ናይጄሪያውያን በዘማሪ ጓደኛዋ ተቀልታ ለተገደለችው ሴት ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው

ሳሎሜ አዳይዱ

የፎቶው ባለመብት, Salome Adaidu / Facebook

ናይጄሪያውያን የፍቅር ጓደኛዋ ነው በተባለ ዘማሪ አንገቶ ተቀልቶ ለተገደለችው ሴት ሐዘናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ እየገለጹ ነው።

ፖሊስ ዘማሪውን ቲሚሌይ አጃይን በአንድ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ በቁጥጥር ስር ሲያውለው የ24 ዓመቷን ሳሎሜ አዳይዱ ጭንቅላት ይዞ ነው።

ወጣቷ አንገቷ ተቀልቶ የተገደለችው ናሳራዋ በተሰኘችው ግዛት ነው።

ግለሰቡ ጭንቅላቷን በከረጢት ይዞ በሚንቀሳቀስበት ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎችን ትኩረት ስቦ እያፋጠጡት በነበረበት ጊዜ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል ተብሏል።

ሌሎች የግለሰቧ የተቆራረጡ የሰውነት ክፍሎች በዘማሪው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ መገኘታቸው ተዘግቧል።

ዘማሪው በቀረበበት ክስ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።

"ተጠርጣሪው የሰው ጭንቅላት ይዞ ነው የተገኘው እናም ስፍራው ላይ ደርሰን በአካባቢው ነዋሪዎች በደቦ ሊያደርስበት ከነበረው ጥቃት ታድገነዋል" ሲሉ የናሳራዋ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ራምሃን ናንሴል መናገራቸውን ፑንች የተሰኘው ድረገጽ ዘግቧል።.

ሟቿ በመዲናዋ አቡጃ የብሔራዊ ወጣቶች አገልግሎት ቡድን የተባለ ተቋም ውስጥ አባል እንደነበረች ተገልጿል። በግድያዋ ላይ ምርመራው እንደቀጠለ ፖሊስ አስታውቋል።

የሟቿ ቤተሰቦች የናይጄሪያ መንግሥት ለግድያዋ ተጠያቂ የሆኑትን አካላት በጥልቀት መርምሮ ለሕግ እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

የሟቿ ጓደኛ የሆነችው አቢ ሲሞን ከሰባት ወራት በፊት ባለቤታቸውን ያጡት ለእናቷ ልብ የሚሰብር ሁኔታ እንደሆነ ለቢቢሲ ፒጂን ተናግራለች። እናትየው የልጃቸውን አሰቃቂ ህልፈት ሲሰሙ ራሳቸውን እንደሳቱ ይህችው ጓደኛዋ ተናግራለች።

ሟቿ ገድሏታል ከተባለው ግለሰብ ጋር ግንኙነት አልነበራትም ስትል ጓደኛዋ ገልጻለች።

"ማንኛውም ሰው በዚህ መንገድ መሞት አይገባውም። የፍቅር ጓደኛው እንኳን ብትሆን በዚህ መንገድ ልትሞት አይገባትም" ብላለች።

የሟቿ እህት ፔሺየንስ አዳይዱ በበኩሏ ፖሊስ ጉዳዩን የያዘበት መንገድ እንዳሳዘናቸው ገልጻ፤ ናይጄሪያውያን እርዳታ እንዲያደርጉላት ጥሪዋን በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል አቅርባለች።

"ፖሊስ ስለ እህቴ ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጠንም። ለጥያቄዎቻችን መልስ አልሰጠንም። ፍትህን እየጠየቅን ነው። ከናይጄሪያውያን እርዳታ እንፈልጋለን" ብላለች።

የግለሰቧን ግድያ ተከትሎ ናይጄሪያውያን ሐዘናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየገለጹ ይገኛሉ።

"ሳሎሜ በሰላም እረፊ። ገዳይሽ ከሞትም በኋላ እረፍት አይኖረውም" ሲል አቭኒ ጄምስ የተባለ ግለሰብ መልዕክቱን አስፍሯል።

"በእንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው ወጣት ሴት ምሥል ልብ የሚሰብር ነው። ለቤተሰቦቿ እጸልያለሁ" ስትል አማራ ጆሴፊን የተባለች ግለሰብ በኤክስ ገጿ አስፍራለች።