ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጥሎሽ ምክንያት የትዳር አጋር ማግኘት ያልቻለችው ወጣት የጀመረችው ዘመቻ
በሕንድ ከአውሮፓውያኑ 1961 ጀምሮ ጥሎሽ ሕገ ወጥ ተደርጓል። ይሁን እንጂ አሁንም የሙሽራዋ ቤተሰቦች ገንዘብ፣ ልብስ እና ጌጣጌጦች ለሙሽራው ቤተሰቦች መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
በማዕከላዊ ከተማዋ ቦህፓል በመምህርነት የምትሠራው የ27 ዓመቷ ወጣት ታዲያ ይህ 'ማኅበራዊ ጠንቅ' እንዲያከትም የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በሚፈፀምባቸው ሥፍራዎች ፖሊስ እንዲሰማራ ለመጠየቅ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምራለች።
ጉንጃን ቲዋሪ ብለን የምንጠራት ይህቺ ወጣት ፊርማ እያሰባሰበች ያለችው ከእራሷ የሕይወት ልምድ በመነሳት እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ጉንጃን በጥሎሽ ምክንያት ውሃ አጣጯን ማግኘት አልቻለችም።
በርካታ ወንዶች ለቤተሰቧ የጋብቻ ጥያቄ ቢያቀርቡም በሚጠየቀው ጥሎሽ ላይ ወላጆቿ እና የሙሽራዎቹ ወላጆች ሳይስማሙ ቀርተዋል።
በቅርቡ አባቷ ልጃቸው ጎጆ እንድትቀልስ በመመኘት ለአንድ ወጣት እና ቤተሰቡ ግብዣ አቅርበው ነበር።
ቤተሰቦቿ ከእንግዶቹ ጋር ሲጨዋወቱ ከቆዩ በኋላም ጉንጃን ሻይ እና ብስኩቶች ይዛ ወደ ሳሎን ገባች።
እርሷ እንደምትለው ሁኔታው በጣም ያስፈራ ነበር። “ሁሉም አተኩረው ይመለከቱኝ ነበር” ትላለች።
በእርግጥ ጉንጃን በእንግዶቹ ፊት እንዴት እና መቼ እንደምትቀርብ ቀደም ብሎ በጥንቃቄ ታቅዶ ነበር።
እናቷ ዐይነ ግቡ እንድትሆን አረንጓዴ ቀለም ያለው ልብስ እንድትለብስ ተጨንቀው ተጠበው መርጠውላታል።
ተስተካክለው ያልበቀሉ ጥርሶቿ እንዳይታዩም እንዳትስቅ ጉንጃንን መክረዋታል።
ጉንጃን ለዚህ አዲስ አይደለችም። ከዚህ ቀደም ስድስት ለሚሆኑ ጊዜያት ያደረገችው ነው።
አሁንም የተጠየቀቻቸው ጥያቄዎች ተመሳሳይ ነበሩ። ስለትምህርቷ እና ሥራዋ እንዲሁም ምግብ ማብሰል ትችል እንደሆነ ነበር የተጠየቀችው።
ወደ ክፍሉ ከመግባቷ በፊት ግን ወላጆቿ ምን ያህል ጥሎሽ እንደሚጠብቁ የዕጩ ሙሽራውን አባት ሲጠይቋቸው ሰምታለች።
“ከአምስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ሩፒስ (ከ61 ሺህ እስከ 73 ሺህ ዶላር) ሲጠይቋቸው ሰምተን ነበር” የምትለው ጉንጃን፣ አባቷ ሲጠይቃቸው ‘ልጅህ ቆንጆ ብትሆን እንኳን እንቀንስልህ ነበር’ ሲሉ መሳለቃቸውን ትናገራለች።
ንግግራቸው እየተራዘመ ሲሄድ ቅናሽ እንደማይደረግላቸውም ጉንጃን ገምታለች።
ሻይ ከተጠጣ በኋላም ከዕጩ ሙሽራው ጋር እንድታወራ ጥቂት ደቂቃዎች ተሰጣት። በዚህ ጊዜ ነበር በጥሎሽ እንደማታገባው የነገረችው።
“እርሱም ቢሆን ጥሎሽ ማኅበራዊ ጠንቅ እንደሆነ ይስማማል” ትላለች ጉንጃን።
ይህም ከዚህ ቀደም ከምታውቃቸው ወንዶች የተለየ እንደሆነ እንድታስብ አድርጓት ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ግን ወላጆቿ የዕጩ ሙሽራው ቤተሰቦች የሁለቱን ጥምረት እንደተዉት አወቁ።
“እናቴ የዚህ ምክንያቱ የእኔ ፀረ ጥሎሽ አቋም እንደሆነ በመግለጽ ተናደደች። ከሁለት ሳምንት በላይ ለሆነ ጊዜ አታናግረኝም ነበር” ትላለች ጉንጃን።
ጉንጃን እንደምትለው ባለፉት ስድስት ዓመታት አባቷ እርሷን ለመዳር ከ100 እስከ 150 የሚሆኑ ቤተሰቦች ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፣ ከ20 በላይ ከሚሆኑት ጋር ተገናኝተዋል።
ከዚህ ቀደም እራሷ ጉንጃንም ከስድስቱ ፊት ቀርባ ነበር።
ነገር ግን ሁሉም በሚባል ደረጃ በጥሎሽ ምክንያት የትዳር ጥያቄያቸው ሳይሰምር ተመልሰዋል።
“በዚህ ምክንያት በራስ መተማመኔን አጥቻለሁ” ትላለች በሒሳብ ሁለተኛ ዲግሪዋን የሠራችው እና በኦንላይን ትምህርቷን የምትከታተለው ጉንጃን።
“ምክንያታዊ ሆኜ ሳስበው እኔ ዕድለ ቢስ እንዳልሆንክ አውቃለሁ። ችግሩ ያለው ጥሎሽ ከሚፈልጉት ሰዎች ጋ ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ የወላጆቼ ዕዳ እንደሆንኩ ይሰማኛል” ትላለች።
በቅርብ እንደወጣ አንድ ጥናት ከሆነ፣ በሕንድ ጥሎሽ መስጠትም ሆነ መቀበል ከ60 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ሕገ ወጥ ሆኖ ቢቆይም 90 በመቶ የሚሆነው ጋብቻ በጥሎሽ የተከናወነ ነው።
በአውሮፓውያኑ 1950 እና 1999 መካከል ባሉት ዓመታት ለጥሎሽ የተከፈለው ገንዘብም ሩብ ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል።
ምንም እንኳን ጥሎሽ ለሙሽራዋ የደስተኛ ሕይወት ማረጋገጫ ባይሆንም፣ የሴት ልጆች ወላጆች ጥሎሽ ለመክፈል በርካታ ገንዘብ ከባንክ በብድር የሚወስዱ ሲሆን፣ መሬታቸውን እና ቤታቸውንም ይሸጣሉ።
እንደ ብሔራዊ ወንጀል መዝገብ ቢሮ ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 2017 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቂ ያልሆነ ጥሎሽ በማምጣት 35 ሺህ 493 ሙሽሮች ተገድለዋል። በአማካይ በአንድ ቀን 20 ሴቶች ማለት ነው።
የመብት ተሟጋቾችም በሕንድ ላለው የተዛባ የጾታ ጥምርታ አንዱ ምክንያት ጥሎሽ ነው ይላሉ።
ወላጆች ሴት ከሆነች ጥሎሽ ታስከፍለኛለች በሚል ከወሊድ በፊት የጾታ መለያ ምርመራዎችን በማካሄድ በዓመት ወደ 400 ሺህ የሚጠጉ ሴት ጽንሶች እንዲወርዱ መደረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት ግምቱን አስቀምጧል።
ጉንጃን ለቦህፓል ፖሊስ አዛዥ ሃሪናራያን ቻሪ ሚሽራ፣ ለማስገባት ባሰባሰበችው ፊርማ እንዳለችው መፍትሔው የሠርግ ፕሮግራም በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ላይ ፖሊስ መሰማራት እና ጥሎሽ የሚቀበሉትንም ሆነ የሚሰጡትን ማሰር ነው።
“ይህም ቅጣትን በመፍራት ልማዳዊ ድርጊቱን ለማስቆም ይረዳል” ብላለች ጉንጃን።
ጉንጃን በምታደርገው ትግል እንዲረዷት ለመጠየቅም ባለፈው ሳምንት ከቦህፓል ፖሊስ አዛዥ ጋር ተገናኝታ ነበር።
የፖሊስ አዛዡ የሰጧት ምላሽም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ጉንጃን ተናግራለች።
“ጥሎሽ ማኅበራዊ ጠንቅ ነው። ይህንን ለማስቆም ቆርጠን ተነስተናል። እርዳታ ለጠየቀች ማንኛዋም ሴት አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርጉ ለሁሉም የፖሊስ ጣቢያዎች መመሪያ ሰጥቻለሁ” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ፖሊስ ውስንነት እንዳለበት እና ሁሉም ቦታ መገኘት እንደማይችል በመግለጽ፣ አስተሳሰብን ለመቀየር በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል።
የሴቶች መብት ተሟጋቿ ካቪታ ስሪቫስታቫም የፖሊስ እርምጃ ድርጊቱን ለማስቆም ቢረዳም የጥሎሽ ጉዳይ ግን ውስብስብ ነው ትላለች።
“በሕንድ ጥሎሽን የሚከለክል ሕግ አለ። ይህ በትክክል እንዲተገበር ነው የምንፈልገው” ብላለች።
እርሷ እንደምትለው ጥሎሽ ምንም የማይደከምበት እና በቀላሉ ሃብታም ለመሆን ስለሚያስችል፣ በተለይ በቀላል ጥሎሽ ለማይረኩ የሙሽራው ቤተሰቦች አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ ላይሆን ይችላል። ከጋብቻ በኋላም ሊቀጥል ይችላል።
በዚህም እድሜ ልካቸውን የቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈፀምባቸው፣ አልፎ ተርፎም የሙሽራውን ቤተሰቦች ፍላጎት ባለመሟላቱ ከራሳቸው ቤት የሚባረሩ በርካታ ሴቶች እንዳሉ አንስሪቫስታቫ ትጠቅሳለች።
በመሆኑም ጥሎሽ እያደረሰ ያለው ስቃይ የሚያበቃው ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ጥሎሽ ላለመቀበል እና ላለመስጠት አቋም ሲይዙ ነው ትላለች።
“ሕይወት ረጅም ነው። ይህን ሁሉ ዘመን ብቻዬን ማሳለፍ ስለማልፈልግ ትዳር መያዝ እፈልጋለሁ” የምትለው ጉንጃን ለምታገባው ባል ቤተሰቦች ጥሎሽ እንደማትከፍል ግን እርግጠኛ ናት።
ሆኖም ጊዜ በሄደ ቁጥር ወላጆቿ ለእርሷ የትዳር አጋር ሊሆን የሚችል ሰው ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ ነው።
“የኡታር ፕራዲሽ ጎረቤት በሆነችው ኢታዋሀ መንደር ከሚኖሩት ዘመዶቼ መካከል በአንዳንዶቹ ትዳር ፈላጊዎች ዘንድ የ25 ዓመት ወጣት እንደ አሮጊት ሴት ነው የምትቆጠረው” ትላለች።
በመሆኑም አባቷ የጋዜጦችን የትዳር አፋላጊ አምድ አብዝተው ይቃኛሉ።
ይህ ብቻም ሳይሆን ለልጃቸው የሚሆን የትዳር አጋር ካገኙ እንዲነግሯቸውም ለዘመዶቻቸው አበክረው ያሳስባሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች የልጆቻቸውን ታሪክ የሚጋሩበት እና ከ2 ሺህ በላይ አባላት ያሉትን የዋትስአፕ ቡድን ተቀላቅለዋል።
“አብዛኞቹ 5 ሚሊዮን ሩፒ ወይም ከዚያ በላይ የሚያወጣ ሠርግ ይፈልጋሉ። አባቴ የሚችለው ግማሽ ያህሉን ብቻ ነው” ትላለች ጉንጃን። ያለ ጥሎሽ አገባለሁ ማለቷም የወላጆቿን ሕይወት የበለጠ አስቸጋሪ አድርጎታል።
“አባቴ ለእኔ የትዳር አጋር የሚሆን ሰው ሲያፈላልግ የቆየው ስድስት ዓመታት ብቻ እንደሆነ እና ያለጥሎሽ ግን ለ60 ዓመታት ያህል ቢፈልግም ቢያስፈልግም የትዳር ጓደኛ ሊያገኝልኝ እንደማይችል ነግሮኛል” ትላለች ጉንጃን።