ቻይናዊው ሚሊየነር ለ27ኛ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ወደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይናዊው ሚሊየነር ለ27ኛ ጊዜ ከባዱን የአገሪቱን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና መውደቁን ተናገረ።
የ56 ዓመቱ ሊያንግ ሺ ባለፈው አርብ ከ750 አጠቃላይ ነጥብ 424 ብቻ ማምጣቱን ሲመለከት ለ27ኛ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን መውደቁን ተረድቷል።
ሊያንግ ፈተናውን የወደቀው ተጨማሪ 34 ነጥቦችን ማግኘት ባለመቻሉ ነው። አንድ ተማሪ ቢያንስ 458 ነጥብ ካመጣ በቻይና በሚገኝ የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር ማመልከት ይችላል።
ከተፈታኞች መካከል አንዱ የነበረው ሊያንግ ሺ ገና ፈተናውን ከመውሰዱ በፊት የመገናኛ ብዙኃን ትኩረትን ስቦ ነበር።
ከእአአ 1983 ጀምሮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምን ለመቀላቀል ያለውን ሕልም ለማሳካት ሲል ፈተናውን ሲወድስ የቆየው ሊያንግ ሺ፤ አሁን ለ27ኛ ጊዜ መውደቁ ተስፋ እንዳስቆረጠው ተናግሯል።
“አሳካዋለሁ ብዬ አምን ነበር። አሁን ግን ተስፋ ቆርጫለሁ” ሲል ለአንድ መገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች ጋአካኦ የተባለውን እጅግ ከባድ ፈተና ይፈተናሉ። ይህ ፈተና የተማሪዎችን የቻይና እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ የሒሳብ እንዲሁም እንደ ተማሪው ምርጫ የሳይንስ እና የሶሻል ሳይንስ ክህሎት እና እውቀትን ይፈትናል።
በቻይና ውስጥ በዚህ ዓመት በአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በመግባት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ለመከታተል 13 ሚሊዮን ተማሪዎች ይህን ፈተና ወስደዋል።
የቻይና መንግሥት አሃዝ እንደሚያሳየው እአአ 2021 ላይ ፈተናውን ከወሰዱት መካከል 41.6 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋምን መቀላቀል የቻሉት።
ሊያንግ ፈተናውን አልፎ ትልቅ ስም ካለው የትምህር ተቋም በዲግሪ ተመርቆ “ምሁር” መባል የሁልጊዜ ሕልሙ እንደነበረ ይገልጻል።
ሊያንግ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ ፈተና የተቀመጠው እአአ 1983 ገና የ16 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። እስከ 1992 ድረስ በየዓመቱ ፈተናውን ሲፈተን ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ከ1992 በኋላ ፈተናውን መውሰድ አቁሞ ነበር፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ፈተናውን ለሚወስዱ ተማሪዎች የዕድሜ ጣሪያ ተጥሎ ስለነበረ ነው።
እአአ 2001 የቻይና መንግሥት በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ለፈተናው መቀመጥ ይችላል ብሎ ሲያውጅ ሊያንግ መፈተኑን ቀጠለ።
ሊያንግ በትምህርት ባይሳካለትም በ1990ዎቹ በጣውላ እና የግንባታ እቃዎች ንግድ ተሰማርቶ ሚሊየነር መሆን ችሏል። ይሁን እንጂ ሊያነግ ከዩኒቨርሲቲ ካልተመረቀ ሕይወት ሙሉ ትሆናለች ብሎ አያስብም።
“ኮሌጅ መግባት ካልተቻለ ደስተኛ አያደርግም፤ ሕይወት ካለ ከፍተኛ ትምህርት ሙሉ አትሆንም” በማለት ይናገራል።
ሊያንግ ፈተናውን ለማለፍ እራሱን ከአልኮል መጠጥ እና ከጨዋታዎች ቆጥቦ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ፣ ፈተናውን በመውደቁ “በቀጣይ ዓመት የምፈተን አይመስለኝም” ብሏል።












