የመንግሥታቱ ድርጅት በጋዛ እርዳታ ለነዋሪዎች መከፋፈል አለመጀመሩን ገለፀ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ11 ሳምንት እገዳ በኋላ ምንም እንኳ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባት ቢጀምሩም እስካሁን ምንም ዓይነት እርዳታ ለነዋሪዎች መከፋፈል እንዳልጀመረ አስታወቀ።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት 93 እርዳታ የጫኑ መኪኖች መግባታቸውን አስታውቀዋል።

መኪኖቹ ዱቄት፣ የሕጻናት ምግብ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እንዲሁም መድሃኒቶችን መጫናቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ምንም እንኳ በፍልስጤም ግዛት ኬረም ሻሎም መኪኖቹ የደረሱ ቢሆንም እርዳታ መከፋፈል አለመጀመሩን ተናግሯል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋኔ ዲጃሪክ እንዳሉት ከሆነ ቡድኑ እስራኤል በአካባቢው መንቀሳቀስ እንድትፈቅድላቸው "ለረዥም ሰዓታት ሲጠበቅ የቆየ ቢሆንም" ነገር ግን "እንደ አለመታደል ሆኖ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ መጋዘናችን ሊያመጡልን አልቻሉም" ብለዋል።

እስራኤል እሁድ ዕለት "መሠረታዊ የሆነ ምግብ" ወደ ጋዛ እንዲገባ የተስማማች ሲሆን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ረሃብ እያንዣበበ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

ይኹን እንጂ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእስራኤል ላይ የሚያደርገው ጫና እያደገ መጥቷል።

ዩኬ እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ባለችው "የሞራል ተቀባይነት የጎደለው" ወታደራዊ እርምጃ የተነሳ የሚኖራትን የንግድ ንግግር ለጊዜው እንደምታቆም ስታሳውቅ፤ ሰር ኪር ስታርመር ያለውን ሁኔታ "ልንታገሰው የማይገባ" ሲሉ ገልጸውታል።

ይህ በእንዲህ እያለ የአውሮፓ ኅብረት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ ከእስራኤል ጋር ያላቸውን የንግድ ስምምነት በጋዛ እየተፈጸመ ካለው ጋር እያጤኑት መሆኑን ተናግረዋል።

ዱጃሪክ እስራኤል የመንግሥታቱ ድርጅት እርዳታዎቹን "በፍልስጤም ኬሬም ሻሎም ግዛት አራግፎ ከተረከበ በኋላ፣ ዳግም በጋዛ ሰርጥ ወደ ሚያከፋፍልበት ስፍራ እንዲያጓጉዝ" መጠየቋን ተከትሎ የእርዳታው እንቅስቃሴ "ውስብሰብ" መሆኑን አስረድተዋል።

ምንም እንኳ የእርዳታው መግባት መፈቀዱ መልካም ቢሆንም ነገር ግን "ከሚያስፍልገው አንጻር በውቅያኖስ ላይ ጠብታ ማለት ነው" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋዛ ያጋጠመውን የከፋ የሰብዓዊ እርዳታ ቀውስ ለመፍታት በቀን 600 የጭነት መኪኖች መግባት እንዳለባቸው አስታውቋል።

ቀደም ብሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ለቢቢሲ እስራኤል በፍጥነት እርዳታ የማትፈቅድ ከሆነ በጋዛ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት ሕይወታቸውን ያጣሉ ብለው ነበር።

ፍሌቸር ከቢቢሲ ቱዴይ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ "በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት እርዳታ ገብቶ ካልደረስንላቸው 14,000 ሕጻናት ይሞታሉ" ነበር ያሉት።

እዚህ ቁጥር ላይ እንዴት እንደደረሱ የተጠየቁት ኃላፊው በጋዛ የሕክምና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች የሚሰራ "ጠንካራ ቡድን" እንዳላቸው ገልፀው ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቢቢሲ በኋላ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትን ማብራሪያ ጠይቆ "በጋዛ ውስጥ በከባድ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸው የሚገመቱ 14,000 ሕጻናትን ለመታደግ የወጣ ሪፖርት እንዳስጠነቀቀው አቅርቦቱን በተቻለ ፍጥነት በ48 ሰዓታት ውስጥ ማስገባት አለብን" ብሏል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የወጣ ሪፖርት እድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ 59 ወር የሚሆናቸው 14,100 ሕጻናት በሚያዝያ 2025 እና መጋቢት 2026 መካከል ለከፋ የምግብ እጥረት እንደሚጋለጡ አስጠንቅቆ ነበር።

ሪፖርቱ ይህ ይሆናል ያለው በ48 ሰዓታት ውስጥ ሳይሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው።

ባለፈው ሳምንት በሃማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር በ11 ሳምንታት ውስጥ በምግብ እጥረት የተነሳ 57 ሕጻናት መሞታቸውን አስታውቆ ነበር።

የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት እስራኤል እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ መፍቀዷን አድንቀዋል።

ሰኞ ዕለት የዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ በጋራ ባወጡት መግለጫ የእስራኤል መንግሥት "ወታደራዊ እርምጃዎቹን አቋርጦ" በፍጥነት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንዲፈቅድ" ጠይቀዋል።

የዩኬ መንግሥት በእስራኤል ሰፋሪዎች እና ከሰፋሪዎቹ ጋር በሚገናኙ ቡድኖች ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የጀመረቸው መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሃማስ ጥቃት ሰንዝሮ 1,200 እስራኤላውያን መግደሉን እና 251 ማገቱን ተከትሎ ነው።

እስራኤል ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረች ጀምሮ 53,475 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ሲነገር ከመጋቢት ወዲህ ደግሞ 3,340 ተጨማሪ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የግዛቲቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።