የአስክሬን ማቆያ ቤት ባለቤት የአካል ክፍሎችን በመሸጥ ወንጀል እስር ተፈረደባት

ሜጋን ሄስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የ46 ዓመቷ ሜጋን ሄስ

በአሜሪካዋ ኮሎራዶ ግዛት የቀድሞው የአስክሬን ማቆያ ቤት ባለቤት እና እናቷ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስክሬኖችን ያለ ፍቃድ በመቆራረጥና የአካል ክፍሎችን በመሸጥ ወንጀል እስር ተፈረደባቸው።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው የ46 ዓመቷ ሜጋን ሄስ አና የ69 ዓመቷ እናቷ ሽርሊይ ኮች በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2018 መካከል ባሉት ዓመታት 560 አስክሬኖችን በመቆራረጥ ያለማንም ፈቃድ የአካል ክፍሎችን ሸጠዋል።

ሁለቱ ሴቶች በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሰሩት ወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነዋል።

ይህንንም ተከትሎ ሄስ 20 ዓመታትን፣ እናት ኮች ደግሞ 15 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸዋል።

እንደ ኮሎራዶ የፌደራል አቃቤያነ ሕግ ከሆነ እናትና ልጅ የአስክሬን ክፍሎችን እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ሙሉ አካልን ለሽያጭ አቅርበዋል።

በሞንትሮዝ ከተማ የሚገኘውን ሰንሴት ሜሳ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅትን ታስተዳደር የነበረችው ሄስ፣ ባልተከናወነ የአስክሬን ማቃጠል ሥነ ሥርዓት ቤተሰቦችን 1 ሺህ ዶላር ታስከፍል የነበረ ሲሆን፣ አንዳንዴ ደግሞ የአካል ክፍሎችን እንዲለግሱ በማድረግ የአስክሬን ማቃጠል ሥነ ሥርዓት በነጻ እንዲፈፀምላቸው ታደርግ ነበር ብለዋል አቃቤያነ ሕጉ።

በዴንቨር የፌደራል ምርመራ ፖሊስ ( ኤፍቢአይ) ወኪል የሆኑት ሊዮናርድ ካሮሎ በሰጡት መግለጫ “ እነዚህ ሁለት ሴቶች በጭንቀትና በሐዘን ጊዜ ወደ እነርሱ የመጡ ሰዎችን ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ክደዋል” ብለዋል።

"እገዛ ከማድረግ ይልቅ እነዚህ ስግብግብ ሴቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጎጂዎችን እምነት በመክዳት የሚወዷቸውን ሰዎች አስክሬን አካል ቆራርጠዋል" ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።

ጉዳዩ የተጋለጠው በሮይተርስ የዜና ወኪል ምርመራ አማካኝነት ሲሆን ዘገባውን ተከትሎ ኤፍቢአይ እንደ አውሮፓውያኑ 2018 ላይ በዚህ ቤት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ እንዲያደርግ ምክንያት ሆኗል።

በአሜሪካ የአካል ክፍሎችን መሸጥ ሕገ ወጥ ሲሆን እስርን ያስከትላል። የአስክሬን አካልን መሸጥ ግን በአሜሪካ ሕግ ቁጥጥር አይደረግበትም።

ማክሰኞ ዕለት በእናት እና ልጅ ላይ የተሰማው ፍርድ በርካታ ተጎጂዎችን ስሜታዊ አድርጓል።

ዴንቨር ፖስት እንደዘገበው ናንሲ ኦቨርሆፍ የተባለች ሴት “ሜጋን የእናቴን ልብ ስትሰርቅ የእኔን ልብ ሰብራለች" ስትል ተናግራለች። ኤሪን ስሚዝ የተባለ ግለሰብ ደግሞ "ዛሬ የመጣነው እጃቸው በካቴና ሲታሰር ለማየት ነው” ብሏል።

ዳኛ ክሪስቲን አርጉሎ በበኩላቸው ጉዳዩን "በዳኝነት ልምዴ ካጋጠመኝ ሁሉ ስሜትን የሚጎዳ ነው" ሲሉ ሁለቱ ሴቶች በአስቸኳይ ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።