ተዋናዮቹ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት ደረሰብን ብለው ክስ ይመሥርቱ እንጂ፣ በዘመናት በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች በጉዳዩ ላይ ቅሬታ አቅርበው አያውቁም።

ተዋናይት ኦሊቪያ ለምሳሌ በፈረንጆቹ በ2018 (እአአ) ሰጥታ በነበረው አንድ ቃለ ምልልስ ፊልሙ ስኬታማ እንዲሆን ያስቻለውን ዳይሬክተሩን አመስግና ነበር።

ጨምራም ከእርሷ በፊት በዚያ ደረጃ እርቃን ሆና የሠራች ደፋር ወጣት ሴት እንዳልነበረች በኩራት ከመናገሯም በላይ ሰውነቷ በከፊል መጋለጡ ለፊልሙ “አስፈላጊ ግብአት” እንደሆነ ተናግራ ነበር።

ከፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገችው ሌላ ቃለ ምልልስ ደግሞ በሮሚዮ እና ጁሊየት ፊልም ላይ የተወሰነ ገላዋ መጋለጡ በወቅቱ በአሜሪካ ባሕል “ነውር” ሆኖ ተወርቶ ነበር ካለች በኋላ፣ “ነገሩ ያን ያህልም መካበድ አልነበረትም” ብላ ነበር።